አርዕስተ ዜና

በዞኑ ለ45 ቀን የሚቆይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ተጀመረ

10 Jan 2017
919 times

ደብረ ማርቆስ አምቦ ጥር 2/2009 በምስራቅ ጎጃም ዞን ለመጪዎቹ 45 ቀናት የሚቆይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ትናንት ተጀመረ።

በምዕራብ ሸዋ ዞንም ከፊታቸው ጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የተፋሰስ ልማት ሥራ ይጀመራል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን አቢታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው 800 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ በ280 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄድ ነው ።

በልማት ሥራውም ከ628 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዞን ደረጃ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራውን በደባይጥላንግን ወረዳ እንቆይ ቀበሌ በተዘጋጀ ሥነ ስርአት ላይ ትናንት ተገኝተው በይፋ ያስጀመሩት የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው።

አስተዳዳሪው በወቅቱ እንዳሉት፣ ዘንድሮ የሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከዚህ ቀደም ከተከናወነው በበለጠ ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ትኩረት ያደረገ ነው።

ከተፋሰስ ልማት ሥራው ጎን ለጎን አርሶአደሩን፣ ወጣቶችንና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማደራጀት በእንስሳት፣ በንብ ማነብና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እዲሰማሩ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል ።

በተለይም እንደ ጌሾ፣ አፕልና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ተክሎችን በዘላቂነት ለማልማት መሰረት የሚጣልበት ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዞኑ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ ታለቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ግድቡን ታሳቢ ያደረገ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት በዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ከተካሄደበት 350 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከ69 ሺህ ሄክታር በላይ በተለያዩ የዛፍ ችግኞች መሸፈኑ ታውቋል።

በዞኑ ባለፉት አምስት ዓመታት በተካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ የደን ሽፋን ከ3 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 16 በመቶ ማደጉ ተመልክቷል ።

በተመሳሳይ ዜና በምዕራብ ሸዋ ዞን ከፊታችን ጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከ262 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ሥራ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተሾመ ጉታ እንደገለጹት፣ የተፋሰስ ልማት ሥራውን በግንባር ቀደምትነት ለሚመሩ አራት ሺህ 725 አርሶ አደሮች በእርከን፣ ክትርና ውሃ ማስረጊያ ሥራዎች ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ።

በተፋሰስ ልማት ሥራው 541 ሺህ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም ጠቅሰዋል ።

ለአንድ ወር በሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ሥራ 124 ሺህ 426 ኪሎ ሜትር  እርከን ጨምሮ የክትር፣ የውሃ ማስረጊያ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ ቦረቦር መሬቶችን የመታደግና መሰል ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።

በዞኑ ባለፉት አምስት ዓመታት በ761 ሺህ 812 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ የተከናወነ ሲሆን በ200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተተከለ የግጦሽ ሣርም ለከብቶች መኖነት መዋሉን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ