አርዕስተ ዜና

ለሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ህልውና ቀጣይነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የፖርኩ ተነሺዎች ገለፁ

17 Jul 2017
2124 times

ጎንደር  ሀምሌ 10/2009 የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ከአደጋ የቅርስ መዝገብ እንዲወጣ መደረጉ ለፓርኩ የወደፊት ህልውና ቀጣይነት ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ የኢኮ-ቱሪዝም ማህበርና የፓርኩ ተነሺዎች አስታወቁ፡፡

 በፓርኩ ክልል ላለፉት 48 ዓመታት በእርሻና በአነስተኛ ንግድ ኑሮአቸውን መስርተው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ኑሬ መሃመድ ፓርኩ ከአለም አቀፍ የአደጋ ቅርስ መዘገብ መውጣቱ አስደስቶኛል ብለዋል፡፡

 ከሶስት ዓመት በፊት ግጭ ከተባለው የፓርኩ ክልል በፈቃደኝነት ተነስተው በደባርቅ ከተማ ኑሮአቸውን የመሰረቱት አቶ ኑሬ ''እኔና አብረን እንኖር የነበርነው 212 አባወራዎች ከፓርኩ ክልል ስንነሳ ለፓርኩ ህልውና ስጋት መሆናችንን በመገንዘብ ነው'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 ''በእርሻ፣ በልቅ ግጦሽ፣ በደን ጭፍጨፋና በህገ-ወጥ አደን ፓርኩ ላይ ጫና ፈጥረን ቆይተን ነበር'' ያሉት አቶ ኑሬ ''ከፓርኩ ክልል ለቀን መውጣታችን የፓርኩን ህልውና ዳግም ለማስቀጠል አግዟል'' ብለዋል፡፡  

 ''መንግስት 590 ሺ ብር የንብረት ካሳና የቤት መስሪያ ቦታ ጭምር ሰጥቶኝ የከተማ ህይወት መምራት ጀምሬአለሁ፤ ፓርኩን በቀጣይ ለመከባከብና ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት የበኩሌን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 ከፓርኩ ክልል በፈቃደኝነት ተነስተው በደባርቅ ከተማ ኑሮአቸውን የመሰረቱት አቶ ኡስማን አደም በበኩላቸው ''ፓርኩ ከአደጋ የቅርስ መዝገብ መውጣቱን ስሰማ ደስታ ፈጥሮብኛል'' ብለዋል፡፡

 ''ተወልጄ ከአደኩበት ቀዬ የለቀቁኩት የፓርኩን ጥቅም በማስቀደም ነው'' የሚሉት አቶ ኡስማን አሁንም ቢሆን ለፓርኩ ደህንነትና ቀጣይነት ከመንግስትና ከማህበረሰቡ ጎን በመቆም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

 የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ሀብት ቱሪዝምና ግብይት ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ስማቸው ታከለ በበኩላቸው ማህበሩ ፓርኩ ከአደጋ ቅርስ መዝገብ እንዲወጣ 7 ሺ አባላቱ ላለፉት 6 አመታት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

 በፓርኩ ክልል ልቅ ግጦሽ እንዲቀንስ፤ ህገ ወጥ አደን እንዲቆምና የደን ጭፍጨፋ እንዲቀንስ በማድረግ በተባበሩት መንግስታት የባህል፣ የትምህርትና የሳይንስ ድርጅት /ዩኔስኮ/ የተቀመጠውን ቅድመ ግዴታ እንዲሳካ ማህበሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡

 ፓርኩ ከአደጋ ቅርስ መዝገብ መውጣቱ የማህበሩ አባላት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውና ወደፊትም የፓርኩ ህልውና ተጠብቆ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለአገር ጥቅም የሚሰጥበትን በማመቻቸትና ቱሪስቶችን በአግባቡ በማስተናገድ ማህበሩ ኃላፊነቱን ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

 የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እ.አ.አ  በ1978 በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን በ1996 ደግሞ በአደጋ ተጋላጭ የአለም የቅርስ ተመዝግቦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

 ፓርኩ በሌላው ዓለም የማይገኙ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የበርካታ አዕዋፍና ጡት አጥቢ የዱር እንስሳት መገኛና ማራኪ የተፈጥሮ አቀማመጥ ያለው የመስህብ ስፍራ ነው፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ