አርዕስተ ዜና

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጀመረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ውጤት እያስገኘ መሆኑ ተገለፀ

15 Feb 2017
1153 times

ሀረር የካቲት 8/2009 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጀመረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት መርሀ ግብር ውጤት እያስገኘ መሆኑን  አስታወቀ።

ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን በአካባቢያቸው ባከናወኑት የተፋሰስ ልማት አነስተኛ ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶች በመቆፈር ውሀ ማግኘት መጀመራቸውን ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ገልፀዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአፈር ሳይንስ መምህርና የሀረማያ ተፋሰስ ልማት ስራ አስተባባሪ አቶ ተፈሪ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት በደን መጨፍጨፍና አሉታዊ የመሬትና የከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀም የሀረማያ ሐይቅን ጨምሮ ሌሎች ሐይቆችና ምንጮች እንዲደርቁ ምክንያት ሆኗል።

ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል የተመለከተው ዩኒቨርሲቲው ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ከ2006 አ.ም ጀምሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት መርሀ ግብር ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

በዳሞታ፣ ጢኒቄና በጨቄ ቀበሌዎች በ100 ሄክታር ላይ 140 ኪሎ ሜትር የእርከንና ሌሎች የአፈርና ውሀ እቀባ ስራዎች በማከናወን በተለያዩ የእፅዋት ችግኞች እንዲሸፈን መደረጉን ጠቁመዋል ።

አርሶ አደሩን በማሳተፍ በተከናወነው የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ  የአካባቢው ልምላሜ ከመመለስ ባለፈ ደርቀው የነበሩ ምንጮች መፍለቅ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችም በመደራጀት በስፍራው ላይ በንብ ማነብ፣ በከብት ማድለብና እርባታ እንዲሳተፉ  በማድረግ አበረታች ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በራሱ አቅምና ህብረተሰቡን በማስተባበር እያከናወነ የሚገኘውን መልሶ የማልማት ስራን አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣዩቹ አራት ዓመታት ውስጥ የጠፋውን የሐረማያ ሐይቅና ሌሎች ምንጮችን ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ ተፈሪ ገልጸዋል።

በሐረማያ ወረዳ የዳሞታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዘይላን ኑሬ ጃማ በሰጡት አስተያየት ከሶስት አመት በፊት የዩኒቨርሲቲው መምህራን ህብረተሰቡን በማስተባበር  በጀመሩት የአፈርና ውሀ እቀባ ስራ በአካባቢው ደርቀው የነበሩ ምንጮች መፍለቅ ጀምረዋል ።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አህመድ ሲራጅ በበኩላቸው ቀደም ሲል ጥልቅ ጉድጓድ ቢቆፍሩም ውሃ ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ግን አነስተኛ ጉድጓዶችን ቆፍረው ውሃ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ