አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 07 July 2017

መቀሌ ሰኔ 30/2009 ወጣቱን ከአደንዛዥ እጽ ጉዳት ለመታደግ  ሁሉም አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተጠቆመ፡፡

" አደገኛ እጽ የማይጠቀም ትውልድ እናፍራ" በሚል መሪ ሀሳብ  ዓለም አቀፍ የጸረ ሱስ ቀንን ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተከበሯል።

በፓናል ውይይት በተከበረው በዚሁ በዓል የተሳተፉት የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረህይወት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ሺሻ ፣ ሲጋራ ፣ጫትና ሌሎችም አደንዛዥች ዕፆች በተለይ ወጣቱን እየጉዳ ነው፡፡

"ከሱስ ነፃ የሆነ የተማረ የልማት ሀይል ለማፍራት የተጀመረው ጥረት ቢኖርም የተፈለገው ያህል ውጤት እያመጣ አይደለም "  ያሉት ዶክተር ክንደያ ወጣቱን ከችግሩ ለመከላከልና ከጉዳት ለመታደግ ሁሉም አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

የዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የማህበረሰብ አገልግሎት ኃላፊ  ፕሮፌሰር ፈቴን አባይ በበኩላቸው ወጣቱ ከማናቸውም አይነት ሱስ ነፃ ሆኖ ለአገር እድገትና ብልፅግና የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል ፡፡

ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው ከትምህርት ተቋማት ባሻገር  የማያቋርጥ የቤተሰብ ክትትል ሲኖር እንደሚገባና በተለይ ወላጆች ወጣቱን በመልካም ስነ ምግባር የመቅረፅ ግንባር ቀደም ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በሱስ የተጠመዱ ሰዎችን ለመታደግ እየሰራ የሚገኘው የመቀሌ ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ስራ አስኪያጅ  አቶ ኤልያስ ካልአዩ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሑፍ "በዓለም በአደንዛዥ እፅ ምክንያት በየደቂቃው ሦስት ሰዎችን ለህልፈት ይዳረጋሉ" ብለዋል።

በኢትዮጵያ  የተደረገ ጥናት ባይኖርም በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለአደጋው የተጋለጡ መሆናቸው  አቶ ኤልያስ ተናግረዋል፡፡

ድርጅታቸው በተገባደደው በጀት ዓመት ከመቀሌና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር  ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች የሱስ አደጋና መፍትሄው ዙሪያ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠቱን አመልክተዋል።

በተሰጣቸው ትምህርት ከሱስ ነጻ ከሆኑት መካከል የመቀሌ ከተማ ነዋሪ  ወጣት ተክሊት ዮሐንስ በሰጠው አስተያየት አደንዛዥ እጽ ለጥፋት የሚዳረግ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ያለሟቋረጥ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

በዓሉብ ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ከመቀሌ ከተማ የተወጣጡ ነዋሪዎች ፣ምሁራን፣  የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2009 መንግስት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ምሩቃን በሥራ እድል ፈጠራ መርሃ ግብር እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት  በሳምንታዊ የመንግስት አቋም  መግለጫው፤ መንግስት ዘንድሮ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚመረቁ ምሁራን ተቀጥሮ ከመስራት ባለፈ በተለያዩ የስራ ፈጠራ መርሃ ግብሮች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።

በጥራትና በቁጥር እያደገ የመጣውን የሰው ሃይል በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባትም ልዩ ልዩ ፓኬጆች ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ጽህፈት ቤቱ ጠቁሟል።

ጽህፈት ቤቱ ታላቁ መሪ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት "የድህነት ተራራ የሚናደው በዕውቀት ጥይት ነው" በሚል የተናገሩትን  በመጥቀስ ተመራቂዎች መንግሥት በዘረጋው የስራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብሮች እንዲሳተፉ ፍላጎት እንዳለው መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ ወጣቶች የቢዝነስ አስተሳሰብ ይዘው በቀጥታ ወደ ሥራ ፈጠራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

አገሪቷን ከድህነት ለማላቀቅ እና የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ እንዲቻል ዜጎች ሁሉ የሥራ ክቡርነትን ተቀብለው በተማሩበት መስክ ውጤታማ ሆነው እንዲገኙም ጠይቋል።

በዘንድሮ የትምህርት መርሃ ግብር ከ150 ሺ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች እንደሚመረቁ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች  ከ125 ሺ በላይ ተማሪዎች ያስመርቃሉ።

ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ለሁሉም ተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ ምኞቱን በመግለጽ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆን ምኞቱን ገልጿል።

  የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

 በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ

ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

                                                           ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም

 የድህነት ተራራ የሚናደው በዕውቀት ጥይት ነው!

 ዘንድሮ በጠቅላላው ከ150 ሺህ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ይመረቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የሚመረቁ ምሁራን ብዛት ከ125 ሺህ በላይ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግስት ለሁሉም ተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ እያለ ለተመራቂዎች መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላችሁ ምኞቱን ይገልጻል።

 ታላቁ መሪ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት የድህነት ተራራ የሚናደው በዕውቀት ጥይት ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የትምህርት ዘርፉ ከመንግሥት ጠቅላላ ዓመታዊ በጀት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እንዲወስድ በማድረግ ትምህርት በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ በውጤቱም ዛሬ ከ28 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በትምህርት ገበታ ላይ ለማሳተፍ ተችሏል።

 መንግሥት ቀደም ባሉት ዓመታት ካስገነባቸው 36 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪ  በሚቀጥለው ዓመት ሌሎች 11 ዩኒቨርስቲዎችን ወደሥራ በማስገባት አዳዲስ ተማሪዎችን እየተቀበሉ እንዲያስተምሩ ይደረጋል፡፡ ይህን ያህል ተቋማትን በማደራጀት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን እያስተማሩ በየዓመቱ ማስመረቅ  ምን ያህል ሃብት እንደሚጠይቅ መገመት አያዳግትም።  በተጨማሪም መንግስት የግል ባለሃብቱን በማበረታታት በርካታ የግል ተቋማትም ተፈጥረው ተመሳሳይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ በየዓመቱ በከፍተኛ ትምህርት እየሰለጠነ ወደሥራ የሚገባው የሰው ሃይል ብዛት እየጨመረ የመጣ ሲሆን ይኸው ሂደት  በቀጣይ ዓመታትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

 በአገራችን ለዘመናት የቆየውን ድህነት በማስወገድና በሂደትም ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በማሸጋገር በኢኮኖሚያችን ላይ ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በዕውቀቱ፣ በክህሎቱ፣ በአመለካከቱ እና በአምራችነት ስነምግባሩ የታነፀ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ይህንኑ በመገንዘብም መንግሥት በአንድ በኩል አጠቃላይ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚጠይቃቸው የኢንጂነሪንግና የሂሳብ ትምህርቶች እንዲስፋፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። ትምህርትን ከማስፋፋት ባሻገርም ጥራቱን ለማሻሻል የጥራት ፓኬጆችን አዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ ሲረባረብ ቆይቷል። ከዚሁ ጎን ለጎን በጥራቱና በቁጥር እያደገ የመጣውን የሰው ሃይል በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባትም ልዩ ልዩ ፓኬጆችን አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ጥረቱ ፍሬ እያፈራና በርካታ ወጣቶችን ሥራ ፈጣሪዎች እያደረገ ነው። በተጨማሪም 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ ወጣቶች የቢዝነስ አስተሳሰብ ይዘው በቀጥታ ወደ ሥራ ፈጠራ እንዲገቡ ለማስቻል ጥረቱ ቀጥሏል።

ውድ ተመራቂዎች! ይህቺ አገር ካላት አነስተኛ ጥሪት ላይ መድባ ያስተማረቻችሁ ወድ ልጆቿ ናችሁ፡፡ አገራችን ከድህነት እና ኋላቀርነት ለመላቀቅ እና ብሎም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ ትችል ዘንድ ተቀጥሮ ከመስራት በላይ ራዕይ እንዲኖራችሁ ትፈልጋለች፡፡ በመሆኑም ሥራን ከመጠበቅ ይልቅ በየተማራችሁበት የትምህርት መስክ በመደራጀት መንግሥት በነደፋቸው ፓኬጆች ተጠቃሚ እንድትሆኑ መንግስት ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

ውድ የተመራቂ ቤተሰቦች! አስተምራችሁ ለማስመረቅ በመብቃታችሁ በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ። ምረቃው በተመራቂዎች ህይወት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ያለው ነው። በማስከተልም ለቀጣዩ ህይወታቸው ትኩረት በመስጠት ሥራን ሳይንቁና ሳይመርጡ እንዲሰሩ ስነልቡናቸውን በማዘጋጀት፣ ተነሳሽነታቸውን በማጎልበት፣ ቁጠባን በማበረታታት እንዲሁም አስፈላጊውን ሞራል እና አቅም ከፈቀደም ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት ለሥራ ፈጣሪነት እንድታበረታቷቸው መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

 ተመራቂዎችን በአስፈላጊው ዕውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት ቀርጾ በማውጣት ረገድ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወታችሁ ላላችሁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ አስተዳደሮች እና መምህራን! የድህነት ተራራ ማፍረሻ ጥይቶችን በማቀበል ረገድ ለአገራችን እያደረጋችሁት ላለው ጉልህ አስተዋጽዖ መንግሥት ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ በአጠቃላይ አገራችንን ከድህነት ማላቀቅ እና የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ እንድንችል ዜጎች ሁሉ  የሥራ ክቡርነትን ተቀብለን በየተሰማራንበት መስክ ሁሉ ውጤታማ ሆነን እንድንገኝ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሰኔ 30/2009 በአዳማ ከተማ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በተሽከርካሪ ተጭኖ የተገኘ 169 ጀሪካን የምግብ ዘይት መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የከተማው ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ ዋና ሳጂን ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደገለጹት 83 ሺህ ብር ግምት ያለው ይሄው ባለ 25 ሊትር ዘይት የተያዘው  ከአዳማ ወደ አርሲ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ነው።

የተያዘውም ከትናንት በስትያ  ምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 - 24783 አዲስ አበባ የሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ዘይቱን በጤፍ ጭድ ሸፍኖ  በህገ ወጥ መንገድ ከከተማዋ ለማስወጣት ሲሞክር  ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ ነው።

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዳማ ቅርንጫፍ ባልደረባ ነኝ ብሎ  የተያዘውን የምግብ ዘይት ህጋዊ በማስመሰል ለማስመለጥ ሲሞክር የተገኘው ግለሰብም ተይዟል።

የምግብ ዘይቱን የጫነው አሽከርካሪ ለጊዜው ቢሰወርም በፖሊስ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ያመለከቱት ዋና ሳጂን ወርቅነሽ ህገ ወጥነትን ለመከላከል ህብረተሰቡ እያሳየ ያለውን  ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2009 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት ዓመት እቅድ አፈጻፅም ውጤታማ መሆኑን አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ገለጹ።

ምክር ቤቱ የ2009 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማድመጥና የተለያዩ አዋጆችን በማጽደቅ የሥራ ዘመኑን አጠናቋል።

ዛሬ አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ ልዩ ስብሰባ ተካሂዷል።

የምክር ቤቱን የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ፤ " በበጀት ዓመቱ ምክር ቤቱ ያከናወናቸው ተግባራት በሁሉም ዘርፎች የተሻለና ውጤታማ ነበር" ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ቅድሚ ተሰጥቶ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የአቅም ግንባታ ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም የእውቀት፣ የክህሎትና የአመለካክት አቅምን ወደላቀ ደረጃ በማድረስ አመራር አባላቱንና አባሉን ወቅቱ ለሚጠይቀው ተልዕኮ ማብቃት መቻሉን ተናግረዋል።

የህዝብን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በተሻለ ደረጃ ያረጋገጡ ጥራት ያላቸው ሕጎች መውጣታቸው ተመልክቷል።

የ2010 የፌዴራል መንግስትን የበጀት አዋጅን ጨምሮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተረቀቁ 68 ልዩ ልዩ፣ የብድርና ዓለምአቀፍ ስምምነቶችና የማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች ውይይት ተደረጎባቸው ጸድቀዋል።

"የተቀናጀ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግም የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የዓመቱ ግቦች ተሳክተዋል፤ የህዝብ ተጠቃሚነትም ተረጋግጧል” በማለት ነው የገለጹት።

በዲፕሎማሲ ግንኙነት የአገር መልካም ገጽታ ግንባታ እንዲጠናከር መደረጉን ጠቁመው፤ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን በሁሉም ስራዎች ውስጥ በማከተት ተፈጻሚነታቸው ማረጋገጥና ተጠቃሚነትን ማሻሻል መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በመንግስት አሰራር ግልጽና ተጠያቂነትን እያረጋገጡ የመሄድ ልምዶች እየዳበሩ መምጣታቸውን የገለጹት አፈ ጉባኤው፤ "ህዝብ በሚያገኘው መረጃና በተግባር በየዘርፉ ተጠቃሚ በመሆኑ ሥርዓቱ የህዝብ አመኔታ እያጎለበተ መሄዱን አረጋግጧል” ብለዋል።

ምክር ቤቱ በጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በተገኙ ግብዓቶችንና በተወሰዱ ማስተካከያዎች ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ያደረገው ጥረት አበረታች እንደሆነም ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ዓመታዊ በጀቱን 97 በመቶ ለታለመለት ዓላማ በማዋል ያቀዳቸውን ግቦች ማሳካቱን አብራርተዋል።

በዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ቢኖርም ከመንግስት የህዳሴ ጉዞ አኳያ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቋቋሚያ እና የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።

የመንግስትና የግል አጋርነት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በመምራት የ2009 በጀት ዓመት የሥራ ዘመኑን አጠናቋል።

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ሰኔ 30/2009 የትግራይ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት ለ2010 የበጀት ዓመት በክልሉ ለሚከናወኑ ስራዎች ማስፈፀሚያ የ12 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ፡፡

 ምክር ቤቱ በመቀሌ ከተማ የአይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም የቀረበው ረቂቅ አዋጅና የዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ማምሻውን ተጠናቋል፡፡

 በምክር ቤቱ የበጀትና ኦዲት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ንጉሰ ለገሰ በቀረበው ዝርዝር ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ከተወያዩ በኋላ ስራ ላይ እንዲውል በአብላጫ ድምፅ  አፅድቀውታል።

 በጀቱ የህዝብን የልማት ጥያቄ የማይመልስ ነው በማለት አንድ የምክር ቤቱ አባል በተቃውሞ ወጥተዋል፡፡

 በጀቱ ድህነትን ለመቀነስ ለተያዙ ፕሮግራሞች፣ ለስራ እድል ፈጠራና ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ ይውላል፡፡

 ምክርቤቱ ካፀደቀው በጀት ውስጥ 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ከፌዴራል መንግስት በቀመር የተገኘ ሲሆን ፣ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከክልሉ የተለያዩ ገቢዎች የሚገኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 ቀሪው ገንዘብ ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰበሰብ ገንዘብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ምክር ቤቱ ካፀደቀው በጀት ውስጥ 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለወረዳዎችና ከተሞች የተመደበ ሲሆን ቀሪው በክልል ደረጃ ለሚከናወኑ የካፒታልና መደበኛ በጀት ይውላል ፡፡

 የፀደቀው በጀት ካለፈው ዓመት በጀት ጋር ሲነፃፀር የ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

 የዘንድሮ የበጀት ድልድል የክልሉ ምክር ቤት በተከተለው አዲሱ ቀመር ድልድል የተሰራ በመሆኑ አብዘኛዎቹ የገጠር ወረዳዎች ባለፈው አመት ከተመደበላቸው በጀት ቅናሽ አሳይተዋል፡፡

 ቅናሽ ያሳየባቸው ወረዳዎች ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ተፈልጎ  ካለፈው አመት  ተመሳሳይ የሆነ በጀት እንዲያዝላቸው ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

 ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ከምስራቃዊ ዞን አቶ ሃይላይ ዘርኡ እንደገለጡት ''ለወረዳዎችና ከተሞች የተደለደለው በጀት ከደመወዝና ስራ ማስኪያጃ አልፎ ሌላ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ያስቸግራቸዋል'' ብለዋል፡፡

 ከማእከላዊ ዞን የተወከሉት የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ በሪሃ ታደሰ ደግሞ  ''በጀቱ ህዝቡ የሚያነሳቸው አዳዲስ የልማት ጥያቄዎች የማይመልስ ነው'' ብለዋል፡፡

 የምክር ቤቱ አባላት በመጨረሻም በመቀሌ አይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

 ምክር ቤቱ 81 የወረዳ፣ የከፍተኛ ዳኞችና ሬጅስራሮች ሹመት በማፅደቅ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ሰኔ 30/2009 በደቡብ ሱዳን መንግስትና ተቃዋሚዎች መካከል ያገረሻውን ግጭት  በመሸሽ ብዛት ያላቸው የሀገሪቱ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸውን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ  አስተዳደር አስታወቀ።

በአስተዳደሩ የጋምቤላ የስደተኞች ጉዳይ አስተባባሪ አቶ መንግስቱ ደሳለኝ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በግጭቱ ምክንያት ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ  ሰባት ሺህ የሚደርሱ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በመሸሽ ጋምቤላ ክልል ገብተዋል።

ስደተኞቹ አብዛኞቹ ህጻናትና ሴቶች በመሆናቸው አፋጣኝ ሰብዓዊ አገልግሎት እንደሚሹ ጠቁመው "ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምሯል "ብለዋል።

ከሀገራቸው ሸሽተው የመጡትን እነዚህ ስደተኞች አስተዳደሩ  በጊዜያዊ  ማቆያ በመቀበል ደህንነታቸውን እየጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አስተባባሪው በደቡብ ሱዳን የተፈጠረው የጸጥታ ሁኔታ ባፋጣኝ መፍትሄ  ካለገኘ የስደተኞች ቁጥር በእጅጉ ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የስደተኞቹ ቁጥር እየበዛ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ  የሰብአዊ  አገልገሎት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያከብደውም  ጠቁመዋል።

በተለይም ስደተኞች ከሌለው ጊዜ በተለየ ሁኔታ  የቀንድ ከብቶቻቸውን ይዘው እየመጡ በመሆኑ  የመጠለያና  ሌሎች  አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ ያደረገዋል እንደአስተባባሪው ገለጻ፡፡

ይሁን እንጂ  አስተዳደሩ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለስደተኞቹ የተቻለውን ሁሉ ሰብዓዊ ድጋፍ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን  ጠቅሰዋል፡፡

ከስደተኞች መካከል ወይዘሮ ኛሪክ ቦዎት በሰጡት አስታያየት  በሀገራቸው በተፈጠረው   ግጭት ሸሽተው  ወደ ኢትዮጵያ መሬት በመግባት ደህንነታችን እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢያችን በተፈጠረው  ከፍተኛ የሆነ የእርስ በርስ ግጭት ሸሽተን ወደ ኢትዮጵያ መሬት በመግባት ደህንነታችን እየተጠበቀ ነው፡፡”

ሌላዋ የደቡብ ሱዳን ስደተኛ ወይዘሮ ኛረካ ካንግ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሰት   ላደረገልን አቀባበል በማመስገን የመጠለያና የምግብ አቅርቦት በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ቤት ንብረታቸውን ጥለው በመምጣታቸው ለልጆቻቸው የምግብና የመጠለያ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ደግሞ  አቶ ሆዝ ቤይ የተባሉት ስደተኛ ናቸው፡፡ 

ይህ ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት  ላደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸው  አቅርበዋል።

በደቡብ ሱዳን  የተፈጠረው  ግጭት በመሸሽ ቀደም ሲል ከ335 ሺህ በላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ተጠልልው እንደሚገኙ የስደተኞችና ከሰደት ተመላሾች ጉዳይ  አስተዳደር  የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ሰኔ 30/2009 በትግራይ ክልል የሚገኙ 13 የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖች ከዱቄት ፋብሪካ ባለንብረቶች ጋር የስንዴ ምርት ግብይት ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ትላንት ተፈራረሙ፡፡

ዩኒየኖቹ ስምምነቱን የተፈራረሙት በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ ስምንት የዱቄት ፋብሪካ ባለንብረቶች ጋር ነው።

በስምምነቱ መሠረት ዩኒየኖቹ በሚቀጥለው የምርት ዘመን ጥራቱን የጠበቀ ከ53 ሺህ ኩንታል በላይ የዳቦ ስንዴ ምርት ለፋብሪካዎቹ ያቀርባሉ፡፡

የፋብሪካ ባለንብረቶቹ ደግሞ ዩኒየኖቹ ያቀረቡትን የስንዴ ምርት በወቅቱ ከሚኖረው የስንዴ ዋጋ ስምንት በመቶ በመጨመር ግዢ ይፈጽማሉ፡፡

ስምምነት ከተፈራረሙት ዩኒየኖች መካከል በእንዳመሆኒ ወረዳ የሚገኝ ቦክራ የአርሶ አደሮች ህብረት ስራ ዩኒን የቦርድ ሰብሳቢ አርሶ አደር አብረሀ በርኸ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ዩኒየኑ ከመሰረታዊ ማህበራት 10 ሺህ ኩንታል ስንዴ በማሰባሰብ ለፋብሪካዎቹ ለማቅረብ ስምምነት አድርጓል ።

ዩኒየኑ ከፋብሪካ ባለንብረቶች ጋር ቀጥታ የገበያ ትስስር በማድረጉ አርሶ አደሩና መሰረታዊ ማህበራት የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡

የደጉዓቴምቤን ህብረት ስራ ዩኒየን ሰብሳቢ ቄስ ገብረሰለማ ግርማይ በበኩላቸው ''የገበያ ትስስር መፈጠሩ አርሶ አደሩ የተሻለ ገበያ እንዲያገኝ የሚረዳ ከመሆኑ በተጨማሪ ምርቱን ለመሸጥ ገበያ መሄድ አይጠበቅበትም'' ብለዋል፡፡

ስንዴ ከውጭ ከማስገባት ይልቅ ለአርሶ አደሮች የተሻለ ዋጋ በመስጠት በብዛት እንዲያመርቱ ማድረግ የፋብሪካዎች ኃላፊነት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በመቀሌ ከተማ የሚገኘው የሁዳ ዱቄት ፋብሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ ከበደ ናቸው፡፡

ፋብሪካዎቹ  ዩኒየኖች ከሚያቀርቡት ዋጋ ባነሰ ገበያ ላይ ምርቱን የሚያገኙ ቢሆንም አርሶ አደሮችን ለማበረታታት ከወቅቱ ገበያ ከፍ ባለ ዋጋ ለመግዛት ተነሳሽነት መውሰዳቸውን ገልፀዋል፡፡

በግብርና ትራንስፎርሜሽን  ኤጀንሲ የትግራይ  ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብረሃ ኪዳነማሪያም በበኩላቸው  የአርሶ አደሮች የህብረት ስራ ዩኒየኖችን ከፋብሪካዎች ጋር ቀጥታ የገበያ ትስስር ለማድረግ ኃላፊነት ወስዶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡፡

ከስንዴ ምርት በተጨማሪ ለራያ ቢራ ግብአት የሚሆን የቢራ ገብስ ለማምረት በደቡባዊ ዞን ሁለት ወረዳዎች ፋብሪካውንና አርሶ አደሮችን የማስተሳሰር ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ደግሞ ጤፍ አምራች ከሆኑ አርሶ አደሮችን ከሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር ለማስተሳሰር እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2009 አቤት ሆስፒታል ለጅምላ ድንገተኛ አደጋ ተጎጅዎች ህክምና በተቀናጀ  መንገድ መስጠት ጀመረ፡፡

ሆስፒታሉ በጅምላ የሚከሰቱ አደጋዎች ሲያጋጥሙ በተቀናጀ መልኩ ምላሽ የሚሰጥበትን አካሔድ አስመልክቶ ዛሬ የሙከራ ልምምድ አድርጓል፡፡

እስካሁን ሆስፒታሉ በአንድ ጊዜ እስከ 30 ለሚደርሱ ተጎጂዎች እርዳታ የመስጠት አቅም የነበረው ሲሆን፤ አሁን በጀመረው የተቀናጀ አሰራር ይህንን ቁጥር ወደ 50 ከፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የሆስፒታሉ የድንገተኛ አደጋዎች ኮማንደር አቶ ዮናስ አበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አገልግሎቱ በተለይም በትራፊክ አደጋና የግንባታ ቦታዎችን ጨምሮ ሌሎች ለሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያስችላል፡፡

ለዚሁ ስራም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ ባለሙያዎችን በማሰልጠን የነርቭና የአጥንት ህክምናን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ 24 ሰዓት ሕክምና አገልግሎትይሰጣል ፡፡

ሆስፒታሉ ለተጎጅዎች ፈጣን እርዳታ ለመስጠት የሚችል ቡድን ማቋቋሙንም ነው ይፋ ያደረገው፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም አደጋ በተፈጠረባቸው ቦታዎች ተገኝቶ አገልግሎት ለመስጠትም ከሌሎች የጤና ተቋማት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑንም አቶ ዮናስ ጠቁመዋል፡፡

ከተቋቋመ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ሆስፒታል በዚህ ዓመት ብቻ በትራፊክ፣ በእሳትና በሌሎች አደጋዎች ለተጎዱ ከ11 ሺ በላይ ታካሚዎች አገልግሎት መስጠቱንም አመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2009 የእንስሳት ደህንነት ጥበቃ ላይ የሚሰራ የሚዲያ ፎረም ተቋቋመ።

ፎረሙ የእንስሳትና አሣ ሀብት ልማት ሚኒስቴርና 'ብሩክ ኢትዮጵያ' የተሰኝ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ናቸው ያቋቋሙት።

ኢትዮጵያ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን 11 ሚሊዮን የቁም እንስሳት ወደ ውጭ ለመላክ አቅዳ እየሰራች ነው።

በእንስሳትና አሣ ሃብት ሚኒስቴር የእንስሳት ልየታ፣ ምዝገባና ደህንነት ዳይሬክተር ዶክተር ሀድጉ ማንደፍሮ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ አገሪቷ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ቢኖራትም የሚፈለገውን ያህል ጥቅም ማግኘት አልቻለችም።

ለዚህም ምክንያቱ የእንስሳቱ ደህንነትና ጤንነት በተገቢው መልኩ ባለመጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

የእንስሳት ምርት፣ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግና የሚፈለገውን ጥቅም ለማግኘት ስለ ደህንነታቸው ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ፎረሙና መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

ሚኒስቴሩ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ጋር በመተባበር የአምስት ዓመት የእንስሳት ደህንነት ስትራቴጂ እያዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

የብሩክ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ጥበቡ ደበበ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የፎረሙ መቋቋም ዋና ዓላማ በእንስሳት ደህንነትና ጥበቃ ላይ ያለውን ዝቅተኛ አመለካከት ለመቀየር ነው።

እንስሳት ለአርብቶና አርሶ አደሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ መሠረት ሆናቸውን አውስተው፤ እንስሳቱ የሚፈለገውን ጥቅም እንዲሰጡ ደህንነታቸውና ጤንነታቸው መጠበቅ እንዳለበት ገልፀዋል።

ግንዛቤ ለመፍጠርም የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ ሲሆን ፤ ፎረሙን መመስረት አስፈላጊ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ፎረሙ የእንስሳት ደህንነት እንዲጠበቅና የሚፈለገውን ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ ግንዛቤ የማስጨበጡ ተግባር ላይ በትጋት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሀምሌ 1/2009 ዛሬ ለባለእድለኞች የሚተላለፉት የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዋጋና የዲዛይን ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል።

ይህን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማትኢንተርፕራይዝና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ለእድለኞች የሚተላለፉ ቤቶች ብዛት 972 ሲሆኑ፤ ባለ አራት ባለ ሶስትና ባለሁለት መኝታ ቤት ያላቸው ለዕጣ ዝግጁ ሆነዋል።

በዚህም መሰረት ባለ አራት መኝታ 168 ነጥብ 68 ካሬ ሜትር፤ ባለ ሶስት መኝታ 129 ነጥብ 5 ካሬ ሜትር እንዲሁም ባለ ሁለት መኝታ 124 ነጥብ 97 ካሬ ሜትር ስፋት እንደሚኖራቸው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ ተናግረዋል።

በዚህም ቤቶቹ በካሬ ሜትር 4 ሺ 918 ብር ከ72 ሳንቲም ዋጋ ተቆርጦላቸዋል።

የዋጋ ማስተካካያ የተደረገው ቤቶቹ ቀድሞ ሊሰሩበት ከነበረው ዓይነት የዲዛይን ለውጥና ማሻሻያ መሰራቱ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

በዚህ መሰረት ባለ አራት መኝታ 829ሺ 689 ከ 69 ሳንቲም፤ ባለ ሶስት መኝታ ቤት 636 ሺህ 974 ከ24 ሳንቲም እንዲሁም ባለሁለት መኝታ ቤት 614 ሺህ 692 ከ 43 ሳንቲም በሆነ ዋጋ ለእድለኞች ይተላለፋሉ።

በቅዳሜው ዕጣ ለ18 ወራት በተከታታይ በመቆጠብ መቶ በመቶ የከፈሉ 11 ሺ 88 ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ በዚህኛው ዕጣ ለባለ አንድ መኝታ የተመዘገቡ ቆጣቢዎች አልተካተቱም፡፡

ለዚህ በምክንያትነት የተነሳው ደግሞ ለጊዜው ባለ አንደ መኝታ ያላቸው ቤቶች ባለመዘጋጀታቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ አብራርተዋል።

አዲስ በተደረገው የዲዛይን ማሻሻያ ባለ አራት መኝታ ያላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው በእጣው ውስጥ መካተታቸውን ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።

ባለአራት መኝታ ቤት ከዕጣው ውጭ ስለሆነና የውል ስምምነት ባለመኖሩ ባለ ሶስት መኝታ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች አቅሙ ካላቸው መውሰድ እንዲችሉ በጋራ ስምምነት ተደርጎ ባለ አራት መኝታዎች አቅማቸው ለሚችሉ ባለ ሶስት መኝታ ለተመዘገቡ እድሉን እንዲጠቀሙ መደረጉንም ነው አቶ በቃሉ የጠቆሙት።

በዚህ የዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት በእያንዳንዱ መርሃግበር 20 ሰዎች በተጠባባቂ እጣ ይያዛሉም ነው የተባለው፡፡

በእጣው ውስጥ የመንግስት ሰራተኛ ሆነው መቶ በመቶ የቆጠቡ 20 በመቶ ቅድሚያ እድል ሲኖራቸው፤ ለዲያስፖራ ደግሞ ሦስት በመቶ ቅድሚያ የማግኘት እድል ተሰጥቷቸዋል።

ዛሬ የሚተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች የእጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት በመገናኛ ብዙሃን በቀጥታ እንደሚተላለፍ ተጠቁሟል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ