አርዕስተ ዜና

በከተማዋ በደረሱ አደጋዎች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ

09 Mar 2017
1058 times

አዲስ አበባ የካቲት 30/2009 ትናንት ማምሻውን በቦሌና የካ ክፍለ ከተሞች በደረሰ የእሳት አደጋ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ።

የአዲስ አበባ እሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን እንደገለጸው የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል።

የእሳት አደጋዎቹ መንስኤ አለመታወቁንም ባለስልጣኑ ገልጿል።

አደጋው ትናንት ሌሊት 6 ሰዓት ከ25 አካባቢ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ቤልጂየም ኤምባሲ አካባቢ በሚገኙ አራት የንግድና መኖሪያ ቤቶች መከሰቱን የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአደጋውም 1 ሚሊዮን 481 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፤ የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ ስድስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል ብለዋል።

እሳቱን ለማጥፋት ባለሙያዎቹን ሲያግዙ የነበሩ ወጣቶች ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በቦሌ ወረዳ 3 በሚገኘው ጤና ጣቢያ ህክምና እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል።

አደጋው የተከሰተበት አካባቢ ቆርቆሮ ቤቶች በብዛት በመኖራቸው የእሳት አደጋውን ያባባሰው መሆኑና መንገዱ ለእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ምቹ ባለመሆኑ እሳቱን በፍጥነት መቆጣጠር አለመቻሉን ነው የተናገሩት።

እሳቱን ለመቆጣጠር አራት የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች፣ አንድ አምቡላንስና 30 ባለሙያዎች ተሰማርተዋል፤ 31 ሺህ ሊትር ውሃም ጥቅም ላይ ውሏል።

በተመሳሳይ ምሽት 2 ሰዓት ከ40 አካባቢ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ሸገር ህንጻ አጠገብ በጅምር ላይ በሚገኝ ህንጻ ላይ የደረሰ አደጋ ለግንባታ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ሙሉ በሙሉ ማውደሙን ገልጸዋል።

በአደጋው 50 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፤ የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን ነው አቶ ንጋቱ የተናገሩት።

እሳቱን ለመቆጣጠር አንድ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪና 10 ባለሙያዎች ተሰማርተዋል፤ 1 ሺህ 500 ሊትር ውሃም ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመዋል።

ሰሞኑን የሚታየው ነፋሻማና ሞቃታማ አየር ለእሳት ቃጠሎ መባባስ ምቹ አጋጣሚን እንደሚፈጥርና ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይልና የቤት ውስጥ እቃዎችን በጥንቃቄ መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል። 

የእሳት አደጋ ሲከሰት የመዲናዋ ነዋሪ በነጻ የስልክ መስመር 939 ወይም 011-155-53-00 በመደወል ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ተናግረዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ