የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ፓርክ በመሬት ወረራና ህገወጥ አደን አደጋ ተጋርጦበታል

15 Jun 2017
1283 times

አርባ ምንጭ ሰኔ 8/2009 በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ የሚገኘው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ብሔራዊ ፓርክ ህልውና በመሬት ወረራና ህገወጥ አደን አደጋ ተጋርጦበታል ተባለ።

በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖችና ሌሎች የዱር እንስሳት ቁጥር እየተመናመነ መሆኑም ነው የተነገረው።

የፓርኩ ኃላፊ አቶ ጀማል ሃሶ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ከሚፈፀመው ህገ ወጥ የመሬት ወረራና አደን ባለፈ ልቅ ግጦሽና የደን ምንጠራ ችግሩን አባብሰውታል።

ይህም በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖችና ሌሎች የዱር እንስሳት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ፓርኩ ይመጡ ከነበሩ ቱሪስቶች ይገኝ የነበረው ገቢ በእጅጉ መቀነሱንም አመልክተዋል።

ችግሩ ከአቅም በላይ መሆኑን ገልጸው የፓርኩን ህልውና ለማስጠበቅ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በፓርኩ የተከሰተው ችግር በሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎችም የሚስተዋል ቢሆንም የባቢሌው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የችግሩ መስፋት በዋናነት ከአካባቢው ህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።

ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ከአካባቢው ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ለአካባቢው ህብረተሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ