አርዕስተ ዜና

በሦስት ዞኖች 700 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጀ Featured

16 Jun 2017
1271 times

ነቀምቴ/ባህር ዳር/ማይጨው ሰኔ 9/2009 በኦሮሚያ፣አማራና ትግራይ ክልል በሚገኙ ሦስት ዞኖች በተያዘው የክረምት ወራት የሚተከል 700 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ተዘጋጀ፡፡

በምስራቅ ወለጋ፣ በደቡብ ጎንደርና በትግራይ ደቡባዊ ዞኖች ችግኙ የተዘጋጀው በመንግስት፣ በማህበራት፣ በአርሶ አደሮችና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች አማካኝነት ነው፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ዞን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የደን ልማት ባለሙያ አቶ ቢራቱ ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ የተራቆቱ አካባቢዎች በተያዘው ክረምት የሚተከል ከ364 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል።

ችግኙ በበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት በተካሄደባቸው በ59 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ የሚተከል ሲሆን እስካሁን 237 ነጥብ 7 ሚሊዮን  የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል።

በችግኝ ጉድጓድ ቁፋሮው ላይ ከ180 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል ።

በዞኑ ባለፈው ክረምት ከተተከለው 366 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ 75 በመቶው ጸድቋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ጎንደር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው 292 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መልካም አያሌው እንደገለጹት ለተከላ ከተዘጋጀው ችግኝ ውስጥ ከ176 ሚሊዮን የሚበልጠው ለደን ልማት የሚውሉ ግራቢሊያ፣ ግራር፣ ዋንዛና ሌሎችን ያካተተ ነው ።

ቀሪው ደግሞ  ለእንስሳት መኖና ለአፈርናውሀ ጥበቃ የሚያገለግሉ  ሳስፓኒያና የተለያዩ የሳር አይነቶች መሆናቸውን ገልፀዋል ።

በተያዘው ወር መጨረሻ ለሚጀመረው የደን ችግኝ ተከላ የሚውል ጉድጓድ ቁፋሮ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በዞኑ ባለፉት ሰባት ዓመታት በ2 ሺህ ተፋሰሶች የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በተደረገለት እንክብካቤ እያገገመ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘ በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከ36 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን  የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታውቋል፡፡

የመምሪያው የደን ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አቻምየለህ አሰፋ እንደገለፁት ለተከላ የተዘጋጀው ችግኝ ከአከባቢው ስነ- ምህዳር ጋር በቀላሉ የሚላመዱና የዝናብ እጥረት ተቋቁመው የሚያድጉ የወይራ፣ የአበሻ ጥድ፣ የኮሶ ፣ የግራርና የዋንዛ  አገር በቀል የዛፍ ችግኝ ነው፡፡

ችግኙ በዞኑ በበጋ ወቅት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በተካሄደበት 18 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ይተከላል፡፡

እስካሁንም የየአካባቢው አርሶ አደሮች 25 ሚሊዮን የችግኝ መትከያ ጉድጓድ መቆፈራቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በዞኑ ከተተከሉት ከ32 ሚሊዮን በላይ የዛፍ ችግኞች ውስጥ 77 በመቶ ፀድቆ እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ