አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

መንግስት ጣና ላይ ለተደቀነው የብዝሃ ሕይወት አደጋ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል - ምሁራን Featured

02 Aug 2017
2287 times

አዲስ አበባ ሐምሌ 26/2009 በጣና ሀይቅ ብዝሃ ህይወት ላይ አደጋ የደቀነውን "እምቦጭ አረም" ለማጥፋት መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ።

መንግስት በበኩሉ የክልሉን ሃሳብ በመደገፍ እምቦጭ አረምን ማጥፋት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሀይቁን ከጥፋት ለመታደግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃና መሬት ሃብት ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጌቴ ዘለቀ እንዳሉት፣ በጣና ላይ የተከሰተው አደገኛ አረም በአጭር ጊዜ በፍጥነት ተስፋፍቶ ሀይቁን ሊያጠፋው ስለሚችል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የመከላከሉን ስራ ሊያከናውን ይገባል።

አረሙን በአስቸኳይ ማጥፋት ካልተቻለ ሃይቁ በደለል ተሞልቶ የጣና በለስን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ብሎም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ጠቁመዋል።

 ዶክተር ጌቴ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠትና የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ስርዓት በሚገባ ተጠንቶ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶክተር ከበደ ጫኔ የጣና ሃይቅ አደጋ ላይ መውደቅ በግድቡም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ መንግስት የእምቦጭ አረምን አገራዊ ስጋት አድርጎ ማየት አለበት ብለዋል።

የእምቦጭ አረም ከጣና አልፎ ጭስ አባይ አካባቢ እንደታየ ጠቁመው፤ የህዳሴውን ግድብ ህልውና በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሃይቁ ላይ የተከሰተውን አረም ለማጥፋት መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የአካባቢ ጥናትና ምርምር በማድረግ እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር የብዝሃ ህይወት ሃብቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ከወዲሁ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙሴ ያዕቆብ እና በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት ዶክተር ሚናስ ህሩይ መንግስት ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የሚሰጠውን ትኩረት ማጠናከር እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

“ጣና በዙሪያው ከሰው ጋር ንክኪ ስላለው በደለል እየተሞላ ነው፤ በእምቦጭ አረምም እየተጠቃ ነው፣ በመሆኑም መንግስት ጉዳዩን አገራዊ ጉዳይ አድርጎ መውሰድና መስራት አለበት” ብለዋል።

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጣና ላይ የተከሰተውን አደገኛ አረም ለመከላከል የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ መነደፉንና ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከባህር ዳርና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን አረሙን በዘላቂነት ማጥፋት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ለዚህም የተለያዩ አገራት የተጠቀሙበትን ልምድ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ በጊዜያዊነት ኅብረተሰቡን በማስተባበር የመመንጠር ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የፌደራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት አረሙን ለማጥፋት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

"እምቦጭ አረምን ማጥፋት የሚችል የቴክኖሎጂ አማራጭ ከየትም ይምጣ እንጠቀማለን፤ መንግስት የሀይቁን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታም አለበት" ብለዋል።

በመጀመሪያ የመንግስትና የህዝብ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የክልሉ መንግስት በስፋት እየመከረበት ያለ አጀንዳ  በመሆኑ የፌደራሉ መንግስትም እንደሚወስደው ተናግረዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ