አርዕስተ ዜና

ህብረተሰቡ ሰደድ እሳትን እንዲከላከል ጥሪ ቀረበ

16 Mar 2017
673 times

አዲስ አበባ መጋቢ7/2009 ኅብረተሰቡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰት ሰደድ እሳትን አስቀድሞ የመከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አሳሰበ።

በአሁኑ ወቅት የዓለም አገራትን እያሳሰበ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተለያዩ ችግሮች በመከሰት ላይ ይገኛሉ።

ከነዚህ ችግሮች መካከል በሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት የሚከሰት የሰደድ እሳት የሚያደርሰው ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ በመምጣቱ በደን ኃብት ላይ ውድመት እየደረሰ ይገኛል፡፡

በአብዛኛው የሰደድ እሳት መነሻ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል የጫካ ማር ለመቁረጥ የሚለኮስ እሳት፣ ከሰል የማክሰል ስራ፣ ጥንቃቄ የጎደለው የእሳት አጠቃቀም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በተለይም በበጋ ወራት የሙቀት መጨመርና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በመኖሩ የሰደድ ችግር እንደሚባባስ ነው የገለፀው፡፡

በኢትዮጵያ በቅርቡ በተወሰኑ አካባቢዎች የወቅቱን ደረቃማና ነፋሻማ አየር ተከትሎ በደን ኃብቱ ላይ የተነሳው ሰደድ እሳት በህዝብና በባለድርሻ አካላት ትብብር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

የደን ቃጠሎ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ችግሮችን የሚያስከትል ሲሆን አሁንም ከወቅቱ የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ ችግሩ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

በመሆኑም የየአካባቢው አስተዳደሮች ሊኖሩ የሚችሉ የሰደድ እሳት ስጋቶችን በመለየት፣ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠርና የሰደድ እሳት የቅድመ መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም የደን ሃብታችንን ከአደጋ መጠበቅ ይገባል ብሏል፡፡

ህብረተሰቡም የሰደድ እሳት ሊያስነሱ ከሚችሉ ተግባራት በመቆጠብና ችግሩ በአካባቢው ሲፈጠርም የበኩሉን ተሳትፎ በማድረግ በመከላከሉ ስራ እንዲሳተፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪ አስተላልፏል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ