አርዕስተ ዜና

በክልሉ ኩታገጠም የደን ልማት ተግባራዊ እየተደረገ ነው

11 May 2017
1205 times

መቀሌ ግንቦት 3/2009 በትግራይ ክልል የደን ሃብቱ በሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ  ጠቀሜታ መሰረት በኩታ ገጠም የማልማትና የመንከባከብ  ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የዘንድሮው ችግኝ የማፍላት ስራም ለኩታ ገጠም ደን ልማት ተስማሚ በሆነ መልኩ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና አጠቃቀም የስራ ሂደት መሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ 57 ሺህ ሄክታር ኩታ ገጠም መሬት በተለያየ የዛፍ ዝርያ ደን እየለማ ነው ።

ከዝርያዎቹ ውስጥ የዘይት አመንጪ፣ የማገዶና ኮንስትራክሽን፣ የቆላና ደጋ ቀርቀሃና ቁርቁራ ተጠቃሽ ናቸው ።

በተጨማሪም የእሬት፣ ሞሪንጋ፣ የእጣንና ሙጫ እንዲሁም የእንስሳት መኖ ስነ- ምህዳርን መሰረት በማድረግ በኩታገጠም እየለማ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዘይት አመንጪ ደን  ጃትሮፋ፣ ብሳና፣ ጉሎና ካንድልነት የተሰኙ የዛፍ ዝርያዎችም በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የእሬት፣ የሞሪንጋና የእጣንና ሙጫ ክላስተሮችም ለኮስሞቲክስና ለተለያዩ መድሃኒቶች መቀመሚያ እንደሚሆኑ በጥናት በመረጋገጡ ቢሮው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንኑ መሰረት በማድረግ በዚህ አመት ለኩታ ገጠም ደን ልማት ተስማሚ የሆኑ የዛፍ ዝርያዎች ችግኝ የማፍላት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

ወጣቶችን በማደራጀት ከደን ሃብቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማብቃት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አቶ ሃፍቱ አስታውቀዋል ።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ ሓበስ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉ ለማ በሰጡት አስተያየት ከ12 ዓመታት በፊት በግላቸው ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዛፎችን በመትከልና በመከባከብ  ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የተጀመረው ኩታገጠምን መሰረት ያደረገ የደን ልማት የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል ።

በትግራይ ማእከላዊ ዞን በወርዒ ለኸ ወረዳ የዘውጊ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ተክኤን ገብረህይወት በበኩላቸው በሚኖሩበት አካባቢ ለ"ሞሞና" ዛፍ ተስማሚ መሆኑ በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን ጠቁመዋል ።

"በግሌም 100 የሚሆኑ የሞሞና ዛፍ ተክየ እያለማሁ ነው " ብለዋል ።

በክልሉ 265 ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ደን በመንግስት ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑ ታውቋል ።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ