አርዕስተ ዜና

አዳማን ከጎርፍ ስጋት ለመከላከል የተቀናጀ የልማት ስራ እየተካሄደ ነው

18 Mar 2017
937 times

አዳማ መጋቢት 9/2009 የአዳማ ከተማን የጎርፍ ስጋት በዘላቂነት ለመፍታት  የሚያስችል  65 ሺህ ነዋሪዎች የሚሳተፉበት የተራራ ላይ  የተፋሰስ ልማት ዘመቻ  ዛሬ ተጀመረ ።

ህዝቡ ከሚሰራቸው የተፋሰስ ልማት በተጨማሪ የአዳማ ከተማ አስተዳደር 150 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ ዘላቂ የጎርፍ መከላከል ተግባር እያካሄደ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ  አዳነች ሐቤቤ  ገልፀዋል ።

ከንቲባዋ የልማት ስራ ሲጀመር እንዳሉት  ዓመታትን ያስቆጠረውና ክረምት በመጣ ቁጥር የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ስጋት የሆነውን የጎርፍ አደጋ በዘላቂነት መከላከል ይገባል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት  መስተዳድሩ ፣ ባለሃብቶችና ነዋሪዎች የየድርሻቸውን ለይተው በማወቅ ወደ ተግባር ገብተዋል ።

አስተዳድሩ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዘላቂ የጎርፍ መከላከያ ጥናት በማካሄድ ለመጀመሪያው ምዕራፍ 150 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ከንቲባዋ አመለክተዋል፡፡

በተመደበው በጀትም " አዳዲስ የጎርፍ መውረጃ ቦዮች ግንባታ ፣ ነባር መውረጃዎች መጠገንና ማፅዳት ፣ የተደፈኑ ቦታዎች ከቆሻሻ ነፃ ማድረግና የአፈር መከላከል ስራ በማካሄድ ላይ ነው "ብለዋል ።

ዋነኛ የጎርፍ ምንጭ እንደሆኑ በሚታመንባቸው የሚጊራ ፣ ደንበላና ለከ አዲ ተራሮች ላይ ለ30 ቀናት የሚቆይ የተፋሰስ ስራ ዘመቻ ዛሬ የተጀመረው የከተማው ነዋሪ ህዝብ  " አዳማን ከጎርፍ ለመታደግ የላብ እንጂ የህይወት መስዋእትነት አይጠይቅም"  በሚል መርህ ነው፡፡

በዘመቻው 65 ሺህ የከተማው ነዋሪ ህዝብ የሚሳተፍ  ሲሆን ከበጋው የተፋሰስ ስራ በተጨማሪ በመጪው ክረምት 3 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱንም  ከንቲባዋ ተናግረዋል ።

"የጎርፍ ስጋቱ መፍትሔው በእጃችን ነው " ያሉት ከንቲባዋ ህዝቡ ዛሬ የጀመረውን የጎርፍ መከላከል ዘመቻ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል ።

የከተማዋ ባለሃብቶች በበኩላቸው በህብረትና በተናጠል ጎርፍ ሰብሮ ሊወጣባቸው ይችላል ተብለው የሚጠረጠሩ አካባቢዎችን  በማጠናከር የድርሻቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ