አርዕስተ ዜና

ድርቁን በዘላቂነት ለመቋቋም በየአካባቢው የሚገኘውን የውሃ ሀብት ለመጠቀም እየተሰራ ነው Featured

07 Mar 2017
891 times

አዲስ አበባ የካቲት 28/2009 እንስሳትን ከማርባት ጎን ለጎን በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ለማምረት በመሞከራቸው ድርቁ በተከሰተበት ወቅት ራሳቸውን ለመደጎም መቻላቸውን የቦረና እና ጉጂ ዞኖች አንዳንድ ነዋሪዎች ገለጹ።

የዞኖቹ አስተዳደሮችም የተከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለመቋቋም እንዲቻል በአካባቢው የሚገኘውን የውሃ ሃብት ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በተከሰተው ድርቅ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎቿ ለእለት እርዳታ ተጋልጠው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ መንግስት ባደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ችግሩን ለመቋቋም ተችሏል።

ዘንድሮ ቁጥሩ ወደ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዝቅ ያለ ሲሆን፤ ከነዚህ ተረጂዎች መካከል ሁለት ሚሊዮኖቹ በኦሮሚያ ክልል የቦረና፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ እንዲሁም ምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ ውስጥ ይገኛሉ።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቅኝት ባደረገባቸው የቦረና ሁሉም ወረዳዎች፣ በጉጂ ደግሞ ካሉ ሰባት ወረዳዎች አምስቱ ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ እንስሳት በተለይም ከብቶች ለአደጋ እየተጋለጡ ናቸው።

በድምሩ ከ637 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችም የምግብ፣ የመጠጥ ውሃና የተጨማሪ ምግብ እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ከዘላቂ መፍትሄ አኳያ አርብቶ አደሩ እንስሳት ከማርባት ጎን ለጎን በዞኖቹ ያሉ ወንዞችንና የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም የእርሻ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።

ለዚህ ተግባር በጉጂ ዞን የባሮ እና ደዋ ወንዞች፣በአካባቢው ያለው የከርሰ ምድር ውሃ ጥቅም ላይ ውለዋል። በቦረና ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች በቀላሉ የሚወጡ የከርሰ ምድር ውሃ መኖሩም ተመልክቷል።

አሁን በተፈጠሩት እድሎች ተጠቅሞ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት የጀመሩ የዞኖቹ ነዋሪዎችም ራሳቸውን መደጎም መቻላቸውን ይናገራሉ።

የጉጂ ዞን ጎሮ ዶላ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አሚኖ አሊ እና በቦረና ዞን ሚዮ ወረዳ ነዋሪ አርብቶ አደር ራቾ ኮንሶሌና ዱብ ኮንሶሌ ተመሳሳይ ሀሳብ ያቀርባሉ።

አርብቶ አደሩ “ከብት ከማርባት ጎን ለጎን የኤክስቴንሽ ስራ በመከናወኑ ለውጥ እየመጣ ነው” የሚሉት የጉጂ ዞን አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ዱሎ ናቸው።

የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሊባን ኤሬሮ በበኩላቸው፤ ''በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ድርቅ ለመቋቋም አርብቶ አደሩን ሌሎች ተጨማሪ የግብርና ስራ ላይ ማሰማራት ግድ ነው'' ብለዋል።

“የዞኑን የከርሰ ምድር ውሃ አውጥቶ መጠቀምና በክረምት ወቅት የሚፈሰውን የዝናብ ውሃ አቁሮ ማቆየት ድርቅ በሚመጣበት ጊዜ እንስሳቱን ለማጠጣት፣ ከዚያም አልፎ በመስኖ ለማምረት ይረዳን ነበር ግን ይህ ባለመሆኑ አሁን ለችግር እየተጋለጥን ነው” ሲሉም አክለዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ