አርዕስተ ዜና

በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የሰብሎችን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት ዝናብ ይጠበቃል

15 Mar 2017
754 times

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2009 በሚቀጥሉት 10 ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የሰብሎችን የውሃ ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ዝናብ እንደሚጠበቅ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በቀጣዮቹ 10 ቀናት አብዛኞቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ዝናብ ያገኛሉ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎች የተጠናከረና ሰፊ ዝናብ ማግኘት እንደሚጀምሩም ገልጿል።

ይህም ለበልግ ሰብሎች እድገትና ለቋሚ የውሃ ፍላጎት፣ ለአርብቶ አደሮችና ለከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለመጠጥ ውሃ እንዲሁም ለግጦሽ ሳር አቅርቦት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በአንዳንድ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ደግሞ በመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት የሚኖረው ደረቃማ አየር በቡቃያም ሆነ በእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰብሎችን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት አሉታዊ ጎን እንደሚኖረው አመልክቷል።

አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚገኘውን ውሃ በአግባቡ በመያዝና ከብክነት በመከላከል ጥቅም ላይ እንዲያውል ኤጀንሲው አሳስቧል።

የባሮ አኮቦና ኦሞጊቤ፣ መካካለኛው ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም የላይኛውና የመካከለኛው አዋሽ፣ የአባይ ደቡባዊና ምስራቃዊ አጋማሽ የላይኛው ተከዜና አፋር ደናከል ተፋሰሶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።

በተጨማሪ በላይኛው ዋቢ ሸበሌና በላይኛውና መካከለኛው ገናሌዳዋ ተፋሰሶች በጥቂት ቦታዎቻቸው ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

በተፋሰሶቹ ላይ የሚገኘው ዝናብ  የአካባቢውን አየር በማቀዝቀዝ በአፈር ውስጥ እርጥበት እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ ለገጸ-ምድርና ለከርሰ-ምድር ውሃ ሃብት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ መግለጫው ጠቁሟል።

በቀሪዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው ደረቅና ፀሐያማ አየር የሰብል ስብሰባ ላላጠናቀቁ አካባቢዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክቷል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ