አርዕስተ ዜና

በአርሲ ዞን ዴራ እና ኢተያ ከተሞች መካከል የተደረመሰውን መንገድ ለመጠገን ጥረት እየተደረገ ነው

13 May 2017
1364 times

አዳማ ግንቦት 5/2009 በአርሲ ዞን ዴራ እና ኢተያ ከተሞች መካከል በተከሰተው ጎርፍ የመደርመስ አደጋ የደረሰበትን መንገድ በአስቸኳይ ለመጠገን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

አዳማ ከተማን ከአሰላ ከተማ በሚያገናኘው በዚህ የአስፋልት መንገድ ላይ የመደርመስ አደጋ የደረሰው ትናንት ሌሊት በአካባቢው የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት ነው።  

የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለፁት የተከሰተው ጎርፍ በዴራና ኢተያ ከተሞች መካከል በሚገኘው የአስፓልት መንገድ ላይ ጉዳት አድርሷል።

አቶ ሳምሶን እንዳሉት፣ ላጋጠመው ችግር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፕሬሽን የጥገና ቡድን ዛሬ ወደ ስፍራው ተጉዟል።

የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብድላ ኦገቴ በበኩላቸው፣ የዞኑ መንገዶች ባለስልጣን ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ዛሬ ጠዋት ላይ ተለዋጭ መንገድ ሰርቶ ለትራፊክ ክፍት ማድረጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በትራፊክ ፖሊስ እገዛ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ መንገዱ በአስቸኳይ ካልተጠገነ በቀጣይ የከፋ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል አመልክተዋል።

ዴራና ኢተያ ከተሞች መካከል ትናንት ሌሊት ጉዳት የደረሰበት መንገድ ከአዳማ ከተማ በግምት 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ