አርዕስተ ዜና

በአባያ ሐይቅ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ሕብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

617 times

አርባምንጭ መጋቢት 4/2010 በአባያ ሐይቅ የተከሰተውን እምቦጭ አረም ለማጽዳት ሕብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር ጥሪ አቀረበ።

አረሙን ከሐይቁ ለማጽዳት እየተደረገ ባለው ዝግጅትና ሐይቁ ባለበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የዞኑ ምክር ቤት መክሯል፡፡

በመድረኩ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ፣ ሐይቁ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በኩል 187 ሄክታር የውሃው አካል በአረሙ ተጠቅቷል፡፡

በሌሎች ወረዳዎች በኩልም አረሙ በፍጥነት በመዛመት ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።

አቶ ኢሳያስ እንዳሉት፣ አስካሁን በሙከራ ደረጃ ከ 2 ሺህ በላይ ህዝብ በማሳተፍ ከ1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ አረሙን የማጽዳት ሥራ ተከናውኗል፡፡

ሐይቁ በውስጡ አዞን ጨምሮ በርካታ ብዝሃ ሕይወት የያዘ መሆኑ በውሃው ላይ ያለውን አረም የማስወገድ ሥራን ከባድ ስለሚያደርገው በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ምልከታዎችና ጥናቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከውሃው ውጭ ያለውን አረም በዘመቻ ለማጽዳት በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የሚመራ አብይና ንዑስ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ አረሙን ለማጽዳት በሚካሄደው ዘመቻ ሕብረተሰቡ የራሱን ሚና እንዲጫወት አቶ ኢሳያስ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዞኑ ምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ዘነበ በየነ በሰጡት አስተያየት ሐይቁን ከአረሙ የማጽዳት ሥራ ጊዜ ሳይወስድ በፍጥነት ሊከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሐይቁ ለአካባቢው ካለው ጥቅም ባለፈ ለአገር ልማትና እድገት ያለውን ፋይዳ በመረዳት  የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የዞኑ አስተዳደር የማስተባበር ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፣ ሐይቁን ከአረሙ ለማጽዳት በሚደረገው ዘመቻ ቢሮው እንደ ዋና ባለድርሻ አካል ሆኖ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና ሌሎች የትምህርት ተቋማት በዘመቻው እንዲሳተፉ ከማድረግ ባለፈ በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላትም ህዝቡን በማስተባበር የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በውይይቱ መጨረሻ ሐይቁን ከእምቦጭ አረም ለማጽዳት በሚደረገው ዘመቻ ግንባር ቀደም ሆነው እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል፡፡  

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን