በከተማው ቅዝቃዜ እየጨመረ መምጣት በ441 የውሃ ቆጣሪዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

11 Jan 2017
1172 times

ደብረ ብርሃን ጥር 3/2009 በደብረ ብርሀን ከተማ የሌሊቱ ቅዝቃዜ እየጨመረ መምጣት በውሃ ቆጣሪያቸው ላይ ጉዳት በማድረስ ለወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ።

የከተማው አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ 441 የውሃ ቆጣሪዎች መስታወታቸው መሰበሩን አመልክቷል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ ደጀኔ ፈንቅሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በከተማው በተለያዩ ጊዜያት ቅዝቃዜ የሚከሰት ቢሆንም ዘንድሮ ከምሽት እስከ ማለዳ የተከሰተው ቅዝቃዜ ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ እየበረታ በመጣው ቅዝቃዜ በጓሮ አትክልት ያለሙት 12 እግር የአፕልና የወይን ተክል ሙሉ በሙሉ በውርጭ መመታቱን ገልጸዋል።

የውሃ ቆጣሪያቸው በቅዝቃዜው በመፈንዳቱ  የውሃ አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ደጀኔ፣ በከተማው ውሃና ፍሳሽ መፍትሄ እስኪያገኙ ድረስ ውሃ ከሌላ ቦታ እያስቀዱ መሆኑንና ይህም ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረጋቸው ጠቁመዋል።

የቀበሌ 09 ነዋሪ ወይዘሮ ኤልሳቤት ጥሩነህ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ልጆቻቸውን ከማለዳው አንድ ሰዓት ተኩል ወደትምህርት ቤት ይልኩ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በቅዝቃዜው ምክንያት እስከ ሁለት ሰዓት በቤት ወስጥ ለማቆየት መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

በቅዝቃዜው ምክንያት የውሃ ቆጣሪያቸው ላይ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ወይዘሮ ኤልሳቤት፣ በየጊዜው የቅዝቃዜው መበርታት በአካባቢያቸው የሌሎች ሰዎች ቆጣሪዎችን እያፈነዳ መሆኑን አመልክተዋል። 

በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ምዕራፍ አብይ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በከተማው በተከሰተው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ እስከ ዛሬ ማለዳ ድረስ 441 የውሃ ቆጣሪዎች መስታወታቸው ተሰብሯል።

በዚህም ምክንያት የጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎች በዕየለቱ ከሕብረተሰቡ የሚመጡትን ችግሮች ለመፍታት በጥገና ሥራ መጠመዳቸውን ተናግረዋል።

ዛሬ ማለዳም "ዳለቻ" እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የጥልቅ ጉድጓድ ጌት ቫልቩ ላይ በቅዝቃዜው ምክንያት ስብራት በመድረሱም ከሌሊት ጀምሮ የውሃ ስርጭት መቋረጡን አስታውቀዋል።

ዘንድሮ የተከሰተው ቅዝቃዜ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ የውሃ ደንበኞች ቆጣሪያቸውን ሙቀት በሚስቡ ቁሶች በመሸፈንና በማለዳ ቆጣሪ ባለመክፈት ችግሩን መከላከል እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ባለሙያ ወይዘሮ አስቴር በረሄ በበኩላቸው በደጋማ ወረዳዎች በበጋ ወራት ፈጥነው የሚደርሱ እንደ ድንችና መሰል ያሉ ሰብሎች እንዳይዘሩ ቅዝቃዜው እንቅፋት መፍጠሩን አስታውቀዋል። 

በምስራቅ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የደብረብርሃን ጣቢያ ሠራተኛ አቶ ኃይለገብረኤል ሙሉጌታ በበኩላቸው ፣ ከዚህ ቀደም በ1991 ዓ.ም ከዜሮ በታች ስምንት ዲግሪ ሴልሺየስ ከዚያ ወዲህም ለአንድ ቀን 7 ነጥብ 8 ዲግሪ ሴልሺየስ የቅዝቃዜ መጠን ተመዝግቦ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዘንድሮው ዓማት በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ ስምንት ዲግሪ ሴልሺየስ የቅዝቃዜ መጠን ቢመዘገብም ለተከታታይ ሃያ ቀናት መቆየቱ ለየት እንደሚያደርገው አስረድተዋል።  

ከምሽት እስከ ማለዳ ያለው ቅዝቃዜ ቀጣይነት ሊኖረው ስለሚችል የከተማው ነዋሪዎች አለባበሳቸውን እንዲያስተካክሉ መክረዋል።

የቤት ውስጥ እንስሳትን ማታ በጊዜ በማስገባትና ጠዋትም ፀሐይ ሞቅ እስኪል ድረስ በቤት ውስጥ በማቆየት ጉዳቱን መከላከል እንዳለባቸው አቶ ኃይለገብረኤል አሳስበዋል ።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ