አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የአፍዴራ የጨው ሐይቅ ጥልቀት 80 ሜትር መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል

17 Feb 2017
1137 times

አዲስ አበባ  የካቲት 10/2009  የአፍዴራ የጨው ሐይቅ ትልቁ ጥልቀት 80 ሜትር እንደሆነ በስፍራው ጥናት የሚያካሂዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምድር ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ገለጹ።

የስነ-ምድር መዋቅራዊ ጂኦሎጂ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ተስፋዬ ኪዳኔ እንደተናገሩት ቀደም ሲል የተካሄዱ ጥናቶች የአፍዴራ ሐይቅ ጥልቀት 250 ሜትር እንደሆነ ነው የሚያሳዩት።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት አንድ የተመራመሪዎች ቡድን ሐይቁን በጀልባ በመቃኘትና ኢኮ ሳውንደር በተባለ ዘመናዊ የመለኪያ መሳሪያ በመጠቀም የባት ሜትር ጥልቀቱ ከዚህ በፊት በገመድ ከተለካው የተለየ መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የስነ-ምድር ትምህርት ክፍል ከዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር የሐይቁን አጀማመር የተመለከተ ጥናት እያካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አጥኚ ቡድኑ የሐይቁን ቅርጽና ጥልቀት የሚገልጽ ካርታ እንደሚሰራ ገልጸው ጥናቱ የጨዋማነቱን ምንጭና ከቀይ ባህር ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያካትት ተናግረዋል።

ሐይቁ ከስምጥ ሸለቆ በተለይም ከኤርታሌ፣ ከታታሌና ከአላይታ ሰንሰለታማ ተራሮች ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል የሚለውም የጥናቱ አካል ነው ብለዋል።

"እስካሁን ጂኦሎጂያዊ መረጃ የሚያሳየን ከ250 ሺህ ዓመት በፊት የቀይ ባህር ውሃ ዳሎልን፣ ባዳን፣ አፍዴራንና ኤርታሌን ሸፈኖ እንደነበር ነው" ብለዋል ተመራማሪው።

መረጃዎቹ በአካባቢው የሚገኙት ኮራልስ የሚሰኙ አለቶች በቀይ ባህር ላይ ከሚገኙት ጋር እንደሚመሳሰሉ ያሳያሉ ነው ያሉት።

"ባዳ 3 ኪሎ ሜትር የፖታሽ ጨው ክምችት ትቶ በአሁኑ ወቅት ውሃ የለውም" ያሉት ተመራማሪው "አፍዴራ ላይ አሁንም ጨዋማነቱ ከፍ ያለ ሐይቅ የተገኘበት ምክንያትና የውሃው ምንጭ የምናጠናው ጉዳይ ነው" ብለዋል።

የአፍዴራ ሐይቀ ከቀይ ባህር ጋር ከተለያየ ወዲህ ውሃ ከየት እንደሚያገኝ እስካሁን አለመታወቁንና ቀደም ሲል ምንጩ ቀይ ባህር ይሆናል የሚል ግምት እንደነበር አውስተዋል።

የአፍዴራ ውሃ ከታታሌ፣ ኤርታሌና ሌሎች አካላት ጋር ያለው ግንኙነትም በጥናቱ የሚታይ ጉዳይ መሆኑን ገለጸዋል።

ቀይ ባህር በምን ምክንያት እንደተዘጋና ከስምጥ ሸለቆ ጋር እንደተለያየ ሁለት መላ ምቶች እንዳሉ ጠቁመው የአፍዴራ ውሃ እየተነነ በሄደ ቁጥር የጨዉ መጠን እየጨመረ መሄዱን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን አፋር ውስጥ በርካታ ጥናቶች እንደሚያካሂድና የኤርታሌ እሳተ ገሞራ ክስተት ክትትልን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ሳይንስ ጥናቶች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ