አርዕስተ ዜና

የእምቦጭ አረም ወደ ጫሞ ሐይቅ እንዳይዛመት መከላከል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል-የዘርፉ ባለሙያዎች

988 times

አርባምንጭ የካቲት29/2010 በአባያ ሐይቅ የተከሰተው የእምቦጭ አረም ወደ ጫሞ ሐይቅ እንዳይዛመት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ስራ ሊሰራ እንደሚገባ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አሳሰበ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስምኦን ሽብሩ እንደገለፁት የጫሞ ሐይቅን ከአረሙ ለመከላከል በአባያ ሐይቅ ላይ የተከሰተውን አረም የማስወገድ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ።

"በአባያ ሀይቅ ላይ የተከሰተው የእመቦጭ አረም በሂደት ወደ ጫሞ ሀይቅ የማይዛመትበት ምክንያት አይኖርም " ያሉት ዶክተር ስምኦን አረሙ ሳይዛመት ከወዲሁ በህዝብ ተሳትፎ የማሶገድ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

እንደ ዶክተር ስምኦን ገለጻ  አረሙን በሳይንሳዊ መንገድ ለማሶገድ የሚቻልበትን መንገድ ለማፈላለግ ዩኒቨርሲቲው ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው።

የጋሞ ጎፋ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ኩማ እንደተናገሩት በአባያ ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም በጫሞ ሐይቅ ላይ እስካሁን አልተከሰተም፡፡

ሁለቱ ሐይቆች በመካከላቸው ባለው የእግዜር ድልድይ ምክንያት የማይገናኙ ቢሆንም በክረምት ወራት በገባር ወንዞች ውሃ ሙላት በመካከላቸው የውሃ መጋራት መኖሩን ተናግረዋል።

በሀይቁ ውስጥና አካባቢ ያሉ አዞዎች፣ ዘንዶና ሌሎች አደገኛ እንስሳት በሰው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ በአባያ ሀይቅ ላይ የተከሰተውን እንቦጭ አረም በህብረተሰብ ተሳትፎ ለማሶገድ አለመቻሉ ሌላው ስጋት መሆኑን ጠቁመዋል ።

በአሁን ሰአት ስጋቱን በመቋቋም አረሙን ለማሶገድ በሚቻልበት መንገድ ላይ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የገለፁት አቶ ዮሴፍ ለጊዜው አረሙ ወደ ጫሞ ሀይቅ እንዳይዛመት በሀይቁ አካባቢ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የእንቦጭ አረም በአባያ ሀይቅ በ180 ሄክታር ስፋት ላይ መከሰቱ  ይታወሳል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን