አርዕስተ ዜና

ከብከለት የጸዳ የኢንዱስትሪ ልማትን እውን ለማድረግ የአቅም ግንባታና የፈጠራ ክህሎት ላይ ሊሰራ ይገባል - ጥናት

15 Mar 2017
727 times

 

አዲስ አበባ  መጋቢት  6/2009 የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ከብከለት የጸዳ እንዲሆን በአቅም ግንባታና በፈጠራ ክህሎት ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አንድ ጥናት አመለከተ።

''በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፖሊሲውንና የአረንጓዴ ልማቱን ማጣጣም'' በሚል ርዕስ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ልማት ጥናት ኢንስቲትዩት ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በጋራ ያካሄዱት ጥናት ዋና ትኩረቱ በኢንዱስትሪዎችና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ትግበራ ላይ ነው።

የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች እንዲሁም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለጥናቱ የተመረጡት ኢንዱስትሪዎች ናቸው።

የጥናት ቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ሙሉጌታ እንደሚሉት የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መሰረት ያደረገ መሆኑና የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ለቀጣይ ጉዞ ተስፋ ሰጪ ነው።

''አገሪቱ አሁን በያዘችው አቅጣጫ ከቀጠለች ወደ ኢንዱስትሪ መር የምትሸጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም'' ያሉት ፕሮፌሰሩ ይህ ሲሆን አካባቢን በመበከልና የሰዎችን ጤና አደጋ ላይ በመጣል መሆን የለበትም ብለዋል።

የተቀመጠው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ትክክለኛ መሆንና መንግስት ይህን ለማስፈጸም ያለው ቁርጠኝነት፣ በበርካታ አገራት የዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ጠንካራ መሆኑ በጥናቱ ያገኘነው ትልቅ ነገር ነው ብለዋል።

''ሆኖም ግን ትግበራው ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ተመልክተናል'' ያሉት የጥናት ቡድኑ መሪ ወጥነት ባለው መልኩ ከብክለት የጸዳ የኃይል አማራጭ ለመጠቀም የሚያስችል የቴክኖሎጂ ግብዓት እጥረት አለ ነው ያሉት።

በተጨማሪም የፈጠራ ክህሎት ክፍተትና የአቅም ግንባታ እንዲሁም የግንዛቤ ችግር መኖሩ በጥናቱ ተለይቷል።

በመሆኑም ፖሊሲውን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት አጋጣሚ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መመካከርና ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም መፍጠር፣ የአረንጓዴ የኃይል አማራጭ ዘርፍ የሚፈልግውን የፈጠራ ክህሎት ማጎልበት፣ የዳታና መረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋትና ሌሎችንም የመፍትሄ አቅጣጫዎች በጥናቱ ተጠቁሟል።

ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት፣ ክፍተቶችን የሚያሳዩና ግልጽ አቅጣጫ የሚያስቀምጡ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ የተናገሩት ደግሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ናቸው።

የአየር ጸባይ መዛባትን ተከትሎ ከብክለት የጸዳ የኃይል አማራጭ መጠቀም የህልውና ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ''ቻይና፣ ሩሲያና ብራዚልን የመሳሰሉ አገራት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታቸው ሁለት በመቶ የሚሆነውን ችግሩን ለመፍታት ለሚረዱ ጥናቶች ወጪ ያደርጋሉ'' ብለዋል።

በአፍሪካ ደረጃም ጉዳዩ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ ቢሆንም አሁን ሁሉም የህብረቱ አባል አገራት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታቸው አንድ በመቶውን ለጥናትና ምርምር እንዲያውሉ ተወስኗል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉን ልማት ማፋጠን የመጀመሪያ ግብ አድርጋ እየሰራች ያለችው ኢትዮጵያ ካስቀመጥችው ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ በተጨማሪ አረንጓዴ ልማት ለመተግበር የሚረዱ ጥናቶችን ለመደገፍ ዝግጁ ናት ብለዋል ሚኒስትሩ።

አገሪቱ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችው ዕቅድ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት መቀመጡ ይታወቃል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ