አርዕስተ ዜና

በዞኑ በ178 ተፋሰሶች ውስጥ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ

1109 times

ማይጨው የካቲት 28/2010 በ178  በተፋሰሶች ውስጥ አርሶ አደሩን ያሳተፈ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት እየተካሄደ መሆኑን የትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ገለጸ፡፡

በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አቻምየለህ አሰፋ ለኢዜአ  እንደተናገሩት በተፋሰሶቹ ውስጥ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት እየተካሄደ ያለው በዞኑ አምስት ወረዳዎች በሚገኙ 93 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው።

በቀበሌዎቹ  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ 178 ከፍተኛ ተፋሰሶች ውስጥ  የአፈርና የድንጋይ እርከን ግንባታ 20 ሺህ በሚጠጋ ሄክታር መሬት ላይ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮ ስራ ካለፈው የሚለየው የዞኑ አርሶ አደር ከተፈጥሮ ሃብት የሚያገኘውን ጥቅም የሚያሳድጉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ቴክኖሎጂ  ልማት  ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ነው ብለዋል።

ከዚህም ውስጥ በ5 ተፋሰሶች የዝናብ ውሃ  ወደ መሬት በማስረግ ለማቀብ  የከርሰ ምድር ውሃን የሚያጎለብቱ  የጎርፍ አልባ  እርከን ቴክኖሎጂ የሙከራ ፕሮጀክት የማልማት ስራዎች ይገኙበታል፡፡

በተቀሩት 173  ተፋሰሶች ደግሞ የአካባቢው ወጣቶችን ቋሚ ተክሎችን በማልማት ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው የጠረጰዛ እርከን ስራ የተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስራውን በጥራት ለማከናወንም 3 ሺህ የኤክስቴንሽንና የቅየሳ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ16 ሺህ ለሚበልጡ  የልማት ቡድኖች አስተባባሪዎች አስቀድሞ ስልጠና ተሰጥቷል።

በአፈርና ውሃ ጥበቃው ልማቱ  220 ሺህ የሚጠጉ አርሶአደሮች በነፃ የጉልበት ስራ እየተሳተፉ ነው ተብሏል፡፡

የአምባላጌ ወረዳ ወጣት አርሶ አደር ግርማይ ህሉፍ  በሰጠው አስተያየት ቀደም ሲል በተከናወኑ የጥበቃ ልማት ስራዎች በማህበር ተደራጅተው ቋሚ ተክሎችን በማልማትና ሳር አጭደው ለእንስሳት መኖ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃው በተራራማ አካባቢ የአፈር መከላትን በማስወገድ የእርሻ መሬት ከደለል እየተከላከለ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የራያ አዘቦ ወረዳ አርሶ አደር ሉባባ ዋዩ ናቸው፡፡

የአፍላ ወረዳ  አርሶአደር አሰፋ አባዲ  በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ጠፍተው የነበሩ  ምንጮችን በማጎልበት የመስኖ ልማት ተጠቃሚ  እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡    

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን