አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የጣና ሀይቅ ስጋት የሆነውን የእምቦጭ አረም ለመቆጣጠር አጋር አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

14 Jun 2017
1892 times

ጎንደር ሰኔ 7/2009 የጣና ሀይቅ ስጋት የሆነውን የእምቦጭ አረም ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረገው የተናጥል ጥረት ዘላቂ ውጤት ባለማምጣቱ አጋር አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

አረሙን ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶችን የሚገመግምና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያግዝ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ዛሬ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል፡፡

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ውባለም ታደሰ እንደተናገሩት የአረሙን ስርጭት ለመከላከል የተደረጉ የተናጥል ጥረቶች ውጤት ማምጣት አልቻሉም።

"ከአምስት ዓመታት በፊት በሀይቁ ላይ የተከሰተው የእቦጭ አረም በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነምህዳራዊ  ጉዳት እያደረሰ ነው "ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምሕርት፥ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) በስነ ህይወታዊ ሀብት  የተመዘገበው የጣና ሀይቅ እያጋጠመው ባለው የአካባቢ መራቆትና የመጤ አረም መስፋፋት  ሳቢያ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

ዶክተር ውባለም "በሀይቁ ዙሪያ የሚገኙ ተፋሰሶች የእጸዋት ሽፋን መመናመን፣ በገባር ወንዞች አማካኝነት ደለል ወደ ሀይቁ በብዛት መግባት፣ በሀይቁ ዳርቻ የእርሻ ስራና የከተሞች መስፋፋት የሀይቁ ተጨማሪ የህልውና ስጋቶች ናቸው "ብለዋል፡፡

"በሀገሪቱ ሀይቆች ሲደርቁና ለመድረቅም ሲቃረቡ አይተናል የቅርብ ዓመታት ማሳያችን የሀሮማያ ሀይቅ ተጠቃሽ ነው"  ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በጣና ሀይቅ ህልውና ላይ የተደቀኑ ተደራራቢ ችግሮች ጊዜ የሚሰጣቸው እንዳልሆነም ነው ያመለከቱት፡፡

ከጥናት ፣ ከህዝባዊ ስብሰባና ምክክር በዘለለ ሀይቁን በተጨባጭ ለመታደግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ፈጥኖ በመውሰድ ሀይቁን በጋራና በቅንጅት ለመታደግ የሁሉም አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከጎንደርና ባህርዳር ዩንቨርሲቲዎች ጋርም በምርምሩ ዘርፍ ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢ ፣የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በበኩላቸው "ብሄራዊና አለም አቀፍ ሀብት የሆነው የጣና ሐይቅ በአሁኑ ወቅት የአደጋ ስጋት ተጋርጦበታል" ብለዋል፡፡

ክልሉ ባለፉት ዓመታት በሰው ጉልበት ለማስወገድ ጥረት ቢያደርግም አረሙን ከመስፋፋት መግታት  አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በአምስት ወረዳዎች 29 ሺህ 90 ሄክታር የውሃው አካል በእምቦጭ አረሙ መወረሩም ተገልጿል።

የጎንደር ዩንቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ሀይቁን የወረረው  አረም በቴክኖሎጂ የታገዝ የመከላከል ስራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ዩኒቨርሲቲው አረሙን  ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚስችል የቤተ-ሙከራ ምርምርን ጨምሮ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች በማካሄድ ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቀየው  አውደ ጥናት  በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በአካባቢ ጥበቃና ልማት ስራ የተሰማሩ መንግስታዊና መንግሰታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ተመራማሪዎችና ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ