አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በአማራ ክልል በለሙ ተፋሰሶች ከ158 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶችና አርሶ አደሮች የስራ እድል ተፈጥሯል

18 May 2017
1179 times

ባህር ዳር ግንቦት 9/2009 በለሙ ተፋሰሶች በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምእራብ ጐጃም ዞን የተለያየ ወረዳ ነዋሪ ወጣቶችና አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡

በአማራ ክልል በለሙ ተፋሰሶች ከ158 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችና አርሶ አደሮች በተለያየ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ተሰማርተዋል፡፡

ከሶስት ዓመት በፊት ስምንት ሆነው በመደራጀት በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ በሚገኘው አባ ገሪማ ሞዴል ተፋሰስ እንስሳት ማድለብ እንደጀመሩ የተናገረው ታደለና ጋሻነህ የበግ ማድለብ ሽርክና ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሲሳይ አስማረ ነው።

በወቅቱ በ10 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የጀመሩት የበግ ማድለብ ስራ፣ ወደከብት ማድለብና ንብ እርባታ በማስፋፋት አሁን ካፒታላቸውን ከ100 ሺህ ብር በላይ ማድረሳቸውን ገልጿል።

በተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ አካባቢያቸው ማገገሙ ከእርሻ ስራ በተጓዳኝ በእንስሳት ማድለብ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው  የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ የብራቃት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለልኝ ታረቀኝ ናቸው።

ከተፋሰሱ በሚያገኙት መኖ እንስሳትን በማድለብ ለሽያጭ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሦስት ዓመት ወዲህ በየዓመቱ ስድስት በሬዎችን እያደለቡ ለገበያ በማቅረብ እስከ 24 ሺህ ብር የተጣራ ትርፍ በማግኘት ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በዚሁ ወረዳ ለሁሉም ሰላም ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ በቀጭኖሽ ሞዴል ተፋሰስ ልማት በጋራ የሚል ማህበር መስርተው በንብ እርባታ እንደተሰማሩ የገለጸው ደግሞ የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ነገሰ አየሁአለም ነው።

ስምንት ሆነው በመደራጀት በአራት ሺህ 500 ብር የገዙትን 12 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በተፋሰሱ በማስገባት የጀመሩት የንብ ማነብ ስራ አሁን ላይ ወደ 20 የንብ ቀፎ ማሳደጋቸውን ተናግሯል።

ከማር ምርት ሽያጭም እስከ 13 ሺህ 500 ብር በዓመት እያገኙ ሲሆን በቀጣይም ተጨማሪ ዘመናዊ ቀፎዎችን ገዝተው የንብ መንጋ በመሙላት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሰሩ ገልጿል።

በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በተከናወነባቸውና ባገገሙ ተፋሰሶች  ከ158 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችና አርሶ አደሮች በተለያየ የገቢ ማስገኛ ስራዎች መሰማራታቸውንም የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እንግዳየሁ እንደገለጹት አርሶ አደሮቹ የስራ እድል የተፈጠረላቸው በ4 ሺ 900 ተፋሰሶች ውስጥ ነው፡፡

በእነዚህ ተፋሰሶች ወጣቶችና አርሶ አደሮች በንብ ማነብ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በደን፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም የለሙ ተፋሰሶችን ዘላቂ የሃብት ምንጭ ለማድረግና ወጣቶችን አደራጅቶ በማስገባት ተጠቃሚ ለማድረግ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ እስካሁን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነባቸው በሚገኙ 17 ሺህ 100 ተፋሰሶች ከሰባት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መልሶ እንዲያገግም መደረጉ ታውቋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ