አርዕስተ ዜና

በምስራቅ ሸዋ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ዘንድሮ ከ62 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ እርከን ተሰራ

19 Apr 2017
633 times

አዳማ ሚያዚያ 11/2009 ምስራቅ ሸዋ ውስጥ የአፈር መሸርሸርን  ለመከላከል ዘንድሮ ከ62 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን እርከንና ሌሎችም የልማት ስራዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ  መከናወናቸውን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

በጽህፈት ቤቱ የጥምር እርሻ ባለሙያ አቶ ቦሰት ቡታ እንደገለጹት በዞኑ በተለያዩ  ጊዜያት በመሬት ላይ የሚደርሰው ጫና እያየለ በመምጣቱ የአፈር መሸርሸር እየደረሰ ነው።

እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የአፈር እርጠበት መጠንና ለምነት ቀንሷል።

ይህንን ችግር ለመከላከል ዘንድሮ በየደረጃው ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ   በመፍጠር የተቀናጀ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ ስራ ተካሂዷል።

በተለይ ባለፉት ሦስት ወራት በዞኑ በሚገኙ 10 ወረዳዎች በተደረገው ርብርብ የአፈር ክለትን  ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች መከናወናቸው ባለሙያው ተናግረዋል።

ከተከናወኑትም መካከል ከ62 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የአፈርና የድንጋይ እርከን ፣የጎርፍ መውረጃ  ቦይና  840 ሺህ ሜትር ኩብ የተለያዩ እርጥበት ማቆያ ስራዎች ይገኙበታል።

ከዚህም ባሻገር የተቦረቦሩ ቦታዎች ተለይተው በድንጋይ፣በእንጨትና በሽቦ የማሰር ተግባር ተከናውኗል።

እንደ አቶ ቦሰት ገለፃ በተጨማሪም በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጠ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ ነፃ በማድረግ የተለያዩ ግንባታዎች ተካሂደዋል።

በዘንድሮው የበጋ ወራት በተከናወኑት  የልማት ስራዎች ላይ ከ353 ሺህ በላይ የዞኑ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ከመካከላቸውም 156 ሺህ ሴቶች  ናቸው።

ባለሙያው እንዳመለከቱት በዞኑ ተፋሰስን መሰረት በማድረግ  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተከናውነውባቸው ያገገሙ ቦታዎች  ለገጠር ወጣቶች ተላልፈው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑበት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ለእርሻ አመቺ ያልሆነን መሬት የእንስሳት መኖ በማምረትና ነፋሻማ ቦታዎች ላይ ደግሞ የንብ ማነብ ሥራ በማካሄድ ለበርካታ ወጣቶች የገቢ ምንጭ ሆነዋል።

ይህም በቋሚነት የኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆኑም በተጨማሪ ተቆጣጣሪ ባለቤት ኖሮት በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሚያስችል ነው።

በዞኑ  ሉሜ ወረዳ የቆቃ ነገዎ ቀበሌ አርሶ አደር ጣፋ ነዶ በሰጡት አስተያየት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከመከናወኑ በፊት  አካባቢው የተጎዳና ከጥቅም ውጪ ሆኖ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት መሬቱ ላይ ዕፅዋት የሌለበትና አፈሩም ተሸርሽሮ እንደነበር አስታውሰው ጉዳቱን በመረዳት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን  የተጎዱ ቦታዎችን እየመረጡ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ ቀደም ሲል በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የለሙ ቦታዎችን  የጋራ ህግ በማውጣት እየተንከባከቡ በመጠበቅ ለከብቶቻቸው የግጦሽ ሳር እንደ ልብ ማግኘት እንደቻሉም ጠቁመዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ