አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 09 July 2017

መቀሌ ሀምሌ 2/2009 በመቀሌ የተገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ  በሚፈጥረው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው የሚጠብቁ መሆናቸውን በከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

ወጣቶቹ እንዳሉት የፓርኩ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ በሀገራቸው  ሰርተው  ለመለወጥ ያላቸውን ተስፋ  አለምልሞታል፡፡ ወደ ተግባራዊ ስራ ሲሸጋገር  በተለያየ ሙያ ሰልጥነው መሳተፍ ይፈልጋሉ፡፡

ወጣት ገብረሚካኤል ሕሉፍ የኢንዱስቱሪ ፓርክ በተገነባበት አካባቢ ተወልዶ ያደገ መሆኑን ገልጾ  መጀመሪያ የእርሻ መሬታቸው ተወስዶ ለፓርኩ አገልግሎት ሲውል ቅሬታ ተሰምቶት እንደነበር ተናግሯል፡፡

ሆኖም የኋላ ኋላ ጠቀሜታውን በመገንዘብ ቅሬታውን ማንሳቱንና በፓርኩ ግንባታ ሂደት  በልስን ሙያ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሷል፡፡

ፓርኩ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ   በሚፈጥረው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው  በመተማመን ከስደት ይልቅ በሀገራቸው  ሰርተው  ለመለወጥ ያላቸውን ተስፋ  እንዳለመለመው ወጣት ገብረሚካኤል ገልጿል፡፡

ወጣት ዮሐንስ ገብሬ በበኩሉ በኢንዱስቱሪ ፓርኩ በኤሌክትሪክ ሙያ ተቀጥሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጾ " ፓርኩ ወጣቶች ስራ አጥተው ተቀምጠው ከመዋል ይልቅ ሰርተው ለመለወጥ የሚያስችል እድል ይዞ መጥቷል"ብለዋል፡፡፡

" ሀገራችንን በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ማዕከል ለማድረግ የቀየስነው የኢንዱስቱሪ ልማት ስትራቴጂ በትክክለኛ መስመር ላይ እየተጓዘች ስለ መሆኑ በሙሉ እምነት ማናገር ይቻላል" ያሉት ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኩን የመረቁት  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ናቸው፡፡

ኢንዱስቱሪ ፓርኩ በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች  የንግድ ፣ ሆቴሎች ፣መኖሪያ ቤቶች ስራና ሌሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በመጥቀስ በተለይም መሬታቸው ለልማት የሰጡ አርሶ አደሮች ልዩ ትኩረት እንዲጣቸው አሳስበዋል፡፡

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ  መስተዳደር ዶክተር አዲስ አለም ባሌማ በበኩላቸው ፓርኩ ውስጥና ከፓርኩ ተያያዥ በሆኑ ስራዎች ሙያቸውና ገንዘባቸው በማፍሰስ ራሳቸውና ሀገራቸው ተጠቃሚ ለማድረግ ፍቃደኛ የሆኑ ዜጎች እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

" በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገቡ የውጭ ባለሀብቶች  ስንጋብዝ አሁን ለተመረቀው  የኢንዱስቱሪ ፓርክ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ለሚስፋፋው ጭምር ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር  አቶ ሲሳይ ገመቹ ናቸው፡:

በአንድ መቶ ሚልዮን ዶላት ወጪ የተገነባ የመቀሌ ኢንዱስቱሪ ፓርክ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ መመረቁን ቀደም ሲል ተገልጿል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ሀምሌ 2/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማት ዙሪያ ዛሬ ተወያዩ፡፡

ባለሀብቶች ፣ ወጣቶች፣  ሴቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት በዚሁ ውይይት ወቅት የተለያዩ የልማት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

የፌደራል መንግስት የመቀሌን  የመጠጥ ውሃና በክልሉ የመስኖ ልማት እጥረት ችግር እንዲፈታላቸው ከህብረተሰቡ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ይገኝበታል፡፡

የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የሚያስፈለገውን ገንዘብ  በፍጥነት የሚገኝበት ሁኔታ ለማመቻቸት እንዲሁም ሌሎችንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ  ጥረት እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጽ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2009 በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በኩል የተሻለ ሥራ መስራቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ።

በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከትና ብጥብጥ ለማረጋጋት እንዲሁም በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች መፍትሄ በመስጠት በኩል የተሻለ ስራ መከናወኑን አባላቱ አንስተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሀዋ ዓሊ እንደሚሉት፤ በዓመቱ መጀመሪያ ከተካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በኋላ ህጎችን በማውጣት፣ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የተሻሉ ስራዎች ተሰርተዋል።

በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት በየአካባቢው ተገኝተው የመስክ ምልከታ ማድረጋቸውንም ነው ወይዘሮ ሀዋ የገለፁት።

ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ተዋበች አስፋው ደግሞ በ2009 በጀት ዓመት ምክር ቤቱ በመልካም አስተዳደርና በትላልቅ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ነው የገለፁት።

አፈጻጸማቸው የተጓተተ ፕሮጀክቶች ላይ ያለውን ችግር በመለየት በተያዘው ጊዜ ወደ ስራ እንዲገቡ ለአስፈጻሚው ድጋፍ መደረጉንና ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ቅድሚያ ሰጥቶ መሰራቱንም ይናገራሉ።

በዓመቱ 46 ያህል ወሳኝ ህጎች ላይ ውይይት መደረጉን የሚያስታውሱት ሌላው የምክር ቤቱ አባል አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በሀብት አጠቃቀም ላይ የተደረገው ክትትልና ቁጥጥር ከወትሮ የተለየ እንደነበር ይናገራሉ።

አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ለምክር ቤቱ በየጊዜው ከሚያቀርቡት ሪፖርት በተጨማሪ በተግባር ያለበትን ሁኔታ መገምገም ላይ ትኩረት እንደተሰጠ የሚናገሩት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ አበራ ቡኖ ናቸው።

ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ሁሴን ዳሪ የምክር ቤቱ አባላት ወደ ተመረጡበት አካባቢ በመሄድ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ጥረት እንደተደረገ ይናገራሉ። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸው ተግባራት በሁሉም ዘርፎች የተሻለና ውጤታማ እንደነበር አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ መግለጻቸው ይታወሳል።

Published in ፖለቲካ

አዳማ  ሀምሌ  2/2009 በምስራቅ ሸዋ ዞን ሁለት ወረዳዎች በመሬት መደርመስና ከባድ ዝናብ ባስከተለው አደጋ ሶስት ሰዎች መሞታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

 የመምሪያው የህዝብ ግንኝነት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት የመሬት መደርመሱ ያጋጠመው በቦራ ወረዳ ሲሆን ከባድ ዝናብ ጉዳት ያደረሰው ደግሞ በፈንታሌ ወረዳ ነው ።

 በቦራ ወረዳ በዳሎሳ መቲ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሰምቦ በተባለ መንደር ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ አሸዋ በማውጣት ላይ በነበሩ 5 ሰዎች ላይ መሬት ተደርምሶ ሁለቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ ሶስቱ ከጉዳቱ በህይወት ተርፈዋል ።

 በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አስከሬንም ለቤተሰቦቻቸው የተሰጠ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

 በተመሳሳይም በፈንታሌ ወረዳ ዳራ ዲማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ላይ ከጧቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ለተከታታይ 5 ሰዓታት በጣለው ከባድ ዝናብ አንድ ቤት በመፍረሱ በውስጡ የነበረች የ30 ዓመት ወጣት ህይወት አልፏል።

 አደጋው በተከሰተበት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን የወጣቷን ህይወት ለማዳን በአቦምሳ መካከለኛ ክሊኒክ የህክምና ድጋፍ  ቢደረግላትም ማትረፍ እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

 በተለይ በክረምት ወራት አሸዋ ለማውጣት የሚደረገው ጥረት ከዝናብ ጋር ተያይዞ መሬቱ በቀላሉ ሊደረመስ ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ አሳስበዋል።

Published in ማህበራዊ

ሀምሌ 2/2009 ቻይና ያለምንም ፖለቲካዊ ተጽእዕኖ የአፍሪካን ልማት እንደምትደግፍ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አስታወቁ፡፡

ፕሬዝዳንት ዢ በጀርመኗ ሀምቡርግ ከተማ በተካሄደው የቡድን 20 አገራት ጉባኤ እንደተናገሩት የአፍካ መልማት የዓለምን ኢኮኖሚ ለማመጣጠንና የጋራ ተጠቃሚነትንም ለማሳደግ ያግዛል፡፡

ቻይና የአህጉሪቱ የረጅም ጊዜ አጋር መሆኗ የተናገሩት ዢ  በቀጣይም የህዝቦቿን የመልማት ምርጫ እንደምታከብር አረጋግጠዋል፡፡

የቡድን 20 አባል ሀገራት በሴቶች መብት፣ በስደት፣ ጤና እንዲሁም በስራ እድልና መሰል ጉዳዮች መምከራቸውን የቻይና ዓለምዓቀፍ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ አስነብቧል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ሀምሌ 2/2009 የጋምቤላ መምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመካከለኛ ደረጃ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለል የጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት ተመለከተ፡፡

ኮሌጁ በተለያዩ  የሙያ ዘርፎች  በመደበኛና በማታው የትምህርት መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 503 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ሰናይ አኩዎር በምርቃው ወቅት እንዳሉት ኮሌጁ ከአሁን በፊት በተለይም የትምሀርትና የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጥን ለክልሉ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡

ኮሌጁ በክልል  በትምህርትና በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥርት ለማቃለል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ተመራቂዎቹ  በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የልማት ስራዎች ጭምር በንቃት በመሳተፍ የክልሉን ህብረተሰብ ከድህነት ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻውን  እንዲወጡም አቶ ሰናይ አሳስበዋል።

የኮሌጁ የምርምርና አካዳሚክ  ምክትል ዲን አቶ ኡቻለ ቻም በበኩላቸው  "ኮሌጁ ለምረቃ ያበቀቸው ተማሪዎች በመምህርነትና በጤና የሙያ ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው " ብለዋል

ከተመራቂዎቹም መካከል አንድ ሺህ 383ቱ በዲፕሎማ መረሃ ግብር ለሶስት ተከታተይ ዓመታት በጤናና በመምህርነት የሙያ መስኮች የሰለጠኑ ናቸው፤ ቀሪዎቹ በሰርትፊኬት ለመጀመሪያ ሳይክል መምህርነት ለአንድ ዓመት ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

በትምህርት ዘርፍ በዲፕሎማ የተመረቁት በቋንቋ፣በተፈጥሮና በህብረተሰብ ሳይንስ   በጤናው ዘርፍ ዲፕሎማ ደግሞ በክሊኒካልና በጤና ቤተ ሙከራ ዘርፍ  የሰለጠኑ ናቸው እንደ ዲኑ ገለጻ፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል 492 ሴቶች ናቸው፡፡

ኮሌጁ በክልሉ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር በማቃለል ረገድ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው "በቀጣይም የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል " ብለዋል አቶ ኡቻላ።

ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል ተማሪ እስማኤል አሰፋ በሰጠው አስተያየት በሰለጠነበት የሙያ መሰክ ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናገሯል።

በሰለጠነበት የሙያ መስክ ጠንክሮ በመስራት እራሱንና አካባቢውን ለመለወጥ እንደሚሰራ የገለጸው ደግሞ ተመራቂ ቾል ኪር ነው።

በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ኮሌጆ የዕለቱን ጨምሮ ለ22ኛ ጊዜ  ባካሄዳቸው  ስልጠናዎች 10 ሺህ 670 የጤናና  የትምህርት ባለሙያዎችን ማስመረቁ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2009 ኅብረተሰቡ በኤሌክትሮኒስ የሚካሄደውን የ'ይሙሉ' ሞባይል ካርድ ግብይት አገልግሎት በተመለከተ በቂ መረጃ እንዳላገኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮ- ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከሎች ገለጹ።

ኢትዮ - ቴሌኮም ለሞባይል ተጠቃሚዎች 'ይሙሉ' የተሰኘ የኤሌክትሮኒክስ ሞባይል ካርድ ሽያጭ ከአራት ወር በፊት መጀመሩን ገልጿል።

የኤሌክትሮኒክስ የካርድ ግብይቱ በኢትዮ- ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከሎች ለማንኛውም ተንቀሳቃሽ ስልክ በሚፈልጉት የገንዘብ መጠን ተሞልቶና በአጭር የፅሑፍ መልዕክት /ኤስ ኤም ኤስ/ አማካኝነት የሚገባ እንደሆነም ተገልጿል።

ኢዜአ ተዘዋውሮ የተመለከታቸውና በአዲስ አበባ የሚገኙ የኢትዮ- ቴሌኮም የሽያጭ ማዕከላት የ'ይሙሉ' ሞባይል ካርድ ግብይት አገልግሎት እየተሰጠ ነው።

የኢትዮ - ቴሌኮም የአራዳ ቅርንጫፍ የሽያጭ ዘርፍ ባለሙያ አቶ ሚካኤል አለማየሁ እንደሚሉት፤ የ'ይሙሉ' ሞባይል ካርድ ሽያጩ ከተጀመረ ወራትን አሳልፏል።

ይሁንና እስካሁን ባለው ሁኔታ ኅብረተሰቡ ስለአልግሎቱ በቂ መረጃ ባለማግኘቱ የሽያጭ አገልግሎቱን መስጠት አለመቻሉን ነው የገለጹት።

በተመሳሳይ የኢትዮ-ቴሌኮም የአዲሱ ገበያ ሽያጭ ማዕከል አገልግሎቱን መስጠት ቢጀምርም ብዙ ሽያጭ አለማከናወኑን የማዕከሉ ተቆጣጣሪ አቶ አስታውሰኝ ጎዳና ተናግረዋል።

የማዕከላቱ ባለሙያዎች እንደሚሉት የ'ይሙሉ' አገልግሎት ስለመጀመሩ ለኅብረተሰቡ የማስተዋወቅ ስራ አልተከናወነም።

የኢትዮ - ቴሌኮም የስድስት ኪሎ የሸያጭ ማዕከል የሂሳብ ባለሙያ አቶ ይሳቅ ገብረማርያምም እንዲሁ በአራት ወራት ውስጥ ወደ 16 ሺ ብር የሚጠጋ ብቻ መሸጣቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮ - ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ ጉዳዩን በተመለከተ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ የሽያጭ አገልግሎቱ በአዲስ አበባ በሚገኙ 70 ቅርንጫፍ ማዕከሎች እየተሰጠ ነው።

በክልሎች ደግሞ በአዋሳ፣ ባህር ዳርና መቀሌ የኢትዮ-ቴሌኮም ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የ'ይሙሉ' የኤሌክትሮኒክስ ካርድ ሽያጭ መጀመሩን ገልፀዋል።

ሕብረተሰቡ በስፋት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚከናወን ገልጸው፤ ለአከፋፋዮች ስለ አገልግሎቱ አጠቃቀም የሚሰጥ ስልጠና እንደሚኖር ተናግረዋል።  

የኤሌክትሮኒክስ ሽያጭ አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች  ከአምስት ብር ጀምሮ የሚፈልጉትን  የአየር ሰዓት ለመግዛት እንደሚያስችላቸውም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያብራሩት፡፡

በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርዓት 80 በመቶ የሚሆነው የአገሪቷ የሞባይል ተጠቃሚ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንደተናገሩት፤ የ'ይሙሉ' ሞባይል ካርድ የግብይት ስርዓት ተግባራዊ መሆን ከዚህ በፊት ለሞባይል ካርድ ግዢ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ያስችላል።

የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ፣ ህብረተሰቡ በሚፈልገው የገንዘብ መጠን እንዲጠቀም በማስቻል፣ የሚነሱ የጥራት ችግሮችንም የሚመልስ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም የሚፋቀውና ከተሞላ በኋላ የሚጣለው የሞባይል ካርድ የሚያደርሰውን የአካባቢ ብክለት በመቀነስ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለሞባይል ካርድ ግዢ በዓመት ሰባት ሚሊየን ዶላር እንደምታወጣ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኤሌክትሮኒክስ ካርድ ግብይቱን በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት እና ሕዳሴ ቴሌኮም አማካኝነት የማስፋፋት ስራ ይከናወናል።

አገልግሎቱ 'ኮንቪቫ' ከተባለ የህንድ ኩባንያ በሁለት ሚሊዮን ዶላር የተገዛ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሙከራ ደረጃ እንደነበርም ተጠቅሷል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2009 በአማራ ብሄራዊ ክልል በሚገኙ አምስት ከተሞች የተገነቡና 256 ሺ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ  የሚያደርጉ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ።

 የግንባታ ስራቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት ንጹህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ አጣየና ሸዋ ሮቢት፣ በሰሜን ወሎ ዞን መርሳና ወረኢሉ በኦሮሞ ልዩ ዞን ዋና ከተማ ከሚሴ የሚገኙ ናቸው ።

በምረቃ ስነ ስርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች የተገነቡት የክልሉ መንግስት በመደበው በጀትና የአውሮፓ ህብረት ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን፤ አጠቃላይ ወጪው 250 ሚሊዬን ብር ነው።

ግንባታው በ2003 ዓ.ም መጀመሩንና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበር የተጠቆመ ሲሆን፤  ሆኖም በስራ ተቋራጮች አቅም ማነስና የመስሪያ ማሽኖች በሚፈለጉበት ጊዜ ከውጭ ባለመግባታቸው ሳቢያ ተጨማሪ አምስት ዓመታትን መውሰዱም ተገልጿል።

ግንባታውን በተቀመጠው ጊዜ መሰረት ማከናወን ያልቻሉትን የስራ ተቋራጮች በአዳዲስ ለመተካት ተጨማሪ ጊዜ መውሰዱም ነው የተጠቆመው።

 የውኃና መስኖ ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቶቹ ለ20 ዓመታት ለከተሞቹ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስቸሉ ናቸው።

 ከ20 ዓመታት በኋላ እንደየከተሞቹ የሕዝብ ቁጥር ሁኔታ "የማስፋፊያ ስራ ይደረግላቸዋልም" ብለዋል።

 በቀጣይም የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ግንባታዎቹ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

 የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቶቹ ደረጃቸውን ጠብቀው መሰራታቸውን ጠቅሰው፤ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የተጠናቀቁት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ሕብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቃቸው አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን 75 በመቶ መድረሱን የገለጹት አቶ ገዱ፤ የክልሉን ሕዝብ በሙሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሌሎች የልማት ስራዎች በተለየ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።

 በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደርና  ከውኃና መስኖ ኤሌትሪክ ሚኒስቴር በተጨማሪ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የዘርፉ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2009 ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያደረጉት ሙያዊና የገንዘብ ድጋፍ ወደ ተግባር ተቀይሮ በማየታቸው መደሰታቸውን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሠራተኞች ገለጹ።

ሠራተኞቹ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።

በሶስተኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉብኝት የተሳተፉ የተቋሙ ሠራተኞች ስለግድቡ ቀድሞ ካዩትና ከሰሙት ባሻገር ያለበትን ደረጃ በአካል ተገኝተው በማየታቸው መደሰታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ እንደገለጹት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የሙያና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ግንባታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የመሬትና አለት ጥናትም አከናውነዋል። ይህ ደግሞ በተግባር ተተርጉሞ ማየታቸው አስደስቷቸዋል።

የኢንስቲትዩቱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ መርሻ ግድቡን ለሁለተኛ ጊዜ መጎብኘታቸውን አመልክተው፤ ቀድሞ ካዩት በጣም ብዙ ለውጥ ያለው መሆኑንም ገልፀዋል።

የግደቡን ግንባታ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት ወይዘሮ መሰረት አርጋው፣ ክብነሽ ወልደሚካኤልና መልካምነሽ አደፍርስ ከሰሙት ይልቅ ባዩት ነገር ደስተኞች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

የተቋሙ ሰራተኞች በሁለት ዙር   የሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውንና የ10 ሺ ብር የሎተሪ ትኬትና የግድቡን ቲሸርቶች በመግዛት የግድቡ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ተቋሙ ግድቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ የመሬትና አለት ጥናት ሲያከናውን ስለመቆየቱ የተቋሙ ባለሙያ ኢንጂነር አብርሃም ሙሉነህና አቶ ግርማ አሰሙ ምስክሮች ናቸው።

ሰራተኞቹ በግድቡ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው አማካኝነት ገለፃ ከተደረገላቸው በኋላ የግድቡን ግንባታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ሲያደርጉት የነበረውን  ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት 3 ሺ 750 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩት 10 የኃይል ክፍሎች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።

ከዋናው ግድብ በስተ ምስራቅ ያለው የሳድል ግድብ ግንባታም የመጨረሻ የአርማታ ሙሊት ስራ እየተሰራ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 58 በመቶው መጠናቀቁ ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

የፀዳወረቅ ታደለ (ኢዜአ)

በየዓመቱ ክረምት ሲመጣ ከዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለዕረፍት የተመለሱ፣ በወጣት ማህበራት የታቀፉ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ተሰባስበው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ። ይህ ደግሞ በአገራችን የተለመደ ተግባር ከሆነ ሰነባብቷል።

ወጣቶቹ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ፣ ደም ልገሳ ፣ የአካባቢ ልማትና ችግኝ ተከላ በማካሄድ እንዲሁም የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዙሪያ የተለያዩ አገልግሎቶችን በነፃ ይሰጣሉ። በጎዳና ላይ ላሉ ወጣቶች ምክርና ስልጠና ፣ አረጋዊያንን መርዳት፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ግንዛቤ የመስጠት ተግባራትንም ያከናውናሉ።

የዘንድሮ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት "በተደራጀ የወጣቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ህዳሴያችንን እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ሀሳብ የዝግጅት እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ ቆይተዋል።

ለአብነት በመዲናችን የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት የተደረገውን ዝግጅት መመልከት ይቻላል። ኢዜአ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው በክረምት የሚያስተምሩ ወጣቶች አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታዎች ማመቻቸታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ዳግማዊ ሚኒሊክ የመጀመሪያ ደረጃ ፣ መስከረም አፀደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ እና ምስራቅ ጎህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ነው የገለጹት። በቂ የሆነ የመማሪያ ክፍሎች ማዘጋጀት፣ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ማሟላት በዝግጅት ምዕራፉ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው።

ማስታወቂያ በየቦታው በመለጠፍና በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ተማሪዎችና ወላጆች መረጃው እንዲደርሳቸውና ልጆች ለክረምት ትምህርት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡም እንቅስቃሴዎች ተደርጓል። አቅም ለሌላቸው ልጆች ደግሞ አልባሳትን ጨምሮ የመማሪያ ቁሳቁሶችን በፈቃደኝነት መሰባሰቡንና ለማከፋፈልም ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ነው የነገሩን።

በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከተመዘገቡ ወጣቶች ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣት ንጋቱ ተሻለ አንዱ ነው። ''በየዓመቱ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ነው የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው ዘንድሮም በዚሁ ዓይነት ተግባር በማሳለፍ ተተኪ ትውልዶችን በማብቃት ረገድ የድርሻዬን እወጣለሁ'' ነበር ያለው።

የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ባሉበት በዚህ ወቅትም ተመላሾችን የመቀበልና እነርሱ የሚፈልጉትን አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያግዙበት ሁኔታም በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተካቷል። 

በዚህም ከ500 የሚበልጡ የክረምት ወራት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሳዑዲ ተመላሾችን በመቀበል ላይ ይገኛሉ። ወጣቶቹ በቀንና በማታ መርሃ-ግብር ተከፋፍለው ተመላሾችን በመቀበል፣ የስልክ አገልግሎት በመስጠት፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እስከሚገናኙ የሚያርፉበት መጠለያ በማዘጋጀት፣ ሻንጣዎቻቸውን በማፈላለግና በማገዝ ብሎም የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራን እያከናወኑ ነው።

ያነጋገርናቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለወገኖቻቸው በሚያደርጉት ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት። የእረፍት ጊዚያቸውን በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ይህንን በመሰለ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያሳለፉ በመሆናቸው ለህብረተሰቡ ከሚሰጡት ጠቀሜታ ባሻገር የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ይገልጻሉ።

ወጣት ኪሮስ ኪዳነማርያምና ወጣት ፍሬወይኒ አበባው በግልና በመንግስት ስራ የተሰማሩ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶቹ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘወትር ክረምት በመጣ ቁጥር ተሳታፊ መሆናቸውን ይናገራሉ። ወጣቶቹ ከስራ ሰዓት ውጪ በሚኖራቸው የዕረፍት ጊዜ ከሳዑዲ ተመላሾችን በመቀበል ላይ ናቸው፤ ይሄ ደግሞ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አባል ወጣት ሕብስቱ አራጋውና ወጣት ይመር ተሾመም እንዲሁ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ መሆኑን ይናገራሉ።

ወጣት ይመር ”በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሳዑዲ ተመላሽ ዜጎችን ተቀባይ በመሆኔ የተለየ ስሜት ፈጥሮብኛል፤ መረዳዳታችንንም በግልጽ የሚያሳይ ነው'' ብሏል።

ወጣት ህብስቱም ከወጣት ይመር ጋር ተመሳሳይ ስሜት እንዳሳደረባት ገልፆ ፤ በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ያልሆኑ ወጣቶች የዕረፍት ጊዜያቸውን በጎ ተግባር በማከናወን የህሊና ዕርካታ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርቧል።

ከሳዑዲ ተመላሽ ዜጎችም በወጣቶቹ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። ወጣቶቹ ያለምንም ክፍያ በበጎ ፈቃድ የሚያደርጉላቸው እገዛ በገንዘብ ቢተመን ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ነውም ይላሉ። ከወጪ ባለፈም ያጋጥም የነበረውን እንግልት ማስቀረቱን ይመሰክራሉ። የተመላሾቹን ሻንጣ መፈለግና የጠፋ ካለም የሚመለከተው አካል ጋር በመሄድ መፍትሄ እንዲያገኙ ትብብር ያደርጋሉ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባለፈው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶቹ በበጎ ፈቃድ ያከናወኑት ተግባር በገንዘብ ሲተመን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ነው። በበጎ ፈቃድ የክረምት ትምህርት አገልግሎት ዘርፍ 1 ሺ 375  ወጣቶች ተሳትፈው ፤ 78 ሺ ተማሪዎችን አስተምረዋል። በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ደግሞ 31 ሺ ተማሪዎች ሥልጠና ማግኘታቸውንም ነው መረጃዎቹ የሚገልፁት። 

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን በዘንድሮ ክረምት 900 ሺ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያሳትፋል። የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳት ወጣት አባይነህ አስማረ እንደሚለው፤ በአዲስ አበባ አስተዳደር ወጣቶቹ በክረምቱ በተለያዩ መስኮች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ የሚሰጠው አገልግሎት 50 ሚሊዮን ብር እንደሚገመትም አብራርቷል።

በዚሁ የበጎ ፈቃድ ስራ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣቱ 2 ሺ 200 ተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጡም ነው የተናገረው። በዚህም በከተማዋ በሚገኙ 100 ትምህርት ቤቶች 85 ሺ ለሚደርሱ ተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱንም አብራርቷል።    

በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ 50 ሺ ተማሪዎች ስልጠና እንደሚያገኙ የተናገረው ወጣት አባይነህ፤ አቅም ለሌላቸው 10 ሺ ህጻናትም የመማሪያ ቁሳቁስና አልባሳት ማሟላታቸውንም ገልጿል። 

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ስድስት ሺ ወጣቶች በደም ልገሳ የሚሳተፉ ሲሆን፤ 100 ሺ ወጣቶች ደግሞ 200 ሺ ችግኞችን ይተክላሉ። አንድ ሺ 500 ወጣቶች በማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትና በትራፊክ ደህንነትና በአካባቢ ልማትና ጽዳት ተግባር ተሳትፈው በመዲናዋ በተመረጡ ቦታዎች 35 ሺ ሜትር ኪዩብ ቆሻሻን ያስወግዳሉ። ከ20 ሺ በላይ ወጣቶች ደግሞ ጤናና ሰብዓዊ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

ሦስት መቶ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በዘርፉ ስልጠና እንደሚሰጡ ነው ወጣት አባይነህ የተናገረው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በበኩሉ ዘንድሮ በመላው አገሪቷ ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጿል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በሚፈልጉት መስክ በቀላሉ እንዲሰማሩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግሯል።

የፌዴሬሽኖቹ ፕሬዚዳንቶች ትምህርት ቤቶች ለክረምት ነፃ ትምህርት ተማሪዎችን ከመመዝገብ ጀምሮ እንደተባበሩዋቸው ነው የሚገልጸው። ትብብራቸው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።

በወጣቶቹ የሚሰጠው የክረምት ትምህርት ሐምሌ 03 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ ይጀመራል። ሁሉም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በዚሁ እለት እንደሚጀመሩም ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት "እኛ ወጣቶች የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ለማድረስ በዕውቀታችንና በጉልበታችን እንተጋለን" በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ ይታወሳል።

Published in ዜና-ትንታኔ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ