ከሮቤ ከተማ ቄራ የሚወጣ ፍሳሽና ተረፈ ምርት አካባቢውን እየበከለ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገለጹ

19 Apr 2017
751 times

ጎባ ሚያዚያ 11/2009 ከባሌ ሮቤ  ቄራ አገልግሎት ድርጅት የሚወጣው ፍሳሽና ተረፈ ምርት ሽታ ለተለያየ በሽታ እየዳረጋቸው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ለችግሩ ጊዜያዊና ዘላቂ  መፍትሄ ለመስጠት በእቅድ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በከተማው የኦዳ ሮቤ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መኮ ሃጂ ሁሴን  በሰጡት አስተያየት “ ከቄራው የሚወጣው ፍሳሽና ተረፈ ምርት  መጥፎ ጠረን የአስም በሽታ ታማሚ እንድሆን አድርጎኛል “ ብለዋል፡፡

ከቄራው የሚወጣው መጥፎ ጠረን በእሳቸውና በልጆቻቸው ላይ ባስከተለው በሽታ ምክንያት በተደጋጋሚ ወደ ህክምና ተቋማት በመመላለስ  ላልተፈለገ ወጪ መዳረጋቸውንም አስረድተዋል።

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሀሰን መሀመድ በበኩላቸው “ ከቄራው የሚወጣውን ፍሳሽና ተረፈ  ምርት በወቅቱ ስለማይወገድ መጥፎ ጠረን እየፈጠረ በቤት ውስጥ ለመቀመጥ የሚያስቸግር ከመሆኑ ባለፈ ለአስምና ለመተንፈሻ አካላት የጤና ችግር እየዳረገን ነው “ብለዋል፡፡

የችግሩን አሳሳቢነት በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳወቁም እሰካሁን ምንም ምላሽ እንዳላገኙ ገልፀው በአካባቢው ተረጋግተው ኑሮአቸውን ለመምራት መቸገራቸውን ተናግረዋል።  

አቶ አብዱሪ ኣደም የተባሉ ነዋሪ  ደግሞ ቤታቸው በተቋሙ አጠገብ እንደሚገኝ ገልጸው የፍሳሽ ቆሻሻው መጥፎ ጠረን የእለተ ተእለት ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ እንቅፋት እንደሆነባቸው አስረድተዋል።

“ችግሩን ለከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ብናመለክትም ምላሽ ማግኘት ባለመቻላችን አካባቢውን ለመልቀቅ እየተገደድን ነው” ብለዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የጤና አገልግሎት የስራ ሂደት  አስተባባሪ አቶ ተሾመ ደምሴ  እንዳሉት ከተቋሙ የሚወጣው ፍሳሽ ያለ አግባብ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ መለቀቁ ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት ችግር ማጋለጡን ተናግረዋል።

"የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ  ለከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ብናሳውቅም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም" ብለዋል፡፡

የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  አቶ ሽበሩ ሱልጣን ስለ ችግሩ ተጠይቀው በሰጡት አስተያያት ችግሩ የተከሰተው ለጽዳት አገልግሎት የሚውል ውሃ እጥረት በመፈጠሩ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ ቄራው በህብረተሰቡ ላይ እየፈጠረ ያለውን ችግር ለመፍታት ጊዜያዊና ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በጊዜያዊነት የቄራውን ፍሳሽና ተረፈ ምርት በአግባቡ ለማጽዳትና ለማስወገድ የውኃ አገልግሎት ሳይቆራረጥ በአካባቢው ማድረስን ጨምሮ በዘላቂነት ቄራውን ከከተማዋ ወጣ አድርጎ በፕላኑ መሰረት ለመገንባት መታቀዱንም አስረድተዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ