አርዕስተ ዜና

በምዕራብ ወለጋ ዞን የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች አበረታች ውጤት አምጥተዋል

20 Apr 2017
770 times

ጊምቢ ሚያዝያ 12/2009 በምእራብ ወለጋ ዞን በበጋው ወቅት በተካሄደ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ52 ሺህ  ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት ተከልሎ ከሰውና እንስሳት ንኪኪ ነፃ መደረጉን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።፡

በፅህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሃብት የስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት መሬቱ የተከለለው በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን ቀደም ሲል ከንክኪ ተከልሎ ያገገመ 9 ሺህ 574 ሄክታር መሬት በመጭው መኸር ወቅት ወደ ምርት እንዲገባ ተወስኖ ለዘር እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል ።

በተጨማሪም ለእርሻ በሚውል ቦታ ላይ የሚገኙ 544 ሺህ 630 የምስጥ ኩይሳዎችን በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ ለማጥፋት ለአርሶ አደሩ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የነጆ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ነገዎ ጫሊ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ባለፉት አመታት በተካሄዱ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለምነታቸውን አጥቶ ከምርት ውጪ የነበረ መሬት ማገገሙ ትልቅ ነገር ነው።

አሁን መሬቱ ለእንስሳት መኖ እና ለግብርና አገልግሎትም የሚያገለግል በመሆኑ ስራቸውን እንደሚያቀልላቸው አስረድተዋል።

ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ዝናቡ ገቢሳ በበኩላቸው  "የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው አካባቢውን ወደ ለምነት እየቀየረው በመምጣቱ ለእንስሳት የሚሆን በቂ መኖ እያገኘን ነው " ብለዋል ።

የተፋሰስ ልማቱን ጠቀሜታ በተጨባጭ በመገንዘቤ ቤተሰቦቼን በማሳተፍ በማሳዬ ውስጥ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎችን እየሰራሁ ነው " ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ተራቁቶ  ከምርት ውጪ የነበረ 588 ሺህ ሄክታር መሬት አገግሞ ለእርሻ አገልግሎት መዋሉ ታውቋል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ