አርዕስተ ዜና

በመጪው ጥር ወር የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለእርሻ ስራ አመቺ መሆኑ ተገለጸ Featured

04 Jan 2017
939 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2009 በመጪው ጥር ወር የሚኖረው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ሰብል ለመሰብሰብ አመቺ መሆኑን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ።

በአንጻሩ የአየር ሁኔታው ዕድገታቸውን ላልጨረሱ ቋሚ ሰብሎችና ለእንስሳት የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

ኤጀንሲው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው የአየር ትንበያ መግለጫ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ደረቅ፣ ፀሃያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚስተዋል ሲሆን ይህን ተከትሎም በአንዳንድ ደጋማ ስፍራዎች የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች ሆኖ ይቀጥላል።

ከዚህ በተቃራኒ በወሩ አጋማሽ በኦሮሚያ፣ ደቡብና ምስራቅ አማራ የተወሰኑ አካባቢዎች አነስተኛ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ትንበያው አመልክቷል።

ደረቃማው የአየር ሁኔታ ለሰብልና ድህረ-ሰብል ስብሰባ አመቺ ሁኔታ ሲኖረው የእንስሳት የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ጠቁሟል።

በመሆኑም በደጋማ አካባቢዎች አርሶአደሩ የአፈር ሙቀት የሚጨምሩ ተግባራትን ማከናወንና እንስሳትም በሌሊቱና በማለዳው ቅዝቃዜ እንዳይጎዱ ከበረታቸው አርፍደው እንዲወጡና ቀድመው እንዲገቡ ማድረግ ይገባል ብሏል።

መለስተኛ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች ደግሞ በሚሰበሰቡ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባና፤ በበልግ ወቅትም የማሳ ዝግጅት ለማድረግ የአየሩን አመቺነት በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ኤጀንሲው በመግለጫው አስፍሯል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ