አርዕስተ ዜና

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ለእንስሳት እርባታና ለመስኖ ልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል....የአጽቢ ወንበርታና የክልተ አውለአሎ ወረዳ ነዋሪዎች

08 Mar 2017
841 times

መቀሌ የካቲት 29/2009 በአካባቢያቸው የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ለእንስሳት እርባታና ለመስኖ ልማትሥራ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የአጽቢ ወንበርታና የክልተ አውለአሎ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት፣ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ተሯቁቶ የነበረው የአካባቢያቸው መሬት መልሶ እንዲያገግም አድርጓል።

ይህም የእርሻ መሬት የሌላቸው ወጣት አርሶአደሮች ኑሮአቸው በንብ ማነብ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ ሥራ እንዲመሰረት  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡

በዞኑ አጽቢ ወንበርታ ወረዳ ሀየሎም ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወጣት ገብረሕይወት ኃይሉ እንደገለጸው ቀደም ሲል የራሱ የሆነ  የእርሻ መሬት አልነበረውም፡፡

በአካባቢው ከሃያ ዓመታት በላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸው እርሱን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ዕድል ፈጥሯል።

ተዳፋትና ተራራማ ቦታዎች መልማታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኝ የ"ገርጋራ ወንዝ" የውሃ መጠን መጨመሩን ገልጾ፣ ይህም አንድ ሄክታር መሬት ተከራይቶ በመስኖ ልማት እንዲሰማራ ማድረጉን ተናግሯል።

የመስኖ ልማት በጀመረበት 2005 ዓ.ም ከምርቱ ሀያ ሺህ ብር ማግኘቱን የገለጸው ወጣት ገብረሕይወት፣ በቀጣይ የመስኖ ልማቱን በማጠናከር ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጿል።

ተራቁቶ የነበረው አካባቢ መልሶ ማገገም በመቻሉ በንብ ማነብና በእንስሳት እርባታ ሥራ ተሰማርቶ ኑሮውን እየመራ መሆኑን የተናገረው ደግሞ በወረዳው የአሳብሎ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወጣት ርእሶም ኃይሉ ነው፡፡

ከስድስት ዓመታት በፊት በስደት ወደሳዑዲ አረቢያ ሄዶ የነበረ ቢሆንም  ምንም ሀብትና ንብረት ሳያፈራ ባዶ እጁን መመለሱን ተናግሯል።

"አገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ቆርጨ ወደ ሥራ በመግባቴ በአሁኑ ወቅት የስልሳ ዘመናዊ ቆፎና የሰማንያ በግና ፍየል ባለቤት ለመሆን ችያለሁ" ብሏል፡፡

በየዓመቱ ከሁለት ኩንታል ማር በላይ  እንሚያመርት የተናገረው ወጣት ርዕሶም በአካባቢያቸው የመንገድ መሰረተ ልማት አለመዘርጋት ምርቱን በቀላሉ ወደ ገበያ ለማቅረብ እንቅፋት እንደሆነበት ገልጿል፡፡

ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎችን ተጠቅመው በእንስሳት ማድለብ ሥራ መሰማራታቸውን የገለጹት በክልተ አውለአሎ ወረዳ የጻእዳ ናዕለ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ሴት አርሶአደር ብረሀ አብረሀ ናቸው፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተከናወነበት ቦታ  ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ ነጻ መደረጉ የእንስሳት መኖ ለማግኘት እንዳስቻላቸው ነው የገለጹት፡፡

ከእርሻ ሥራ በተጨማሪ በዓመት ሦስት ጊዜ በጎችን እንደሚያደልቡና ከአንዱ በግ እስከ ስድስት መቶ ብር ትርፍ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአጽቢ ወንበርታ ወረዳ እርሻና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይላይ ገብረ በበኩላቸው ፣ ላለፉት ዓመታት ባተካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መስኖና ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች እንዲስፋፉ መደረጉን ገልጸዋል።

የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች የከርሰ ምድር ውሀ እንዲጨምር ማድረጋቸውን ገልጸው፣ "ይህም የመስኖ ልማት ሥራ እንዲካሄድ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው" ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ስድስት ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እቅድ ተይዞ እስከ አሁን 4 ሺህ 629 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን  የገለፁት አቶ ኃይላይ በዚህም 8 ሺህ 700 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በንብ ማነብና በደን ልማት ለሚሰመሩ በማህበር ለተደራጁ 7 ሺህ 20 ወጣቶች የለማውን ተደፋት መሬት ተንከባክበው እንዲጠቀሙ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ