አርዕስተ ዜና

ዩኒቨርሲቲው በ150 ሚሊዮን ብር ያስገነባው የፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

21 Apr 2017
864 times

ነቀምቴ ሚያዝያ 13/2009 የወለጋ ዩኒቨርሲቲ 150 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ያስገነባው የፍሳሽ ቆሻሻ ማካሚያ ፕላንት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የዩኒቨርሲቲው የሕንጻ ግንባታና የመሰረተ ልማት ዳይሬክተር ዶክተር ደረጄ አደባ ትናንት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የማከሚያ ፕላንቱ በመንግስት በጀት ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው።

ዶክተር ደረጄ እንዳሉት ማከሚያ ፕላንቱ ከዩኒቨርሲቲው በሦስት አቅጣጫ የሚወጣውን ፍሳሽ ቆሻሻ በአንድ ቦታ በማከማቸትና በማጣራት መልሶ ለልማት ሥራ ለማዋል የሚያስችል ነው።

በተጨማሪም ፕላንቱ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ፣ የቆሸሸ ውሃን ወደ ንጹህ ውሃ የሚቀይርበት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያና  የባዮጋዝ ማምረቻ ክፍሎች እንዳሉት አስረድተዋል።

በተለይ ቆሻሻን ወደ ባዮጋዝና ማዳበሪያነት በመቀየር የአካባቢውን አርሶአደሮች በነጻ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

ፍሳሽ ቆሻሻን በማጣራት የሚገኘውን ንጹህ ውሃ ለግንባታ፣ ለመስኖ ልማትና ለሌሎች ሥራዎች  ለማዋል ጥረት እንደሚደረግም አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ደረጄ ገለጻ፣ የፍሳሽ ቆሻሻ መካሚያ ፕላንቱ በቅርቡ ሥራ ከጀመረበት አንስቶ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ ከ350 ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል።

"በአሁኑ ወቅትም ማዳበሪያውን ለአርሶአደሩ በነጻ ለማሰራጨት ዝግጅት ተደርጓል" ብለዋል።

የማጣሪያ ፕላንቱ ግንባታ ሥራ በጀርመን ዓለም ዓቀፍ የትብብር ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ) እና "አዲስ ገላው" በተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ ሥራ ተቋራጭ የተሰራ ነው።

የግንባታ ሥራው በውል ስምምነቱ መሰረት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ ቢኖርበትም ከውጭ የሚገቡ ማሽኖች ዋጋ መወደድ ምክንያት በወቅቱ ሊገቡ እንዳልቻሉና በዚህም ሥራው ሊዘገይ መቻሉን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያ ፕላንቱ ለ24 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ታውቋል።

በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊቶ ጊዳ ወረዳ የጋሪ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገመቹ ዋቅጅራ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ከዩኒቨርሲቲው የሚወጣው ቆሻሻ በአካባቢያቸው በሰዎችና በእንስሳት  ጤና ላይ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል ።

በተጨማሪም የፍሳሽ ቆሻሻው አካባቢውን በመበከሉ ልብስ የሚታጠብበት ውሃ በማጣት ለብዙ ጊዜ ሲቸገሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው የነዋሪውን አቤቱታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ባካሄደው ግንባታ ሥራ ችግሩ በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

መናገራቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ