አርዕስተ ዜና

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እየተደረገ ነው Featured

12 Feb 2017
884 times

ጅግጅጋ  የካቲት 5/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የአደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሥራ ሂደት አስተባባሪ  አቶ አብዲራዛቅ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፣  በክልሉ አንድ ሚሊዮን 697 ሺህ 794 ዜጎች ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በጥናት ተለይቷል።

በድርቁ ምክንያት የቤት እንስሳት ተክለ ሰውነት ከመቀነሱ ባለፈ በገበያ ላይ ያላቸው ተፈላጊነትንም ሆነ አርብቶአደሩ ከእንስሳት ያገኝ የነበረው ጥቅም እየቀነሰ መምጣቱን ስረድተዋል።

በአሁኑወቅት 31 ሺህ 452 ሜትሪክ ቶን ስንዴ፣ አልሚ ምግብ፣ ዘይትና ጥራጥሬ ቀርቦ ለሕብረተሰቡ በመከፋፈል ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 6 ሺህ 689 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግብ ለ119 ሺህ 724 ለሚያጠቡ፣ ለነፍሰ ጡር እናቶችና ሕጻናት የቀረበ ነው።

በመጪዉ ሚያዚያና ግንቦት ወራት በክልሉ የሚጠበቀው ወቅታዊ ዝናብ ካልጣለ የተረጂዎች ቁጥር አሁን ካለው በላይ ሊጨምር እንደሚችል አቶ አብዲራዛቅ ጠቁመዋል።

ድርቁ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመቆጣጠር የሚመለከታቸው አካለት ርብርብ እንዲያደርጉም አቶ አብዲራዛቅ ጠይቀዋል።

የቢሮዉ ምክትል ኃላፊ አቶ አንዋር አሊ በበኩላቸው፣ በአርብቶአደሩ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ከተጠቁ የአገሪቱ ክልሎች  የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አንዋር እንዳሉት፣ ባለፈው ታህሳስ ወር በተካሄደ ጥናት በክልሉ ካሉ 93 ወረዳዎች መካከል በ67ቱ የሚኖሩ አርብቶአደሮች በከፋ ሁኔታ ለውሃና ለመኖ እጥረት መጋለጣቸው ተረጋግጧል።

ሲቲና ፋፈን ዞኖች ጨምሮ የተቀሩት የክልሉ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በተፋስስ ወንዞች ዳርቻ የሚገኙ ነዋሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ተጋላጭ አለመሆናቸውን አመልክተዋል።

በድርቁ የተጋለጡት አርብቶአደሮች ለእንስሳዎቻቸው ውሃ እና ሣር  ለማግኘት ሲሉ በ53 ውሃ መገኛ ማዕከላት መሰባሰባቸውን ገልጸዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ በአሁኑ ወቅት በማዕከላቱ 250 ሺህ እስር የእንስሳት መኖ በመከፋፈል ላይ ነው።

“ድርቁ ለቀጣይ ወራት እንደሚቀጥል የትንባያ መረጃዎችን ያስረዳሉ ያሉት” ኃላፊው፣ ከፌዴራል መንግስትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርቁን ለመከላከል የክልሉ መንግስት 200 ሚሊዮን፣ የፌዴራል መንግስት 100 ሚሊዮን ብር በጀት መመደባቸውንም አመልክተዋል።

የቢርቆድ ወረዳ ሆሳለ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በሼር መሀሙድ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ያለው ድርቅ የከፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“በድርቁ ምክንያት ከነበሩኝ 33 ከብቶች መካከል 24ቱ በመኖ እጥረት ምክንያት መንቀሳቀስ አቅቷቸው ነበር፤ ይሁንና መንግስት በአቅራቢያችን የጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በማዘጋጀቱና ለእንስሳት መኖ ማቅረብ በመጀመሩ እንስሳቱ አገግመዋል" ብለዋል፡፡

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ አብዲራን ሂርስ  በበኩላቸው “መንግስት ለእንስሳት መኖ፤ ለእኛም አልሚ ምግብ፣ ሩዝና ስጋ እያቀረበልን በመሆኑ የድርቁን አደጋ ለመቋቋም ችለናል” ብለዋል

ለድርቅ ለተጋለጡ አርሶአደሮች እየቀረበ ያለው የእንስሳት መኖና መድኃኒት ከእንስሳቱ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ አቅርቦቱ እንዲሻሻል የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

በጀረር ዞን ደሮር ወረዳ ዱንዱመአድ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርብቶአደር ከደር አብዲ በበኩላቸው ድርቁ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ በአካባቢያቸው መከሰቱን ገልጸዋል።

ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወራት በአካባቢው ይጠበቅ የነበረው የ"ዳይር" ወቅት ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ለሰውና እንስሳት የመጠጥ ውሃ እጥረት መከሰቱን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ካለው ከቢርቆድ ወንዝ ውሃ በመቅዳት በየቀኑ እያቀረበላቸው መሆኑን የተናገሩት አርብቶ አደሩ በዚህም የነበረባቸው የውሃ ችግር እንደተቃለለላቸው ገልጸዋል፡፡

"የእንስሳዎቻችን በሽታ የመቋቋም አቅም እየተዳከመና ከዚህ በፊት የማናውቃቸው በሽታዎች በእንስሳቱ ላይ እየተመለከትኩ ነው፤ይህም ስጋት ፈጥሮብኛልበማለት መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ