የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በሃገሪቱ ለተመዘገበው የምርት እድገት አስተዋጽኦ አድርጓል - ዶክተር እያሱ አብረሃ Featured

10 Jan 2017
1396 times

ባህር ዳር ጥር 2/2009 ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በሃገሪቱ ለተመዘገበው የምርት እድገትና የመስኖ ልማት መስፋፋት የላቀ አስተዋጽኦ ማድረጉን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብረሃ አስታወቁ።

የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ጥራትን፣ ዘላቂነትንና የህዝብ ተጠቃሚነትን መሰረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገልፀዋል።

የዘንድሮው  የአገር አቀፍና የአማራ ክልል የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ትናንት ተጀምሯል።

ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብረሃ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ጠንካራና የማይፈርስ የልማት ሰራዊት ከተገነባባቸው ዘርፎች መካከል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ዋነኛው ነው።

በተገነባው ሰራዊትም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 50 ሺህ ተፋሰሶችን በጥናት በመለየት የተለያየ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ገልፀዋል።

እንዲሁም 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ በመከለል የመጠበቅና 24 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ደግሞ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን መልሶ እንዲያገግምና ለልማት እንዲውል ተደርጓል ብለዋል።

''በተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራም የመሬቱን ለምነት በመጠበቅ በሃገሪቱ ለተመዘገበው ከፍተኛ የምርት እድገትና የውሃ አማራጮችን በማሳደግ የመስኖ ልማት መስፋፋት ጉልህ ሚና አበርክቷል'' ብለዋል።

በአያያዝና በአጠቃቀም ጉድለት ተመናምኖ የነበረው የደን ሽፋንም ተመልሶ አረንጓዴ እንዲለብስ በማድረግ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን አብራርተዋል።

ይህም ሃገሪቱ በግብርናው ዘርፍ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ያስቀመጠችውን ዘርፈ ብዙ የእድገት ግብ ውጤታማ እንዲሆን እያገዘ መሆኑን ዶክተር እያሱ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራም ሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዚህ ዓመት የልማት ስራም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በተገነባው ጠንካራ የልማት ስራዊት ግቡን ይመታል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው የበጋ ወቅት በህዝብ ንቅናቄ የሚከናወነው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ጥራትንና ዘላቂነትን መሰርት ተደርጎ ይከናወናል።

እንዲሁም ህዝቡ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬና መሰል የገቢ ምንጭ በሆኑ ዘርፎች በልፋቱና በድካሙ ልክ ቀጥተኛ ተጠቀሚ የሚሆንበትን መንገድ በማመቻቸት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው ህዝቡ ተጎትቶ የሚሰራው ሳይሆን ወዶና ፈቅዶ በሙሉ ፍላጎቱ የሚያከናውነው ዋነኛ ተግባሩ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ግድቦችን ከደለል ስጋት ለመጠበቅ ጭምር የሚከናወን በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር የዚህ ዓመት የተፈጥሮ የልማት ስራ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

ህብረተሰቡም ለጉልበቱ ሳይሰስት በላቀ ትጋትና ህዝባዊነት መንፈስ መስራት እንዳለበት አቶ ገዱ አሳስበዋል።

በአማራ ክልል በ6 ሺህ ተፋሰሶች አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በሚሸፍን መሬት የልማት ስራው መጀመሩን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ተሾመ ዋለ ናቸው።

ከ20 ቀናት በላይ ለሚቆየው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በቀጥታ እንደሚሳተፍ ኃላፊው ገልፀዋል።

ለልማት ስራው የሚውል መሳሪያ፣ የባለሙያዎችና አርሶ አደሮች በተግባር የተደረገ ስልጠና በመስጠትም ቀደም ብሎ ለልማት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰሜን አቸፈር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አግማስ ባዩ በበኩላቸው ''በዚህ ዓመት በ202 ተፋሰሶች ህዝቡ በሚያበረክተው ነፃ የጉልበት ተሳትፎ የሚካሄደው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተጀምሯል'' ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የልማት ስራም በለሙ ተፋሰሶች ወጣቶችን በማደራጀት በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ በማሰማራት ለ2 ሺህ 200 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

በዚሁ ወረዳ የፎረን ሳንቅራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተመስገን ዘውዱ በበኩላቸው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመስራታቸው ለም አፈሩን በማስቀረት ለሰብል ምርታማነት አስተዋጽኦ አንዳደረገላቸው ተናግረዋል።

ወይዘሮ ደቋናየ ወርቁ በበኩላቸው የአፈርና ውሃ ስራ በመስራታቸው በአካባቢያቸው በየክረምት ወቅቱ ይከሰት የነበረው ከፍተኛ ጎርፍ መቀነስ መቻሉን አስታውቀዋል።

የዚህ ዓመት የአገር አቀፍና የአማራ ክልል የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እንቅስቃሴ በሰሜን አቸፈር ወረዳ ይስማላ ጃንኪት ቀበሌ በተጀመረበት ስነስርዓት ላይ የፌደራል፣ የአማራ ክልል፤ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ