አርዕስተ ዜና

የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የጥናት ሰነዶች ይዘት ላይ የጥራት መጓደል ችግር ይስተዋላል

11 Feb 2017
988 times

አዲስ አበባ የካቲት 3/2009 በአንዳንድ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የጥናት ሰነዶች ይዘት ላይ የጥራት መጓደል ችግር መኖሩንና የሚሰጠውም ትኩረት ዝቅተኛ እንደሆነ አንድ ጥናት አመለከተ።

የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አማካሪ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ጋር በግምገማ ሰነዶቹ ይዘት ላይ መክሯል።

ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ አቶ ያለምሰው አዴላ በአንዳንድ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰነዶች ይዘት ላይ የጥራት መጓደል ችግር መኖሩን ገልጸዋል።

የይለፍ ይሁንታ ባገኙ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰነዶች ላይ በተደረገ የቴክኒካዊ ይዘት ዳሰሳ ጥናት ለማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ የተሰጠው ትኩረት እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ አሳይቷል ብለዋል።

በጥናታዊ ሰነዶቹ ለማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ከተጠቀሱ መሰረታዊ ኩነቶች 50 በመቶና ከዚያ በላይ መዳሰስ አለመቻላቸው ለግምገማው የተሰጠውን ትኩረት ዝቅተኝነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

ጥናቱ አማካሪ ድርጅቶች እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎችን ይዘው የአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ይሁንታ ፈቃድ እንደሚሠጡም ጠቁሟል።

ህብረተሰቡን ያላሳተፉና ትርጉም የሌላቸው ፎቶግራፎችን በሰነዶች ውስጥ እንደ ማስዋቢያ የመጠቀም ዝንባሌ በጥናታዊ ሰነዶቹ  ላይ እንደተስተዋለም አመልክቷል።

አብዛኛዎቹ ጥናታዊ ሰነዶች የገጾቻቸውን ቁጥር ማብዛት ላይ መጠመድና እንደ ማጠቃለያ “የተገለጸው ፕሮጀክት ይሄ ነው የሚባል ተጽዕኖ የለውም” የሚል ዓረፍተ ነገር መጠቀም እንደሚመርጡም ተስተውሏል።

አብዛኛውን ጊዜ ዲፕሎማቲክ ቃላቶችን ከሳይንሳዊ ቃላቶች በበለጠ መልኩ የመጠቀም ሁኔታዎች እንደታዩም በጥናቱ ተጠቅሷል።

"በአካባቢና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ልዩ ትኩረት ቢደረግ፣ ለአማካሪዎች ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ቁጥጥር ቢካሄድ" የሚሉ ሃሳቦች ከመድረክ ተነስተዋል።

ውክልና በተሰጠው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የባለሙያ ቅጥር እንዲያካሄድ ማድረግ ቢቻል፤ ወይም ውክልናው በተደራጀ መልኩ ማዕከላዊ ዳይሬክቶሬት በማቋቋም ቢሠራ የተሻለ ይሆናል የሚሉ ምክረ ሃሳቦችም ቀርበዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ችግሩን ለማስወገድ ሙያዊ ስነ ምግባር በተላበሰ መልኩ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በየዘርፉ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች የአካባቢ ብክለትና ብክነት ሳያስከትሉና በማህበረሰብ ደህንነት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በማስወገድ  ዘላቂነት ባለው አግባብ ሊፈፀሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ራዕይን እውን ለማድረግ ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ