አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 08 July 2017

 አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2009 በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያዊው ፅጋቡ ገብረ ማርያም ብርቱ ፉክክር እያደረገ ነው።

በ104ኛው የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ከ32 አገራት የተውጣጡ 198 ብስክሌተኞች በመካፈል ላይ ይገኛሉ።

ለባህሪኑ ክለብ 'ባህሪን መርዲያ' የሚወዳደረው ብስክሌተኛ ጽጋቡ ገብረማሪያምም በፉክክሩ ቀጥሏል።

21 ዙር ያለው የቱር ደ ፍራንስ ውድድር በድምሩ 3 ሺህ 540 ኪሎ ሜትር ርቀት ይሸፍናል፤ እስካሁን ሰባት ዙር ውድድሮች ተካሂደዋል።

ጽጋቡም በሰባቱ ዙር ውድድሮች ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን ማጠናቀቅ ችሏል።

14 ኪሎ ሜትር በሸፈነው የመጀመሪያ ውድድር 108ኛ፣ 203 ነጥብ 5 በሸፈነው ውድድር 143ኛ፣ 212 ነጥብ 5 በሸፈነው ውድድር ደግሞ 109ኛ ደረጃን በመያዝ ነው ያጠናቀቀው።

207 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በሸፈነው የአምስተኛው ዙር ውድድር 173ኛ፣ በ160 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር 134ኛ፣ በ216 ኪሎ ሜትር 157ኛ፣ በ213 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር 177ኛ ወጥቷል።

ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሰባት ዙሮች ይቀሩታል።

በውድድሩ እየተሳተፉ ከሚገኙት 198 ብስክሌተኞች መካከል 49ኙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

ብስክሌተኛ ጽጋቡ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የኢጣሊያውን ላምፒሬ ሜርዮ ብስክሌት ክለብ በመወከል መሳተፍ መጀመሩ ይታወቃል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2009 በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር ቀይረው በቂ ዕውቀት እንዲጨብጡ ለመማር ማስተማሩ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ሊሟሉ እንደሚገባ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመራቂዎች ተናግረዋል።

በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ከ124 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የሙያ መስኮች እንደሚመረቁ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ከተቋማቱ መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀን፣ በማታና በርቀት ትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ነገር ግን ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር ቀይረው በቂ ዕውቀት እንዲጨብጡ ለመማር ማስተማሩ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ሊሟሉ እንደሚገባ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመራቂዎች ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቂ ልምድ ያላቸው መምህራን፣ የቤተ ሙከራና የህክምና መሳሪያዎች እጥረት እንዳጋጠሟቸው ነው የተናገሩት።

የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ተመራቂው ዮሴፍ ከተማ በዩኒቨርሲቲው በቂ የመጽሃፍት አቅርቦት መኖሩን ገልጿል።

ይሁን እንጂ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሁፍ ሲሰሩ የአማካሪ መምህራን እጥረት መኖሩንና ይህም ችግር ፈቺ ጥናታዊ ጽሁፎችን በጥራት ማውጣት እንዳይቻል ማድረጉን ተናግሯል።

የጤና ሳይንስ ተመራቂው ከድር አህመድ በበኩሉ "የህክምና መሳሪያዎች በሚፈለገው ልክ ባናገኝም በዩኒቨርሲቲው ቆይታችን በቂ ዕውቀት አግኝተናል" ነው ያለው።

የሲቪል ኢንጂነሪንግ ተመራቂው ሲኖዶስ እሸቴ በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ልምድ ያላቸው መምህራንን ቁጥር መጨመር አለበት ብሏል።

የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተመራቂው ፓውሎስ ስመኘው  ላቦራቶሪ እጥረትና ኮምፒዩተሮችም እንደፈለጉ አለማግኘታቸው በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮባቸዋል፡፡

በ1942 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ 33 ተማሪዎችን ያስመረቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  ዛሬ የምሩቃኑ ቁጥር 10 ሺህ 908 ሆኗል፤ ከእነዚህ መካከልም 211ዱ በዶክትሬት፣ 4 ሺህ 351 በሁለተኛ ዲግሪ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ለምረቃ የበቁ ናቸው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2009 በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ያሉትን እድሎች በመጠቀም የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ማቀዳቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፣ በማታና በርቀት የትምህርት መርኃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 10 ሺህ 908 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ከእነዚህም  211 በሦስተኛ ዲግሪ፣ 4 ሺህ 351 በሁለተኛ ዲግሪና ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመራቂዎች እንደተናገሩት በግልም ሆነ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከመቀጠር ባለፈ በራሳቸው ሥራ ፈጥረው ለመንቀሳቀስ አቅደዋል።

ለዚህም ያሉትን ዕድሎች ለመጠቀምና አስፈላጊ የሚባለውን ግላዊ ዝግጅት ከወዲሁ መጀመራቸውን ነው የተናገሩት።    

በኮምፒዩተር ሳይንስ የተመረቀው አብዲ ጠና በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በኮምፒዩተር ዙሪያ በቂ እውቀትና ክህሎት ማግኘቱን ገልጿል።

የመመረቂያ ጽሁፉን ሰዎች ሞባይልን በመጠቀም ጤናቸውን እንዴት በሳይንስ መደገፍ እንደሚችሉ ማሳየቱንና፤ ይህም ወቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ጥናት እንደሆነ ገልጿል። 

በዘርፉ ያካበተውን እውቀት በመጠቀም በጥቂት ወራት ውስጥ የራሱን ሥራዎች ለመጀመር መዘጋጀቱን ነው የተናገረው።

የስፖርት ሳይንስ ተመራቂው አብዲ ግርማ በበኩሉ ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀል ራሱ በሚከፍተው የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከል ውስጥ ለማድረግ ሁኔታዎችን እያመቻቻ መሆኑን ገልጿል።

ሰዎች የስፖርት እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው የሚከሰቱትን ከልክ ያለፈ ውፍረትና ሌሎች የጤና እክሎች ለመፈወስ የሚያግዘው ስፖርት በመሆኑ ውጤታማ እሆናለው ብሏል።

"በሠለጠንበት የሙያ መስክ ከመቀጠር ይልቅ በራሳችን ሥራ ለመፍጠር እያሰብን ነው" ያለው ደግሞ የሶሻል ወርክ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂው ፍቅሩ ወልዴ ነው።

ለዚህም እሱና ጓደኞቹ አንድም በራስ አቅም አልያም በመንግሥት የተመቻቹ ዕድሎችን በመጠቀም ሥራ ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን ነው የሚናገረው።

ሌላዋ የሶሻል ወርክ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ ራሄል ብርሃኑ በበኩሏ ከምትሰራበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወጥታ በሰለጠነችበት የሙያ መስክ በራሷ ለመሥራት "እቅድ አለኝ" ብላለች።

ይህን ለማድረግ ፍላጎቱ እንዳላትና በሌላ በኩል ደግሞ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ሌሎች ተመራቂዎችን በማስከተል ለመሥራት መወጠኗን ገልጻለች።   

በዚህ ዓመት ከሁሉም የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 124 ሺህ ተማሪዎች እንደሚመረቁ መረጃዎች ያሳያሉ።

Published in ማህበራዊ

ሽሬ እንዳስላሴ ሃምሌ 1/2009 የዲላ ዩኒቨርሲቲ በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን ለሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማጠናከሪያ የሚሆን የ300 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ።

ዩኒቨርሲቲው የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ዴኢህዴን) በተመሰረተበት ሥፍራ ላይ ለመታሰቢያነት ለተሰራው "ጽጌረዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት" ነው።

ዴኢህዴን ከ27 ዓመት በፊት የተመሰረተው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ታህታይ ቆራሮ ወረዳ ልዩ ስሙ “ሽሉም በዓቲ” በተባለ ታሪካዊ አካባቢ መሆኑ ይታወሳል።

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ መምህር ገብረኪዳን በርኽ ለድርጅቱ መታሰቢያነት በተገነባው ትምህርት ቤት የተገኙት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስ ለትምህርት ቤቱ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

ለትምህርት ቤቱ ከተለገሱ የትምህርት ቁሳቁስ መካከል ለስብሰባ፣ ለቤተ መጻህፍትና ለቤተ ሙከራ የሚያገለግሉ 150 ወንበሮች፣ አምስት ኮምፒዩተሮችና 16 ጥቁር ሰሌዳዎች ይገኙባቸዋል።

የመታሰቢያ ትምህርት ቤቱ በትግራይና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ በኩል የጎላ አስዋጽኦ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ተወካይ አቶ ደሳለኝ በየነ ናቸው።

ደኢህዴን አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ የአካባቢው ሕዝብ ላበረከተው አስተዋጽኦ እርዳታው የሚመጥን ባይሆንም በመታሰቢያነቱ ግን ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የመታሰቢያ ትምህርት ቤቱን ለማጠናከር የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም  አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።

ከ12 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው ይህ ትምህርት ቤት የማስተማር ሥራውን በ2009 የትምህርት ዘመን የጀመረ ሲሆን ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ 800 ተማሪዎችንም ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2009 በአዲስ አበባ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በይፋ ወጣ። 

በሰንጋ ተራና በክራውን ሳይቶች የተገነቡት 972 ባለ አራት፣ ባለ ሦስትና ባለሁለት መኝታ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።   

ዕጣው ለተከታታይ 18 ወራት ሳያቋርጡ የቆጠቡና ክፍያቸውን ሙሉ ለሙሉ የፈጸሙ 11 ሺህ 88 ተመዝጋቢዎችን ማዕከል ያደረገ ነው።   

ከእነዚሁ መካከል የመንግስት ሰራተኞች 20 በመቶ እንዲሁም ዳያስፖራዎች ሦስት በመቶ ቅድሚያ ዕድል ተሰጥቷቸዋል፣ ቀሪው ለሌሎች ዕድለኞች ሆኗል። 

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አባተ ስጦታው በዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት በከተማዋ እየተከወነ የሚገኘው የተቀናጀ የልማት ፕሮግራም የህብረተሰቡን የቤት ችግር ከማቃለልና የመዲናዋን ገጽታ ከመገንባት አኳያ ላቅ ያለ ሚና አለው።

በ40/60 ፕሮግራም ከተመዘገቡ 164 ሺህ ቤት ፈላጊዎች መካከል 140 ሺህ የሚሆኑት ቁጠባቸውን በመክፈል ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል። 

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ የ40/60 የልማት ፕሮግራሙ የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ በ372 ህንጻዎች ላይ ከ39 ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው።  

በመሆኑም ተመዝጋቢዎች የቤት ባለቤት መሆን የሚያስችላቸውን ቁጠባ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

የዛሬዎቹ የዕጣ ዕድለኞች አስፈላጊውን ሁኔታ በሟሟላት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቤቶቻቸውን መረከብ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ በበኩላቸው ባንኩ ለሁሉም አይነት የቁጠባ ቤት መርሃ ግብሮች አስፈላጊውን ፋይናንስ በማቅረብ የቤቶች ልማት ዘርፉ ዓላማ እንዲሳካ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል። 

የቤቶቹን ግንባታ አፈጻጸም በቅርበት በመከታተል የሚጠበቀውን የጥራት ደረጃ አሟልተው የተጠናቀቁ 972 ቤቶችን መረከቡንም አክለዋል።

በቤቶች ፕሮግራም አማካኝነት የህብረተሰቡን የቤት ችግር ለመቅረፍና የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠን የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ በኩል ባንኩ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል። 

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ እንዲሁም የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶች የተሟላላቸው መሆኑ ተገልጿል።   

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2009 በመዲናዋ የሚከናወኑ የውበትና መናፈሻ ልማት ሥራዎች ኅብረተሰቡን አሳታፊና ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ገለጹ።

የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች አደባባይ ፓርክ ምረቃ ሥነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

ከንቲባ ድሪባ ኩማና ምክትል ከንቲባ አባተ ስጦታውን ጨምሮ የከተማዋ ከፍተኛ ባለስልጣናት በግንባታ ላይ የሚገኙትን ፓርኮች ተዛዋውረው ተመልክተዋል።

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ፣ የአቃቂና የልደታ ፓርኮች እንዲሁም ከአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ጀርባ የሚገኘው የፓርክ ልማት ፕሮጀክት የግንባታ ሂደታቸውና የደረሱበት ደረጃ ታይቷል።

ከንቲባ ድሪባ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የውበትና መናፈሻ ልማት ሥራዎች ኅብረተሰቡን አሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ናቸው።

በጥቃቅንና አነስተኛ ከተደራጁ ወጣቶች ጀምሮ በሌሎች የእድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች በፓርኮቹ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የኢትዮ - ኩባ ወዳጅነት ፓርክ 27 ሺ 226 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የብሔር ብሔረሰቦች አደባባይ ፓርክ 32 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ሸፍኗል።

ለሁለቱ ፓርኮች ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

የፓርኮቹ ልማት ለመዲናዋ ነዋሪዎችና ለበርካታ "የከተማዋ ወጣቶች የሥራ እድል ያስገኘ በመሆኑ ህብረተሰቡን አሳታፊ የሆነ የልማት ተግባር ነው" ብለዋል።

የከተማዋን የአረጓንዴ ልማት ሽፋን ከማሳደግና ገፅታዋን ከመገንባት አኳያ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውበትና መናፈሻ ልማት ስራዎች በመንግስት አቅም ብቻ የሚከናወኑ አለመሆናቸውን የጠቆሙት ከንቲባው፤ ባለሀብቶችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በአረንጓዴ ልማት ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ውበት፣ መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ግንባታቸው ተጠናቆ የተመረቁትና በሂደት ላይ የሚገኙት ፓርኮች በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጀመሪያ የተጀመሩ ናቸው።

ይሁን እንጂ  በወሰን ማስከበር፣ በመሬት ርክክብና በዲዛይን ላይ በተደረጉ ተደጋጋሚ ለውጦች ፓርኮቹን በታቀደላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻለም።

በአሁኑ ወቅት ደረጃቸውን የጠበቁ የመናፈሻ አገልግሎቶች የሚሰጡ ፓርኮች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ፣ የአቃቂና የልደታ ፓርኮች እንዲሁም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ጀርባ የሚገኘው የፓርክ ልማት ፕሮጀክት በ2010  ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ ወይዘሮ አልማዝ ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበባ ውበት፣ መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሁሉም ወረዳዎች አጎራባች ፓርኮች ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው 16 የመናፈሻ ፓርኮችና 19 ዘላቂ ማረፊያዎችን ያስተዳድራል።

Published in አካባቢ

ወልዲያ ሀምሌ 1/2009 በሰሜን ወሎ ዞን  ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ህብረተሰቡ በማቆያ ቤቶች የምግብና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ፡፡

በበጀት ዓመቱ  39ሺ192 እናቶች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቋማት  በባለሙያ ታግዘው መውለድ ችለዋል፡፡

በመምሪያው የእናቶችና የወጣቶች ጤና ባለሙያ አቶ ጀማል መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት እነዚህ እናቶች የወለዱት በዞኑ በሚገኙ 64 ጤና ጣቢያዎች ነው፡፡

በጤና ጣቢያዎቹ በተለይ ከሩቅ ቀበሌዎች የሚመጡ ነፍሰጡሮች በማቆያ ቤቶች  ቆይተው እንዲወልዱም ህብረተሰቡ 504 ኩንታል እህልና 178ሺ594 ብር በማዋጣት ድጋፍ አድርጓል፡፡

በጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎችና በሴቶች አደረጃጀቶች አማካኝነት ነፍሰጡር እናቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤና ተቋማት እንዲወልዱ በተፈጠረው ግንዛቤ  ህብረተሰቡ   የሚያደርገው ድጋፍ አሁንም እንደቀጠለ ነው ባለሙያው ያመለከቱት፡፡

ይህም ሆኖ በበጀት ዓመቱ በጤና ተቋማት እንዲወልዱ በእቅድ ከተያዘው አንጻር አፈጻጸሙ 70 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የጤና ተቋማት የሴቶችን አደረጃጀት በአግባቡ አለመጠቀምና ነፍሰጡሮች በጤና ተቋም እንዳይወልዱ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ሰዎችን የማሳመኑ ስራ ሁኔታ አለመጠናከር  ለእቅዱ አለመሳካት በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡

እንዲሁም በየወሩ መካሄድ ያለበት የነፍሰጡሮች ኮንፈረንስ ወቅቱን ጠብቆ ተፈጻሚ አለማድረግም ሌላው ክፍተት ነው።

እንደባለሙያው ገለጻ በተጀመረው በጀት ዓመት ክፍተቶችን በማስተካከል ሁሉም ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ በማድረግ  "አንድም እናት በወሊድ ምክንያት አትሞትም"  የሚለውን ግብ ለማሳካት ከወዲሁ ዝግጅት እየተካሄደ ነው ።

በመቄት ወረዳ የደብረ ዘቢጥ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ተስፋዓለም መብራት በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1ሺህ በላይ ነፍሰጡር እናቶች  በጤና ጣቢያው ተስተናግደው መውለዳቸውን ገልጸዋል፡፡

" ይህም ከአምናው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው "ብለዋል ፡፡

ለዚህም  መንግስት ለወረዳው የመደባቸው  ሶስት አምቡላንሶች  በተጠሩበት ቦታ ሁሉ ፈጥነው  ወላዶችን በማምጣት አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረጋቸው ነው ተብሏል፡፡

ወይዘሮ ታምር ከበደ  በወልዲያ ከተማ የዜሮ ስምንት  ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  መንታ ልጆችን በወልዲያ ሆስፒታል በቀዶ ህክምና በሰላም መገላገላቸውን ተናግረዋል፡፡

በጤና ተቋም ባለሙያ ታግዘው መውለዳቸው በራሳቸውም ሆነ በህፃናቱ ህይወት ላይ ሊደርስባቸው ከሚችል ጉዳት መጠበቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በከተማው የዜሮ ሶስት ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ  ተዋበች ተሾመ እንዳሉት በቅርቡ   የመጀመሪያ ልጃቸውን  ሲወልዱ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እስከ እኩለ ቀን ድረስ ምጥ ጠንቶባቸው  ወደ ህክምና ተቋም ሄደው በቀዶ ህክምና በሰላም ተገላግለዋል፡፡

ነፍሰጡሮች ለራሳቸውም ሆነ ለህፃናቱ ጤና ሲሉ ከጤና ተቋም ውጭ ለመውለድ ፈጽሞ እንዳይሞክሩ የራሳቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አምቦ ሃምሌ1/2009 የኦሮሚያ ልማት ማህበር በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ15 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ካስጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የመጠጥ ውሃ ተቋም፣ የወጣቶች መዝናኛና የሙያ ማሰልጠኛ  ማዕከላት ግንባታ ማጠናቀቁን ገለጸ፡፡

በማህበሩ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ መረራ ወርቅነህ ለኢዜአ እንዳሉት  የተጠናቀቁት  ማህበሩ ካለፈው ዓመት ወዲህ ካስጀመራቸው ዘጠኝ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ነው፡፡

በዳንዲ ወረዳ ዩብዶ ለጋ ባቱ ቀበሌ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም በአሁኑ ወቅት  አገልግሎት መስጠት መጀመሩንና 120 የቤተሰብ ኃላፊዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመልክቷል

አራት የወጣቶች መዝናኛና አንድ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሌሎቹ  ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

በዞኑ ድሬ እንጪኒ፣ ጅባት፣ ኖኖና ግንደበረት ወረዳዎች የተገነቡት ማዕከላቱ የሰው ሃይልና የውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት በተጀመረው የበጀት ዓመት ለአገልገሎት ይበቃሉ እንደ አስተባባሪው ገለጻ፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኙት የጊንጪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ስራ፣ የኢለፈታ ወረዳ  የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከልና በጅባት ወረዳ የሸነን ከተማ የውሃ ፕሮጀክት ደግሞ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

እስካሁንም ግንባታቸው ከ60 በመቶ በላይ መከናወናቸውን የጠቀሱት አስተባባሪው የተጠናቀቁትና በሂደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ወጣቶችንና ሌሎች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ  ያደርጋሉ ተብሏል።

እንደ አስተባባሪው ማህበሩ ከአባላት ከሚሰበስበው መዋጮ 90 በመቶ ለአካባቢው ልማት የሚውል ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት በተካሄደው እንቅስቃሴም 232 የልማት ፕሮጀክቶች በመገንባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

የድሬ እንጪኒ ወረዳ ነዋሪ አቶ አበበ ተፈራ በሰጡት አስተያየት  የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል በአካባቢው  መገንባቱ ወጣቱ ከአልባሌ ቦታ ርቆ  የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ ማዕከሉን በውስጥ ቁሳቁስ ለማሟላት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የአካባቢው ህብረተሰብ መሳተፍ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ማህበሩ ህብረተሰቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በሚያደርገው እንቅስቃሴ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ  የተናገሩት ደግሞ  የአምቦ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሚሊ ኬሳ ጡሪ ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ልማት ማህበር በዞኑ ካሉት ከ330 ሺህ በላይ አባላት በየዓመቱ 7 ሚሊዮን ብር ይሰበስባል፤ ዓመታዊ መዋጮውን ወደ 10 ሚሊዮን ብር ለማሳደግም አቅዷል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ሀምሌ 1/2009 ምሩቃን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ለሃገራቸው ዘላቂ እድገትና ብልጽግና መረጋገጥ ማዋል እንደሚገባቸው  ተመለከተ፡፡

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 8 ሺህ 289 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡

የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አዲስ ዓለም ባሌማ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ  እንዳሉት፣ ሃገሪቱ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን እድገት ከዳር ለማድረስ ምሩቃኑ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር ማዋል ይገባቸዋል፡፡

''የሃገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የከፈተውን ሰፊ የስራ ዕድል በመጠቀም እውቀታችሁን በተግባር ማዋልና የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞ ማፋጠን ይጠበቅባችኋል''  ብለዋል፡፡

''በምትሰማሩት የስራ ዘርፍም አገራችሁን በትጋትና በቅንነት ለማገልገል በቁርጠኝነት መነሳት አለባችሁ'' ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረህይወት በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች አሰልጥኖ ዛሬ ካስመረቃቸው መካከል  ሁለቱ በሦስተኛ ዲግሪ፣ ከ600 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል ደግሞ 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮውን በጥራት ለማሳካት የምርምር ቤተ ሙከራዎችና ዘመናዊ ቤተ ሙከራዎች  በማስፋፋትና በመገንባት ላይ ይገኛል እንደ ዶክተር ክንደያ ገለጻ፡፡

ዩኒቨርስቲው በመኸኒ፣ አብዓላ፣ ዓጉላዕ፣ ላሊበላና ውቅሮ ከተሞች የምርምር ጣቢያዎችን በመገንባት በምርምር የሳይንስ ግኝቶች በማፍለቅ የተማሪዎች የፈጠራ አቅም እንዲዳብር ለማድረግ እየሰራ ነው።

ከ52 የዓለም መንግስታትና የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ጋርም 115 ስምምነቶችን በመፈራረም አብሮ ለመስራት የተግባር እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ከእለቱ ተመራቂዎች መካከል በመካኒካል ኢንጂነሪንግ የተመረቀው ወጣት ተስፉ ገብረሊባኖስ በሰጠው አስተያየት በዩኒቨርሲቲው የአምስት ዓመት ቆይታው ከቀለም ትምህርት ባሻገር ከተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመጡ ወጣቶች ጋር  የአብሮ መኖርና የመቻቻል ባህል የቀሰምኩበት ነው ብሏል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊላንድ፣ ከኤርትራና ከኡጋንዳ የመጡ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ31 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መሰኮች እያሰለጠነ እንደሚገኝም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

ወልዲያ ሃምሌ 1/2009 የወልድያ ፖሊቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ  በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በደረጃ ያሰለጠናቸውን 406 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ፡፡

የኮሌጁ ምክትል ዲን አቶ አስረሳው ደርበው እንደገጹት፣ የዕለቱ ምሩቃን ከደረጃ 2 እስከ ደረጃ 5 የትምህርት መርሀ ግብሮች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

ምሩቃኑ በኮንስትራክሽን፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በቅየሳ፣ በብረታብረት፣ በሆቴል ማኔጅመንትና በሌሎች 18 የሙያ መስኮች የሰለጠኑ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ከተመራቂዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ በራሳቸው አቅም ሥራ ለመፍጠር የሚያበቃቸውን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት በስልጠና  ወቅት ማግኘታቸውን አቶ አስረሳው ተናግረዋል።

ተማሪዎች ወደ ኮሌጁ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ገንዘብ እንዲቆጥቡ መደረጉን ያስታወሱት አቶ አስረሳው፣ በዚህ ዓመት ብቻ ከ300 ሺህ ብር በላይ መቆጠባቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ ውስጥ ከ82 ሺህ ብር በላይ የሚሆነውን የቆጠቡት የዛሬ ተመራቂዎች ሲሆኑ፣ ተመራቂዎቹ በቡድን በመደራጀት የሥራ ዕቅድና ፕሮጀክት አዘጋጅተው ማጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

የወልድያ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ፍቅር መውደድ በበኩላቸው፣ ኮሌጁ ሥራ አጥ ዜጎችን በመቀነስ በኩል ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ተመራቂዎች በሰለጠኑበት ሙያ ሥራ ለመፍጠር ለሚያደርጉት ጥረት የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል።

በሆቴል ሙያ የሰለጠነችው ወጣት መሰረት ሲሳይ በሰጠቸው አስተያየት 10 ሆነው በመደራጀትና በኮሌጅ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም በምግብና መጠጥ አገልግሎት ሥራ ለመሰማራት ማቀዳቸውን ተናግራለች፡፡

የወልድያ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የማስተማር ሥራውን በ1990 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን ባለፉት 18 ዙሮች ከስድስት ሺህ 600 በላይ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ