ከተሞች ለአደጋ ምላሽ የሚሰጥ አካልን ሊያቋቁሙ እንደሚገባ ተጠቆመ

14 Jun 2017
1331 times

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2009 ከተሞችን ከሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ለመጠበቅ የሚየስችል ለአደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በዘጠኙ ክልሎች ዋና ዋና ከተሞችና በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ የተካሔደው የከተሞችን ደህንነትና ለአደጋ የመጋለጥ ሁኔታ የሚያሳይ ጥናት ዛሬ ይፋ ሆኗል ።

ናቱ በአገሪቷ የሚገኙ ከተሞች በፍጥነት እያደጉ መሆናቸውን ጠቁሞ፤ ቀድመው አደጋን ለመከላከል ለአደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወንና የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ስልት መጠቀም እንዳለባቸው አመላክቷል።

በከተሞች በፍጥነት እያደገ ያለውን የሰው ኃይል ፍልሰትን፣ የውሃ እጥረትንና ጎርፍን መቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ አደጋዎቹን አስቀድሞ ለመከላከል መተግበር ያለባቸው ቁልፍ ጉዳዮች በማለት ካስቀመጣቸው የመፍትሄ ሀሳቦች መካከል ይገኙበታል።

የመሬት መንቀጥቀጥን ለመቋቋም የግንባታ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋትና በየዘርፍ መስሪያ ቤቱ አደጋን የሚመለከት ቡድን ማቋቋምም ሌላው ችግሩን ለመከላከል እንደ መፍትሄ የተቀመጡ ናቸው።

በአለም ባንክ የከተማ ልማት ባለሙያና የጥናቱ አስተባባሪ አቶ አበባው አያሌው እንደገለጹት፤ ከተሞች ለአደጋ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አካልን ሊያቋቁሙ ይገባል።

የሚቋቋመው አካልም አደጋ ሲደርስ እርዳታ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከመድረሱ በፊት መረጃ በመሰብሰብ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚሰራ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የከተማና ቤቶች ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ከተሞቹን ምቹና ከአደጋ የፀዱ ለማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ማካሔድ እንደሚያስፈልግም አመልክቷል ፡፡

ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን ፤ የአገሪቷ ከተሞች ከኢኮኖሚው ጋር በፍጥነት እያደጉ ቢሆንም "የሰው ሰራሽና ተፈጥራዊ አደጋ እንዳይገጥማቸው ካሁኑ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል" ብለዋል።

መንግስት በፍጥነት የሚያድገውን ኢኮኖሚ ለማስቀጠልና ከዚሁ ጎን ለጎን አደጋን በቅድሚያ ለመከላል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከተሞችም አደጋን ለመከላከል ለሚደረግ ዝግጅት በጀት ሊመድቡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሁሉም የክልሎች ከተሞች ለእሳት አደጋ፣ ለጎርፍ፣ ለመኖሪያ ቤትና ለመጠጥ ውሃ እጥረት የመጋለጥ እድል ሊኖራቸው እንደሚችል ጥናቱ ይገልፃል።

የጥናቱ ተሳታፊና የከተማና አደጋ ባለሙያ ወይዘሮ አስሚታ ቲዋሪ በበኩላቸው መንግስትና የከተማ አስተዳደሮች አደጋን ቀድመው ለመከላከል የተቀመጡትን የመፍትሄ ሀሳቦች ሊተገብሩ ይገባል ብለዋል።

ጥናቱ ሚኒስቴሩና የአለም ባንክ  በጋራ ያካሔዱት ሲሆን፤ የሁለት ዓመት ጊዜ መውሰዱም ተገልጿል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥናቱ ቀድሞ የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

በ2004 ዓ.ም በተደረገ ጥናት በከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 15 ሚሊዮን አካባቢ ሲሆን፤ በ2026 ዓ.ም 42 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ