አርዕስተ ዜና

በምስራቅ ጎጃም ዞን የበጋ ተፋሰሶች ስራ በተሰራባቸው 110 ሺህ ሄክታር መሬት የሚተከል ችግኝ እየተዘጋጀ ነው

1029 times

ደብረ ማርቆስ የካቲት 29/2010 በምስራቅ ጎጃም ዞን በበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በተከናወነባቸው ተፋሰሶች የሚተከል ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ አቶ ጤናው አላምረው ለኢዜአ እንደተናገሩት በመጪው ክረምት በዞኑ ከ316 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም በ48 ሺህ የመንግስት፣ የማህበራትና የግል ጣቢያዎች ችግኝ የማፍላት ስራ በመሰራት ላይ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

በችግኝ ዝግጅቱ ከአንድ ሺህ 900 በላይ ሰዎች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ እስካሁንም ቀደም ብሎ የተዘራና ለቆጠራ የደረሰ ከ40 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱ በቆጠራ ተረጋግጧል። 

ከተዘጋጀው ችግኝ ውስጥ ግራልቪያ፣ ሰስፓኒያ፣ ዲከረንስ፣ ሰሳ፣ ብሳና፣ ግራር፣ ዋርካ ጽድ፣ በሃርዛፍ፣ ጌሾ፣ ኮሽም፣ ወይራና መሰል የደን ዛፍ ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡

ችግኙ በበጋው ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በተከናወኑባቸው ተፋሰሶች በሚገኝ 110 ሺህ ሄክታር የግል፣ የወልና የተቋማት መሬት ላይ እንደሚተከል ተናግረዋል፡፡

የደጀን ወረዳ  የገልገሌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ያለው አምጤ በሰጡት አስተያየት በማሳቸው ጌሾ፣ የእንስሳት መኖና የዛፍ ችግኝ በመትከል ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በዚህ አመትም ከ500 በላይ የጌሾ ችግኝ እያፈሉ መሆኑን ጠቁመው ችግኙ በመጭው ክረምት በማሳቸው ለመትከልና ለሽያጭ ጭምር እንደሚጠቀሙበት አመልክተዋል።

የዚሁ ወረዳ የቆቅ ውሃ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አባቴነህ ሙሉ እንዳለው በማህበር ተደራጅተው የሀገር በቀል ችግኝ እያፈሉ በአመት ከ15 እስከ 20 ሺህ ብር እንደሚያገኙ ገልጿል።

በዚህ አመትም ከ18 ሺህ በላይ ችግኝ ለተከላና ለሽያጭ ማፍላታቸውን ገልጿል፡፡

ለቀጣይ አመት ደግሞ ሽፈራው የሚባለውን ችግኝ ለማፍላት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል።

በዞኑ ባለፈው የክረምት ወቅት በ100 ሄክታር መሬት ከተተከለው 290 ሚሊዮን ችግኝ በማህበረሰቡ በተደረገለት እንክብካቤና ጥበቃ ከ75 በመቶ በላይ መጽደቁ ታውቋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን