አርዕስተ ዜና

በዞኑ ነባር ተፋሰሶችን መልሶ የማልማት ስራ እየተካሄደ ነው

15 Feb 2017
1138 times

ጎንደር የካቱት 8/2009 በሰሜን ጎንደር ዞን በእንክብካቤ ጉድለት ጥቅም ያልሰጡ ነባር ተፋሰሶችን በመለየት መልሶ የማልማት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

አርሶ አደሮች በበኩላቸው ተፋሰሶቹን በተጠናከረ መንገድ አልምተውና ጠብቀው በዘላቂነት ለመጠቀም እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛት ጀመረ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከለሙ 1 ሺህ 54 ተፋሰሶች መካከል 994ቱ በእንክብካቤና በጥበቃ ጉድለት ጥቅም ላይ አለመዋላቸው በግምገማ ተረጋግጧል፡፡

ተፋሰሶች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ተጠብቀውና ዘላቂነት ባለው መንገድ ለምተው ጥቅም እንዲሰጡ በማድረግ በኩል ሰፊ ክፍተት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ የበጋ ወራት የፈራረሱ እርከኖችና ክትሮች ተመልሰው እንዲሰሩና ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተጠብቀው በአጭር ጊዜ እንዲያገግሙ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተፋሰሶቹ ለገጠር ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩበት፣ በስነ ህይወታዊ ዘዴ የሚጠናከሩበት፣ ለእንስሳት ሀብት ልማት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬና ለደን ልማት ግልጋሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የልቅ ግጦሽ መስፋፋት ተፋሰሶች ዘላቂነት ያለው ጥቅም እንዳይሰጡ እንቅፋት መፍጠሩን የተናገሩት አቶ ግዛት ችግሩን ለመቅረፍ አርሶአደሩ የቤት እንስሳቱን አስሮ የመቀለብ ባህል እንዲያጎለብት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተፋሰሶች ላይ የሚፈጸሙ ጥፋቶችን ለመከላከል በየወረዳው ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተፋሰስ ኮሚቴ እንዲዋቀርና ህገ-ደንብ በማውጣት አጥፊዎችን ለመቅጣትና ለማረም የሚያስችል ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡ 

ዘንድሮ በህዝብ ንቅናቄ በሚከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ በአንድ ሺህ 54 ነባርና በ60 አዲስ ተፋሰሶች ላይ 10ሺ ሄክታር የሚሸፍን የእርከንና ክትር ስራ ይከናወናል፡፡

የአዲአርቃይ ወረዳ የአባው ማር ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሙላው ታፈረ  እንዳሉት ''የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው ጠቅሞናል፤ ምርታችን እንዲጨምርና ለከብቶቻችን የመኖ ሳር እንድናገኝ ረድቶናል'' ብለዋል፡፡

በጃናሞራ ወረዳ የአረጋይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ትዛዙ ወረታው በበኩላቸው ''የተፈጥሮ ሀብት ልማት በሰራንባቸው ቦታዎች ለሰውም ሆነ ለእንስሳት የሚውል የመጠጥ ውሃ በበጋው ጭምር ማግኘት ጀምረናል'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በጥር አጋማሽ በተጀመረው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ከ700 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በልማት ቡድን ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን እስከ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ ይቀጥላል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ