አርዕስተ ዜና

የኢንደስትሪ ፓርኩ የአካባቢ ተስማሚነት መርሆችን የተከተለ በመሆኑ ለሌሎች ምሳሌ ይሆናል Featured

18 Jun 2017
1698 times

ሰኔ 11/2009 የሃዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ ዲዛይኑና ግንባታው የአካባቢ ተስማሚነት መርሆችን የተከተለ በመሆኑ በሃገሪቱ እየተገነቡ ላሉ ሌሎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ሞዴል እንደሚሆን ፒፕልስ ዴይሊ ድረ ገፅ ዠንዋን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡  

በሚቀጥለው ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ወደ ማምረት እንቅስቃሴ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ፓርኩ የዘመኑ የመሰረተ ልማቶችና ፋሲሊቲዎችን በሟሟላት ቀጣይነት ባለው መልኩ ጨርቃጨርቅና አልባሳትን በማምረት ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን ዘገባው ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ፓርኩን ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ማስገባቷ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያላትን ተስፋና ቁርጠኝነት ያጠናክረዋልም ነው የተባለው፡፡

የአረንጓዴ  ልማት ኢኮኖሚን ታስቦ  ዲዛይን ተደርጎ የተገነባው  የኢንደስትሪ ፓርኩ 90 ከመቶ የውሃ ፍጆታውን አክሞ መልሶ የሚጠቀምበት ዘመናዊ ቴክኖሎጂም ተገጥሞለታል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ ባሳለፍነው አርብ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም “የሃዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ፍሳሽ አልባ Zero-Liquid Discharge (ZLD) ሆኖ በመገንባቱ  ከአካባቢ ጥበቃ አኳያ  በምስራቅ አፍሪካ  እየተሰሩ ላሉ ተመሳሳይ የኢንደስትሪ ፓርኮች አርአያ መሆን ይችላል” እንዳሉ ዘገባው አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በመላ ሃገሪቱ አስር የኢንደስተሪ ፓርኮችን በመገንባት የስራ እድሎችን የማስፋት፣ገቢን የማሳደግ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የማፋጠን እቅድ እንዳለው የገለፁት ደግሞ የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ  ናቸው፡፡

ከሃዋሳው የኢንደስትሪ ፓርክ በተጨማሪ መንግስት የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ እያከናወነባቸው ከሚገኙ ቦታዎች  መካከል ኮምቦልቻ፣መቀሌ፣ቂሊንጦ ፣ቦሌለሚ II፣ድሬደዋ እና አዳማ ይገኙበታል፡፡

የመቀሌና ኮምቦልቻ ኢንደስትሪ ፓርኮች በቅርቡ እንደሚመረቁ ዘገባው አመልክቷል፡፡

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ