አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 06 July 2017

አዲስ አባ ሰኔ 29/2009 ወላይታ ዲቻ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥሎ ማለፍ ሻንፒዮና አሸናፊ ሆነ።

የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ በወላይታ ዲቻ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዚህም ክለቡ እ.ኤ.አ በ2018 በሚካሄደው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽ ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ መሳተፍ መቻሉን አረጋግጧል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ወላይታ ዲቻ ከመከላከያ ጋር ባደረጉት የፍጻሜ ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ይህም ሁለቱ ተጋጣሚዎች ወደ መለያ ምት እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል።

በመለያ ምቱም ወላይታ ዲቻ አራት ለሁለት በሆነ ውጤት በመርታት ሻምፒዮን መሆን ችሏል።

የፍጻሜው ተፋላሚ የነበረው መከላከያ በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ቢሆንም፤ በሁለተኛው አጋማሽ ወላይታ ዲቻ ባገኘው የፍጹም ቅጣት ምት አንድ አቻ መሆን በመቻላቸው ነው ወደ መለያ ምት ያመሩት።

ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ፕሪሜይር ሊግ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊ በመሆኑ፤ በ2017 እና በ2018 ለአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እንደሚሳተፍ ማረጋገጡ ይታወሳል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2009 በአዲስ አበባ ከተማ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሁለት የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከነገ በስቲያ ለእድለኞች እንደሚተላለፉ ተገለጸ።

ቤቶቹ ግንባታቸው በጥራት ተጠናቆ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተረከባቸው መሆኑም ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስራ ኃላፊዎች ዛሬ በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የሚተላለፉት ቁጠባ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለተከታታይ 18 ወራት ያለማቋረጥ ለቆጠቡና ሙሉ ለሙሉ ከፍለው ላጠናቀቁ ባለእድለኞች ነው።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ እንዳሉት፤ መንግስት የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በያዘው እቅድ መሰረት በሰንጋ ተራና ክራውን  አካባቢዎች ግንባታቸው የተጠናቀቁ 972 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለእድለኞች ይተላለፋሉ።

የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ እንዲሁም የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶች እንደተሟላላቸው ኃላፊው ጠቁመዋል።።

በዕጣውም የመንግስት ሰራተኛች 20 በመቶ ዲያስፖራዎች ደግሞ ሦስት በመቶ የቅድሚያ ተጠቃሚነት እድል ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ቀሪው ድርሻ ለሌሎች ባለእድለኞች እንደሚሆን አቶ ይድነቃቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ባንኩ ከመንግስት ጋር በገባው ውል መሰረት የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ምንም ዓይነት የጥራት ችግር እንደሌለባቸው አረጋግጧል።  መሰረተ ልማታቸው በተገቢው ሁኔታ የተሟላ መሆኑም ቁጥጥር ተደርጎባቸው ርክክብ ፈጽሟል።

በሁለቱ የግንባታ ስፍራዎች ተጠናቀው ለባለእድለኞች ከሚተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ 320 የንግድ ሱቆች ለጨረታ እንደሚቀርቡ በመግለጫው ተብራርቷል::

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው እንደተናሩት፤ የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ የግንባታ ቦታዎች በ40/60 የቤት ልማት መርሃ ግብር 39 ሺ ቤቶች እየተገነቡ ናቸው። 

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማግኘት 164 ሺ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በመቆጠብ ላይ ያሉት 140 ሺ መሆናቸው ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ሰኔ 29/2009 በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ቢገቡም  ምቹ የመስሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በየበኩላቸው በወጣቶች የተነሳው ችግር በቅርቡ እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡

ወጣቶቹ እንዳሉት በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መሰኮች ተሰማርተው እየሰሩ ቢሆንም የመስሪያ ቦታና ብድር አገልግሎት ስላልተመቻቸላቸው በተፈለገው ደረጃ መንቀሳቀስ አልቻሉም።

አማኑኤል ፒተር በከተማው  በብረታ ብረትና እንጨት ሥራ የተሰማራ ወጣት ሲሆን  በማህበር ተደራጅቶ በሚያገኘው ገቢ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሆኖም የብድር አገልግሎት ባለመመቻቸቱ ሥራዎቻቸውን  ማስፋፋት እንዳልቻሉ ነው ያመለከተው።

"ተደራጅተን በመስራታችን ከምናገኘው ገቢ ተጠቃሚ ከመሆናችንም  ባሻገር የሙያ ክህሎት ባለቤት ሆነናል "ያለው ደግሞ ሌላው ወጣት ኡቦንግ ቻም ነው።

ወጣቱ አልባሌ ቦታ ከመዋል ይልቅ በማህበር ተደራጅቶ ቢሰራ ተጠቃሚ  እንደሚሆን የጠቀሰው  ወጣት ኡቦንግ ፣ መንግስት  ለወጣቱ የሚያደርውን እገዛ ሊያጠናክር እንደሚገባም ጠቁሟል።

ወጣት ያሲን ኩቤ  በበኩሉ ተደራጅቶ በዶሮ እርባታ ላይ  መሰማራቱ ገልፆ  ምርቱን በበቂ ሁኔታ ለህብረተሰብ ለማቅረብ በገንዘብ ማነስ ምክንያት እንዳልቻለ ተናግሯል።

"በማህበር ተደራጅተን ብንሰራም የመስሪያና የመሸጫ  ቦታ ባለማግኘታችንና የገበያ ትስስር  ባለመፈጠሩ  ተጠቃሚ ልንሆን አልቻልንም "  ያለው ደግሞ ወጣት ዮሐንስ ተስፋዬ ነው።

መንግስትም ይህን ችግር በመረዳት መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክቷል።

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አከኔ ኡፓዳ የወጣቶችን ጥያቄ ለመመለስ  አስተዳደሩ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ አካባቢዎች የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ አከኔ "እነዚህን ቦታዎች ለወጣቶች በቅርብ ቀን እንሰጣቸዋለን " ብለዋል፡፡

የክልሉ ብድርና ቁጠባ ተቋም ኃላፊ አቶ ቦል ዋኝ በበኩላቸው ወጣቶች ብድሩን ለማግኘት የሚጠበቅባቸውን የስራ እቅድ አሟልተው ባለማቅረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶቹ እንደ ሀገር በተጀመረውን ተዘዋዋሪ  የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆኑ ግንዛቤ ለማስጨባጥ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው  የሚጠበቅባቸው አሟልተው ለሚቀርቡ ወጣቶች  ከሐምሌ ወር 2009ዓ.ም ጀምሮ ብድሩ እንደሚለቀቅላቸው ተናግረዋል። 

በጋምቤላ ከተማ የዘንድሮን ሳይጨምር ከ1ሺህ 300 በላይ ወጣቶች ተደራጅተው በተደረገላቸው ድጋፍ በአገልግሎት ፣ በንግድ፣ በማምረቻና በእንስሳት እርባታ ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውን ከከተማው አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ሰኔ 29/2009 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጣና ሀይቅን የአሳ ሀብት ከጉዳት ጠብቆ በተገቢው ጥቅም ላይ እንዲውል የቴክኖሎጂ የምርምር ማዕከል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መስፍን ለኢዜአ እንደተናገሩት ተቋሙ  የሀይቁን የአሳ ሀብት በመጠበቅ በኩል በምርምር የታገዘ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

የተመናመኑ ነባር ዝርያዎችን የመጠበቅ እንዲሁም አዳዲስ የአሳ ዝርያዎችን ደግሞ የማላመድ ስራ በሀይቁ ዳርቻ ባቋቋመው የቴክኖሎጂ የምርምር ማዕከል እየሰራ ይገኛል፡፡

ዳይሬክትሩ እንዳሉት ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዩኒቨርሲቲው በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ በማስገንባት ላይ የሚገኘው ዘመናዊ የአሳ ማራቢያና ስነ-ህይወታዊ ኡደት ጥናት ማካሄጃ ኩሬ 90 በመቶ ተጠናቋል፡፡

አሳን በዘመናዊ ኩሬ የማራባት ቴክኖሎጂን ከማስተዋወቅ ባለፈ ዝርያቸው የተመናመኑ አሳዎችን አራብቶ መልሶ ወደ ሀይቁ በመጨመር ህልውናቸውን የማስቀጠል አላማ አለው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሀይቁ አሳ በማስገር ለተሰማሩ ሶስት ኢንተርፕራይዞች የአሳ ሀብቱን በማይጎዳ መልኩ እንዲያመርቱ በ700ሺ ብር ወጪ የገዛቸውን ሶስት ዘመናዊ ጀልባዎች ድጋፍ አድርጓል እንደዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የአሳ ሀብት መምህር  ኪዳኔ ምስጋናው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት ዓመታት የጣና ሀይቅ የአሳ ሀብት የሚገኝበትን ደረጃ በሀይቁ ሶስት ቦታዎች ጥናት ማካሄዱን ተናግረዋል፡፡

በጥናቱ መሰረት የሐይቁ የዓሳ ሃብት እየቀነሰ በመምጣቱ ከአራት ዓመት በፊት አንድ አሳ አስጋሪ በቀን ያሰግር የነበረው 10 ኪሎ ግራም አሁን ወደ ሁለት ኪሎ ግራም ዝቅ ማለቱን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት የአሳ መራቢያ ወራቶች የማስገር ስራ በስፋት መካሄድ፤ ደረጃቸውን ባልጠበቁ መረቦች ለምግብነት ያልደረሱ የአሳ ጫጩቶችን በማጥመድ ለገበያ ማቅረብ የሀይቁን የአሳ ሀብት እንዲመናመን ማድረጉን ጥናቱ አሳይቷል፡፡

የእምቦጭ አረም የአሳዎችን ስጋ ጣእም በመቀየር እንዲሁም የአሳ መራቢያ ቦታዎችን በመውረርና የጸሃይ ብርሃን ወደ ሀይቁ እንዳይገባ በመከላከል በሀብቱ  ላይ ስጋት መፍጠሩንም መምህር ኪዳኔ ተናግረዋል፡፡

በጣና ሀይቅ እስከ 18 የሚደርሱ የአሳ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን በተለይ ነጭ አሳና ቀረሶ የተባሉት ለምግብነት በስፋት የሚውሉ ናቸው፡፡   

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ሰኔ 29/2009 በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ950 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ መደረጉን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ባሃሩ ተክሌ ለኢዜአ እንደገለጹት ወጣቶቹ የስራ እድል ካገኙባቸው ዘርፎች መካከል ግብርና፣ግንባታ፣ማዕድን ልማት፣ አነስተኛ ንግድ፣ ማምረቻ እንስሳት እርባታና ማድለብ ይገኙበታል፡፡

በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ለወጣቶቹ በመደበኛነት ከተሰጠው አንድ ቢሊዮን ብር በተጨማሪ የክልሉ መንግስት የመደበውን ከ660 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ስራ ላይ አውሏል፡፡

የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እጥረትን ለማቃለል በክልሉ በህገ ወጥ መንገድ በባለሃብቶችና በክራይ ሰብሳቢ አመራሮች ተይዞ የነበረ ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መንግስት በማስመለስ ለወጣቶች ተላልፏል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለፃ አዲሱን የወጣቶች የዕድገትና የልማት ፓኬጅ መሰረት ያደረገ የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት፣ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ተግባራት ተከናውኗል።

የጅማ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ጆብር በሰጡት አስተያየት በዞኑ ከ56 ሺህ በላይ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ መደረጉን ተናግረዋል።

በህገ ወጥ መንገድ የተያዘን ከ6 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በማስመለስ ለወጣቶች መተላለፉን ጠቁመው "እስካሁን ባለው ሂደት ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ለወጣቱ ተሰራጭቷል" ብለዋል።

ከምልመላ ጀምሮ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በተከናወነው ስራ ከ47 ሺህ በላይ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የአርሲ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ አብቾ ናቸው።

በዞኑ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ለወጣቶች በማሰራጨት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ዘርፍ የ2009 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም፣ የቀጣዩ የስራ ዘመን መሪ ዕቅድ እና የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የሚመከር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ከክልሉ 20 ዞኖችና ከሁሉም የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ናቸው፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ጅግጅጋ ሰኔ 29/2009 የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፖሊስ  አባላትና አመራሮች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል  ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ  ለገሱ።

የተለገሰውን ገንዘብ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር  በክልሉ  ለድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሜቴ ሰብሳቢ አቶ ከደር መዓልን አሊ ትናንት አስረክበዋል፡፡

ኮሚሽነር ፋርሃን ጣሂር በርከድሌ በዚህ  ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ  የክልሉ ፖሊስ አባላትና አመራሮች የለገሱት ገንዘብ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ነው፡፡

የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ ከማረጋገጣቸው ባሻገር ለድርቅ ተጎጂዎች ያደረጉት ድጋፍ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህልን እንደሚያጠናከር ተናግረዋል፡፡

የድርቅ ተጎጂዎቹ መልሰው እንዲቋቋሙ የክልሉ ፖሊስ አባላት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል ።

የክልሉ ፖሊስ አባል ኮንስታብል ግርማ ስንታየሁ በሰጡት አስተያየት የአንድ ወር  ደሞዛቸውን  በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች  ድጋፍ ሲያደረጉ በራሳቸው ፈቃድ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ለድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሜቴ ሰብሳቢ በበኩላቸው ከፖሊስ አባላትና አመራሮች የተለገሰው ገንዘብ ለድርቅ ተጎጂዎች  የምግብ ድጋፍ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

ከፖሊስ አባላትና አመራሮች ያደረጉት ድጋፍ ለሌሎች ተቋማት አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸው አቀርበዋል።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አንወር አሊ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ  ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ክልሉ  ከፌዴራልና ከዓለም ምግብ ድርጅት ጋር በመተባባር የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ሌሎች አካላት ጭምር እገዛቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡ 

 

Published in ማህበራዊ

ሀረር ሰኔ 29/2009 በሐረሪ ክልል ከ280 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የኤረር ቂሌ የንጹህ መጠጥ ውኃ ኘሮጀክት ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱን የመረቁት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ ናቸው።

የክልሉ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን የምህንድስና ስራ ሂደት ኃላፊና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ መሐመድ አህመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በየካቲት ወር 2007 ግንባታው ተጀምሮ ለአገልግሎት የበቃው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 50 ሺ የሚደርሱ የኤረርና ሶፊ ወረዳ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል።

በዚህም 68 በመቶ የነበረውን የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ወደ 75 በመቶ ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ ስርጭትን በሁሉም አካባቢ ለማዳረስም የመስመር ማስፋፊያ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የዲያስፖራ መኖሪያ ቤቶች፣ የሴቶች የእደ ጥበብ መማሪያና የክልሉን የግብርና ልማት እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነትና የዲያስፖራውን ጥያቄ ለመመለስ እያከናወነ ያለው አበረታች ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2009 በኢትዮጵያ በሚታዩ የጤና ችግሮች ዙሪያ በምርምር ያገኙትን የመፍትሄ ሃሳብ ያቀረቡ 14 ተመራማሪዎች የስራ ውጤቶቻቸውን በተግባር ለመፈተሽ የሚያስችላቸውን ስምምነት ከአለርት ማዕከል ጋር ዛሬ ፈጸሙ።

ስምምነቱን የፈጸሙት ተማራማሪዎች በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና የህክምና ተቋማት የሚያገለግሉ ኢትዮጵያውን ምሁራን ናቸው።

ተመራማሪዎቹ የተግባር ፍተሻ ለማድረግ የውል ስምምነቱን ያደረጉት በማዕከሉ ስር ከሚተዳደረው የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ነው።

በምርምርና በፈጠራ ባለሙያዎቹ የመፍትሔ ሐሳብ የቀረበው በእናቶች እና ህፃናት እንዲሁም በአርብቶ አደሮች ዘንድ የጤና ችግሮች ተብለው በተፈረጁት ላይ ነው። 

በሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተጠቆመው ለእነዚህ "ምላሽ መስጠት ያስችላሉ" የተባሉ 42 ሳይንሳዊ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡

ለሙከራ የተግባር ምዕራፍ ለማሸጋገር በቅድሚያ ከተመረጡት ጥናቶች መካከል በእናቶችና ህፃናት እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት እንዲሁም ሁለት የአርብቶ አደር አካባቢ የጤና ችግሮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ታውቋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ እንዳሉት፤ በአገሪቷ ጤና ዘርፍ በቅድሚያ መፈታት የሚገባቸውን ችግሮች በመለየት ተመራማሪዎችና የፈጠራ ሰዎች መፍትሄ እንዲያፈላልጉ ይበረታታሉ።

በአገሪቷ በአሁኑ ወቅት በአርብቶ አደሩ አካባቢ፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና መሻሻል ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በለያቸው የጤና ችግሮች ተመራማሪዎች የምርምር ውጤታቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያጋጥማቸውን የገንዘብና የመሳሪያ ችግር ለመፍታት የፕሮጀክት ስምምነቱ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱን የመጀመርያ ምዕራፍ ስራ ወደ ተግባር ለማስገባት 22 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ያለባቸውን የዕውቀት፣ የልምድና የክህሎት አቅም በማሳደግና ተጠቃሚ በማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው እምነታቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

በጤና ችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ ያቀረቡና ያስመረጡ ግለሰቦች እያንዳንዳቸው 300 ሺ ብር ይሸለማሉ።

ሙከራው ውጤታማ ከሆነ እያንዳንዱ ተመራማሪ የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ይኖረዋል።

በመጨረሻም የሙከራ ውጤቱ ወደ ተግባር ምዕራፍ ሲሸጋገር ደግሞ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር እንደሚያሸለሙ ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ደሴ ሰኔ 29/2009 የወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ከ10 ሺህ በላይ የአከባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር አነጋገረኝ ጋሻው እንደገለጹት የማህበረሰብ አገልግሎቱን የሰጠው በግብርና፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በትምህርት ዘርፎች ነው።

በተለይም በዘር ብዜትና ዝርያ ማሻሻል፣ በካንሰር ምርመራ፣ በሰላም ግንባታ፣ በፍትህ ተደራሽነትና በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል እገዛ እያደረገ ይገኛል።

በዚህም እየተጠናቀቀ በሚገኘው በጀት ዓመት ከ10 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የማህበረሰብ አገልግሎት ስራው ውጤታማ ለማድረግ ከደሴ ከተማ አስተዳደር፣ ከደቡብ ወሎና ኦሮሞያ ልዩ ዞኖች ጋር ስምምነት መስርቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ናቸው።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማሩና ከምርምር ስራቸው ጎን ለጎን በየአከባቢያቸው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሰሩ በተቀመጠው ግብ መሰረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ ዩኒቨርሲቲው ከደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ጋር በመተባበር ባካሄደው የቅድመ ካንሰር ምርመራ በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት ከ3 ሺህ በላይ የአካባቢው እናቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በማህበረሰብ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አህመድ ሙስጠፋ እንደገለጹት በዚህ ዓመት በዩኒቨርሲቲው የቀረበላቸው የጤፍ ምርጥ ዘር ተጠቅመው የተሻለ ምርት ለማግኘት በመስራት ላይ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደምም ቁንጮ የተባለውን የጤፍ ዝርያ ጨምሮ የተያየ ምርጥ ዘር በማምጣት እርሳቸውንም ሆነ ጎረቤቶቻቸው ምርታማነታቸው እንዲያድርግ እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ባካሄደው ነጻ የጡት ካንሰር ምርመራ ተጠቃሚ የሆነችው ወጣት ራሂመት ሰይድ በበኩሏ በተሰጣት ምርመራ ራሷን እንድታውቅ ከማድረጉም በላይ ስለ በሽታው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራት ማድርጉን ገልፀዋል፡፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በዚህ አመት በ10 ሚሊዮን ብር በጀት የተለያዩ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ሲያከናውን መቆየቱን ከዩኒቨርሲቲው የተገኙ መረጃዎች ያመላክታል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2009 የአፍሪካ ህብረት ላቀደው የኢኮኖሚ ውህደት ኢትዮጵያ አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኗን የህብረቱ ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።

በተጠናቀቀው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተሳታፊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና አህጉራዊ ተቋማት ወኪሎች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝምን ረጅም ጊዜ አንስቶ ስታቀነቅን የቆየች አገር በመሆኗ ለኢኮኖሚያዊ ውህደቱም ጥረቷ የሰፋ ነው።

የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና መሃመድ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የዘመነች አፍሪካን መፍጠር የሚቻለው "አገሮች በራቸውን ለእርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ዝግጁ ሲያደርጉና ከተጽዕኖ የሚያላቅቁ ስራዎችን መስራት ሲችሉ ነው" የሚል ሃሳብን ከረጅም ጊዜ አንስቶ ስታቀነቅን ቆይታለች።

"ኢትዮጵያ የተባበረችና አንድ አፍሪካን መፍጠር የሚቻለው ደግሞ አመቺ መሰረተ ልማቶች ሲዘረጉ ነው የሚል አቋም አላት። በዚህ ረገድ  የኤሌትሪክ ኃይል ልማትና ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን በሰፊው እያስፋፋች ነው'' ብለዋል።

"ከምስራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር በንግድ የሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማቶችን ኢትዮጵያ በማካሄድ ላይ ናት" ያሉት ውጭ ጉይይ ሚኒስትሯ፤ ከኬንያም ጋር በመንገድና በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር መስራቷንም ተናግረዋል።

የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ቢዝነስ ምክር ቤት ሊቀመንበር ዶክተር አማኒ አስፎር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ለያዘው የኢኮኖሚ ውህደት ከጎረቤት አገሮች ጋር ማስተሳሰር የሚያስችላትን የንግድ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ መሆኗ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ ከየትኛውም ዓለም ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ እምቅ የተፈጥሮ ማዕድናትና ሌሎች ሃብቶች ባለቤት ብትሆንም "ለዘመናት ለቅኝ ገዢዎች በተመቸ መንገድ ጥሬ ዕቃዎችን ስትልክ ቆይታለች" ብለዋል።

"አፍሪካ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ችግር ያለባት አህጉር በመሆኗ የአባል አገራቱ የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ከ10 በመቶ በታች አድርጎታል'' ሲሉም አውስተዋል።

''ከዓለማችን 287 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ንግድ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ ከ22 ቢሊዮን ዶላር እንዳይበልጥ አድርጎታል" ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ዶክተር አንቶኒ ሞቴ ማሩፒንግ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ የወጪ-ገቢ ምርቶች ንግድ በየዓመቱ እድገት በማሳየት ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ላለፉት 10 ዓመታት በአማካይ 623 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ወደ ውጭ አገሮች ልካለች።

"ኢትዮጵያ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሰጠችው ትኩረት  ከጎረቤት አገሮችና ከሌሎች የአለም ገበያዎች ጋር ያላትን ትስስር አሳድጎታል" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የተጀመሩና በቀጣይ ለመገንባት የተያዙ የመሰረተ ልማት እቅዶች የንግድ ትስስሩን የበለጠ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ አፍሪካ እንደ አንድ አህጉር ዕውነተኛ ህብረት ሊኖራት የሚችለው "በመሰረተ ልማት እርስ በርስ መተሳሰር ስንችል ነው" የሚል አቋም አላት።

በዚህ መሰረትም አፍሪካዊያን ቅኝ ገዥዎች ካሰመሩልን ድንበር አልፈን የተሳለጠ የእርስ በርስ ንግድ ማካሄድ የሚያስችል መሰረተ ልማት መዘርጋት የህልውና ጉዳይ መሆኑ እንደ አቋም መወሰዱን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ  ውህደት ማሳካት የሚያስችል መሰረተ ልማት እያካሄደች መሆኗንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን ጋር በሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች አማካኝነት ጠንካራ የኢኮኖሚና  ማህበራዊ ትስስር ለመፍጠር የረጅም ጊዜ እቅድ ይዛ በመንቀሳቀስ ላይ ስትሆን፤ የቴሌኮሙንኬሽን፣ የመንገድ፣ ባቡርና አየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች።

29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤውን በኢትዮጵያና በህብረቱ የፖለቲካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለአንድ ሳምንት ሲመክር መቆየቱ ይታወሳል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ