አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 05 July 2017

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2009 መንግስት የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሚያደርገውን ጥራትን የማስጠበቅ እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ አባላትን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የቦርድ አባላቱ ድርጅቱ የአገሪቱን ምርቶች ጥራት ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ጥረትና በአህጉሪቷም ታዋቂ ለመሆን ያለውን ራዕይ በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጻ  አድርገዋል።

ከቦርድ አባላቱ መካከል ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ መንግስት ለድርጅቱ እስካሁን ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምም በሰጡት ምላሽ፤ መንግስት ለድርጅቱ የቅርብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን ፕሮፌሰር አበበ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተመሰረተው ይህ ድርጅት እስካሁን በአራት ዙሮች ለ211 ድርጅቶች የጥራት ሽልማት ሰጥቷል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቴድሮስ መብራቱ  እንደገለጹት፤ የድርጅቱ ዓላማ የጥራትን ጽንሰ ሃሳብ በሕብረተሰቡ፣ በአምራቾች፣ በአገልግሎት ሰጪዎችና በግንባታ ዘርፍ በተሰማሩት ዘንድ ማስረጽ ነው።

ይሁን እንጂ እስካሁን በደርጅቶች ረገድ ያለው የመወዳደር ስሜት የታሰበውን ያህል ባለመሆኑ ይህንን ችግር ለመፍታት "ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተካሄደው ውይይት እገዛ ያደርጋል" ብለዋል።

ድርጅቱ በቀጣዩ ነሐሴ መጨረሻ  63 ድርጅቶችን በአምስተኛ ዙር የጥራት ደረጃ ተሸላሚ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2009 የፌደራል ከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በስራቸው ጥሩ አፈጻጸም ላሳዩ ሰራተኞችና ተቋማት እውቅናና ሽልማት ሰጠ፡፡

ኤጀንሲው ከዘጠኙ ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ  አስተዳደሮች ጥሩ አፈጻጸም ላሳዩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማትና ባለሙያዎች ነው እውቅናና ሽልማቱን  የሰጠው።

በአገሪቱ  ከሚገኙ 1ሺ 371 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት መካከል በአፈጻጸማቸው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ 60 ማዕከላት እና 60 ባለሙያዎች ተመርጠዋል።

ለ60ዎቹም ማዕከላት የእውቅና የምስክር ወረቀት የተሰጠ  ሲሆን፤ ከ60ዎቹ መካከል ኤጀንሲው ያስቀመጠውን የአንድ መስኮት አገልግሎት በላቀ ሁኔታ ያሳኩ  አስር ማዕከላት ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ፕሪንተር እንዱሁም 25 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች እያንዳንዳቸው  አንድ ዴስክ ቶፕ  ኮምፒውተር አግኝተዋል።

ጥሩ አፈጻጸም ያሳዩ  ግንባር ቀደም ባለሙያዎችም የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

ማዕከላቱ በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በተለይም የንግድ ፈቃድ፣ የብድር አገልግሎት፣ 'የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር' እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ከአንድ ቦታ የሚያስገኙ ናቸው።

ከትግራይ ክልል ኮረም ከተማ የመጡት አቶ ኃይለመስቀል ባራክ እንደገለጹት፤ ለግንባር ቀደም ፈጻሚዎችና ማዕከላት የእውቅና ሽልማት መስጠቱ የበለጠ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ያነሳሳቸዋል

አቶ ኃይለመስቀል አክለውም ኤጀንሲው ከእውቅና ሽልማት በተጨማሪ ማዕከላቱ ያለባቸውን የመስሪያ ቁሳቁስ ችግር ከክልሎች ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ከደቡብ  ብሄሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የመጡት ወይዘሮ የምስራች ማሞ  "ዘርፉን ለመለወጥና ተገልጋዩን ለማርካት ባለሙያዎች ላይ መስራትን ይጠይቃል፣ ኤጀንሲውም ይህንን በመገንዘብ ለባለሙያው እውቅና መስጠቱ ተጨማሪ የቤት ስራ እንደመስጠት ነውና ሊቀጥልበት ይገባል" ብለዋል።

የፌደራል ከተሞች ስራ ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ጌታቸው እንደገለጹት፤ በአገሪቱ ያሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተመሳሳይ አቅም እንዲኖራቸው  የባለሙያዎች ስልጠናና  የልምድ ልውውጥ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው።

በየማዕከላቱ የሚስተዋሉ የግብዓት ችግሮችን ለመፍታት ከክልሎች የዘርፉ ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2009 በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ ውስጥ የኢንዶስኮፒ ህክምና ማሰልጠኛ ማዕከል ተከፈተ።

የሥልጠና ማዕከሉ የተከፈተው ከጃፓኑ ፉጂ ፊልም ኩባንያ እና ከጃፓን ኤምባሲ በተገኘ የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ነው።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ የህክምና ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ብርሃኔ ረዳኤ እንዳሉት ማዕከሉ በአገሪቷ ያሉትን ውስን የጨጓራ፣ የጉበት እና የሆድ እቃ ሀኪሞች ቁጥር ለመጨመር አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ማዕከሉ በዓመት 20 ለሚሆኑ የኢንዶስኮፒ ሐኪሞች አጫጭር ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል አቅም አለው ነው የተባለው።

ዶክተር ብርሃኔ እንደተናገሩ ፤ ህሙማን በባለሙያ እና በህክምና እቃዎች እጦት ከሩቅ ቦታ ወደ ህክምና ኮሌጁ በመምጣት ለእንግልት ይጋለጣሉ።

የጨጓራ፣ የጉበት እና የሆድ ዕቃ በሽታዎች ችግር ያለባቸውና እንዲሁም የካንሰር ህሙማንን ለማከም የማዕከሉ መከፈት በጣም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ። አጫጭር ስልጠናዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርገም ተጠቁሟል።

የፉጂ ፊልም የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ እውነቱ እንዳሉት፤ ኩባንያው በተለያዩ ተቋማት የሕክምና ባለሙያ ማሰልጠንና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።

ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ የጨጓራ፣ የጉበት፣ የሆድ ዕቃ እና ሌሎች በሽታዎች ህክምና የሚሰጥ ህንጻ በመንግስት በጀት እያስገነባ ነው።

ከሁለት ዓመት በኋላ የሚጠናቀቀው ይህ ህንጻ በአገሪቷ ዘመናዊ  አገልግሎት የሚሰጥበት ማዕከል እንደሚሆን ተጠቁሟል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2009 የአፍሪካ ህብረት ለኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች የሰጠው ዕውቅና ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሥርዓትና ጊዜ ለአፍሪካውያን ታማኞች መሆናቸውን ያረጋገጠበት ውሳኔ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ29ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መጠናቀቅ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አፄ ኃይለሥላሴ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከአቻ አፍሪካዊ መሪዎች ጋር ባደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ትናንት ምሽት በተጠናቀቀው የ29ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ አወድሷቸዋል።

በሌላ በኩል ኅብረቱ እንዲጠናከርና በአህጉሪቷ የሚቀሰቀሱ ግጭቶች እንዲፈቱ በግላቸው ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ  ኅብረቱ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል።

የታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ሽግግር እንዲያደርግ ለተጫወቱት የመሪነት ሚናም ኅብረቱ እውቅና ሰጥቷል

ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት /ኔፓድ/፣ የአፍሪካ  እርስ በርስ መገማገሚያ መድረክ እንዲመሰረትና በ1998 ዓ.ም በዴንማርክ መዲና ኮፐንሃገን በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ አፍሪካን በመወከል ላደረጉት አስተዋጽኦ ህብረቱ እውቅና ከሰጠባቸው ምክንያቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ጎን ለጎንም አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮች በአንድ ድምፅ የጋራ አቋም በመያዝ ተቀባይነቷና ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ ላደረጉትን ግለሰባዊ አስተዋጽኦ አመስግኗል። 

ይህንንም ከግምት በማስገባት ኅብረቱ ለአጼ ኃይለሥላሴና አቶ መለሰ ዜናዊ በኅብረቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ኃውልት እንዲቆምላቸው ትናንት ውሳኔ አሳልፏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደገለጹት፤ በስብሰባው የታደሙ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና ተወካዮች ኢትዮጵያ ላለፉት 54 ዓመታት ስብሰባውን በተሳካ መልኩ ማካሄዷን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ለትናንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና ለዛሬው የአፍሪካ ኅብረት ዓላማዎች መሳካት በታማኝነት ኃላፊነታቸውን እንደተወጡም መሪዎቹ መግለጻቸውን ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።

የመዲናዋ ነዋሪ ከልጅ እስከ አዋቂ ከፀጥታ አስከባሪው ጋር በመተባበር ኅብረቱ የሚያካሂዳቸው ስብሰባዎች ያለ ምንም ችግር እንዲጠናቀቁ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በተጠናቀቀው 29ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ስብሰባ ለሁለቱም የአገሪቷ መሪዎች የመታሰቢያ ኃውልት እንዲቆምላቸው መወሰኑ "ለመላው ኢትዮጵያዊ ሽልማት ነው" ብለዋል

አዲስ አበባ ለአፍሪካውያን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ መዲናነት የህዝቦቿ ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ መለስ "አፍሪካዊያን ለቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች የሰጡት ዕውቅና  የዛሬውና የነገው ትውልድ ለአፍሪካ ተጨማሪ የቤት ስራዎችን እንዲሰራ ያነሳሳል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ይህን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ያላሳለሰ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ለወደ ፊቱም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።

Published in ፖለቲካ

                       ትንሳኤ ገመቹ (ኢዜአ)

"በወጣቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ለአንድ ሳምንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው 29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

በዚሁ ጉባኤ ላይ  ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ 24 የኅብረቱ አባል አገሮች መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የመሪዎቹ ስብሰባ በህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት፣ በህብረቱ የወቅቱ ሊቀ መንበር አልፋ ኮንዴ፣ በመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሃመድ እንዲሁም በፍልስጤሙ መሪ ሙሐሙድ አባስ  ንግግር ነበር የተጀመረው።

በአህጉሪቷ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ ግጭቶችን በራስ አቅም መፍታት፣ የማዕከላዊ አፍሪካ፣ የደቡብ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ የኤርትራና ጂቡቲ ወቅታዊ ጉዳይ፣ የወጣቶች ተጠቃሚነትና ህገ ወጥ ስደት እንዲሁም የህብረቱን የፋይናንስ አቅም ማጠናከር የህብረቱ ዋነኛ ማጠንጠኛዎች ነበሩ።

ለመሆኑ 29ኛው የህብረቱ የመሪዎች ስብሰባ  ምን ዓይነት አዳዲስ ክስተቶች ተስተናገዱበት?

29ኛው የመሪዎቹ ስብሰባ የህብረቱን ኋላ ቀር አሰራር ለማስቀረት በጀመረው የለውጥ ትግበራ ላይ ቁርጠኛ አቋም ይዞ መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ይናገራሉ።

ቀደም ሲል በመሪዎቹ ስብሰባ በርካታ ጉዳዮች በሰፊው ውይይት ሳይደረግባቸውና ሳይፈተሹ ውሳኔ ሲተላለፍባቸው እንደነበር ያስታውሱት አቶ ኃይለማርያም፤ ይህም "በውሳኔዎቹ አፈጻጸም ላይ ክፍተት ፈጥሯል" ብለዋል።

ይህን አሰራር ለማስቀረትም  በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ መሪነት  ታዋቂ የአፍሪካ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የህብረቱን የለውጥ አጀንዳ ሲያጠና ቆይቷል።

ባለፈው ጥር 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የህብረቱ 28ኛ ስብሰባ የለውጥ አጀንዳው ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቷል።

የለውጥ አጀንዳው ካስቀመጣቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ደግሞ መሪዎቹ የተመረጡ ጉዳዮች ላይ ብቻ የበሰለ ውይይት አድርገው ውሳኔዎችን ማሳለፍ አፈጻጸማቸውንም መገምገም ነው።

በዚህ መሰረት ባለፈው ጥር አዲስ አበባ በተካሄደው የመሪዎቹ ስብሰባ የተመረጡ ዋና ዋና ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን አቶ ኃይለማርያም አስታውሰዋል።

የወጣቶች ተጠቃሚነት፣ ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የህብረቱ የበጀት ጉዳይ በወቅቱ ከተነሱ የተመረጡ ጉዳዮች ዋነኞቹ ነበሩ።

29ኛው የመሪዎቹ ጉባኤም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በየአገሮቹ  የነበረው አፈጻጸም ላይ ትኩረት አድርጎ መክሯል። 

በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግና የወጣቶቹን አቅም መጠቀም እንዲቻል ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ወደ ተግባር መግባታቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በጥልቀት በመታደስ እንቅስቃሴ ውስጥ ከያዘቻቸው አጀንዳዎች አንዱ የወጣቶችን የኢኮኖሚ  ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው የሚሉት አቶ ኃይለማርያም፤ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በ29ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ኢትዮጵያ የወጣቶችን በኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ ከሌሎች አገሮች ልምድ የወሰደችበት እርሷም ልምዷን ያካፈለችበት መሆኑን ነው ያብራሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት "ቀደም ሲል የህብረቱ አባል አገሮች መሪዎች ብዙ ሃሳቦችን በማንሳት በሃሳቦቹ ላይ በቂ ውይይት ሳያደርጉ የሚያሳልፉት ውሳኔ የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ቆይቷል።"

ከብዛት ጥራት እንደሚባለው በ29ኛው የመሪዎቹ ጉባዔም ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮችን ብቻ በመምረጥ ለጉዳዮቹ  ጊዜ ሰጥቶ መወያየትና አፈጻጸማቸውንም የመገምገም አሰራር የተጀመረበት መሆኑ ከቀደምቶቹ ስብሰባዎች ለየት ያደርገዋል።

በዚሁ የመሪዎች ጉባኤ  አህጉራዊ  አጀንዳዎችን በፍጥነት ለመፈጸም እንዲሁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ  ትስስሮችን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች አሳልፏል።

ጉባኤው በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ መሰረታዊ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን፤ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ የቡሩንዲ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ የሊቢያና ሌሎች አሕጉራዊ ሰላምና ደህንነት ጉዳይም ትኩረት ተሰጥቶታል።

በአህጉሪቷ የጋራ ነጻ የንግድ ቀጣና ለመፍጠር የተገቡ ስምምነቶች ትግበራ ላይም ውይይት ተደርጎ ውሳኔዎች ተላልፈውበታል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ተላቀው ነጻነታቸውን እንዲያውጁ ያደረገችው አስተዋጽኦ፤ በዚሁ የመሪዎች ጉባዔ ከአፍሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነትና አክብሮት ተችሮታል።

ከቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ ህብረቱ ምስረታ የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ እንደነበር የአፍሪካ መሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ለዚህም ነው በ29ኛ ጉባኤ የአፍሪካ  መሪዎች ለእነዚህ ታላላቅ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች በህብረቱ ቅጥር ግቢ የማስታወሻ ሐውልት እንዲቀመጥላቸው የተስማሙት።

በተለይም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች አፍሪካን ወክለው ያሰሙት ድምጽ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ተሰሚነት እንዲጨምር አድርጎታል።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም  ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረትና ለአፍሪካውያን አንድነት ባበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና መሰጠቱ ለአፍሪካውያን ያሳዩት የማይናወጽ አቋም ምስክር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ህብረቱ ለመሪዎቹ የሰጠውን ዕውቅና "ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ደርጅት እስከ ህብረቱ መመስረት ለአፍሪካ አጀንዳዎች ቅድሚያ የምትሰጥ፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ዕድገትና ብልጽግና ሌት ተቀን የምትሰራ አገር መሆኗን የሚያሳይ ነው" ብለውታል።

ህብረቱ ለቀድሞው የኢትዮጵያ መሪዎች የሰጠውን ዕውቅና ተከትሎ ቀጣዩ ትውልድ በመሪዎቹ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ የሚሄድ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የህብረቱ ልዩ ክስተት የሆነው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ህብረቱን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ ኃላፊነትን ከራስ መጀመርን ያሳዩበት መንገድ ነው። ፕሬዝዳንት ሙጋቤ 300 ከብቶቻቸውን ሸጠው ያገኙትን አንድ ሚሊዮን ዶላር ቼክ ለኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ማስረከባቸው በተጠናቀቀው የ29ኛው ጉባኤ ላይ አነጋጋሪ ጉዳይ  ሆኖ አልፏል።

ባለፈው ጥር 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው 28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የኅብረቱ ኮሚሽነር፣ ምክትል ኮሚሽነርና የስምንት ኮሚሽነሮች ምርጫ ተካሂዷል።

ሆኖም የኅብረቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች እና የሰው ሃብት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽነርነት ለመወዳደር የቀረቡት ዕጩዎች የሚጠበቀውን ድምጽ ባለማግኘታቸው ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

በ29ኛው ጉባኤ  በተካሄደ ምርጫ የኢኮኖሚክ ጉዳዮች ኮሚሽነርነት ቦታ ላይ ለመወዳደር ከቀረቡት የሶስት አገር ዕጩዎች መካከል ማዳጋስካራዊው ቪክቶር ሃሪሰን እንዲሁም ለሰው ኃብት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽነርነት ከቀረቡት ሁለት ተወዳዳሪዎች መካከል ካሜሮናዊቷ ሳራህ አያንግ አግቦር አሸናፊ ሆነዋል።

ባለፈው ስብሰባ ከህብረቱ የቀድሞ ኮሚሽነር ከዶክተር ዲላሚኒ ዙማ ስልጣን የተረከቡት ቻዳዊው ሙሳ ፋቂ መሃማት "የተሰጠኝ ኃላፊነት ትልቅ እንደመሆኑ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ" ማለታቸውም የማይዘነጋ ነው።

ሊቀመንበሩ ስልጣናቸውን ከተረከቡ ከሶስት ወራት ተኩል በኋላ በህብረቱ 29ኛ ጉባዔ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ስልጣናቸውን ከተረከቡ ጥቂት ጊዜ ቢሆንም  የአፍሪካን ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት ከአገራት መሪዎች ጋር በቅርበት ለመስራት ጥረት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

ህብረቱን ለአንድ ዓመት በሊቀ መንበርነት የመሩት የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ሊቀ መንበርነታቸውን ለጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ማስረከባቸው እንዲሁም፤ ሞሮኮ ከ 33 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አፍርካ ህብረት አባልነት ዳግም መመለሷም የጉባዔው ሌላ ገጽታ ነበር።

በ29ኛው ጉባኤ የጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ የስልጣን ዘመናቸውን በመጭው ጥር 2010 ዓ.ም የሚያጠናቅቁ ሲሆን፤ በ30ኛው የህብረቱ ጉባኤ ላይ ለሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ ያስረክባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተለይም ከብዛት ወደ ጥራት ለመሸጋገር ውስን አጀንዳዎችን መምረጡ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። በህብረቱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ዳር እንዲደርሱና በ2063 በኢኮኖሚ የተሳሰረችና የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር የተያዘው ግብ እንዲሳካ የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች በተናጠልም ሆነ በጋራ የጀመሯቸውን ጥረቶች አጠናክረው መቀጠል ግድ ይላቸዋል።

Published in ዜና-ትንታኔ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2009 ከሳዑዲ ዓረቢያ የተመለሱት ስደተኞች በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተደረገላቸው ቀልጣፋ አገልግሎትና አቀባበል መደሰታቸውን ገለጹ።

500 የሚሆኑ የክረምት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የሳዑዲ ተመላሾችን በመቀበል ላይ ይገኛሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ከስደት ተመላሾች በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተደረገላቸው አቀባበልና ድጋፍ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ ይህም ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው የተናገሩት። 

ከተመላሾቹ መካከል ወይዘሪት ትዕግስት ኃይሉ እንደገለጸችው፤ ወጣቶቹ ለተመላሾቹ ያለምንም ክፍያ እያደረጉት ያለው እገዛ እጅግ የሚያስደት ነው።

''ቦሌ እንደገባሁ በወጣቶቹ ያለምንም ክፍያ እቃዬን እስከምፈልግበት ቦታ ድረስና የምፈልገውን አገልግሎት በቀላሉ እንዳገኝ ረድተውኛል፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ'' ብላለች።  

ሌላኛው የሳዑዲ ተመላሽ አቶ ሱልጣን አበራ ''ወጣቶቹ ሻንጣ ከመፈለግና ከማገዝ ጀምሮ ቤተሰቦቼን እንዳገኝ ስልክ በማስደወል አስፈላጊ የሆነ አቀባበል አድርገውልኛል’’ ብለዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ በአየር መንገዱ ውስጥ ትብብር በሚያስፈልግ ነገር ሁሉ ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገረው ደግሞ ሌላኛው ከሳዑዲ ተመላሽ ወጣት መብራቶም ጥላሁን ነው። 

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በየዓመቱ በክረምት ወራት በተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰማሩ ሲሆን፤ በዚህም ዓመት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሳዑዲ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን የመቀበል ሥራ ላይ ተጠምደዋል።

ወጣቶቹ በቀንና በማታ መርሃ-ግብር በመከፋፈል ከስደት ተመላሾችን በመቀበል፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት እና የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራን እያከናወኑ ይገኛሉ።

ወጣት ሕብስቱ አራጋው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው ከሳዑዲ ወደ አገራቸው ለሚመለሱት አገልግሎት ከሚሰጡ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። 

ወጣቱ ከስደት ለሚመለሱት ዜጎች ማንኛውንም አገልግሎትና ድጋፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጿል።

ስልክ በማስደወል ብሎም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እስከሚገናኙ ማረፊያ ቦታ በማዘጋጀትና ሌሎች የሚፈልጉትን እገዛ እያደረጉ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ይመር ተሾመ  ነው።

በሳዑዲ አረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ከ450 ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን የሚገኙ ሲሆን፤ ወደ አገር ቤት የተመለሱት ከ50 ሺ እንደማይበልጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ወደ አገራቸው ለመመለስ የተመዘገቡና የጉዞ ሰነድ የወሰዱት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር 110 ሺ መድረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን በበኩሉ ከአዲስ አበባ የወጣት አደረጃጀት የተውጣጡ ወደ አምስት መቶ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሥራ መጀመራቸውን ገልጿል።

የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር እንደገለጸው፣ ወጣቶቹ ሥራቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲያከናውኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በቅንጅት የሚሰራበት ሁኔታ ተከናውኗል።

ፌደሬሽኑ የበጎ ፈቃደ አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ለመስጠት ከወጣቶቹና ከባለድርሻ አካላት ጋር ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራም ጠቁሟል።

ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በአጠቃላይ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ላይ እንደሚሳተፉ መረጃዎች ያመለክታሉ።  

Published in ማህበራዊ

ሶዶ ሰኔ 28/2009 በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተገነቡ የመለዋወጫ ቁሳቁስ ማምረቻ አነስተኛ ኢንዱስትሪ ማዕከላት ክፍተት እንዳለባቸው ተመለከተ፡፡

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በወላይታ ሶዶ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የቢሮው  ምክትል ኃላፊ አቶ አሼቦ ኡሊሶ እንደገለጹት ማዕከላቱ  ኢንዱስትሪው መሪነቱን እንዲይዝ ለተጣለው ግብ  መሳካት ብሎም  ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ጭምር የተገነቡ ናቸው፡፡

የመለዋወጫ ቁሳቁስ ማምረቻ አነስተኛ ኢንዱስትሪ ማዕከላቱ የተገቡት "ፍሌክሴብል ማኑፋክቸሪንግ " በሚል ስያሜ ከሶስት ዓመታት በፊት ከ195 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ ሀዋሳ ፣ ሆሳዕና ዲላ ፣ ወላይታና አርባምንጭ ከተሞች ውስጥ ነው፡፡

ማዕከላቱ ባለፈው ዓመት ተመርቀው ወደ ስራ ቢገቡም የአሰራር ፣ የመመሪያ ግልጽነት ማጣትና በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች የአመለካከት ክፍተት በመኖሩ እንደሚፈለገው ውጤታማ እንዳልሆኑ ነው የቢሮው  ምክትል ኃላፊ ያመለከቱት፡፡

ጥራት ያለው ምርት አምርተው በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ የክህሎት ጉድለት እንዳለም ተጠቅሷል፡፡

በዘርፉ ለመሰማራት በማህበር ለተደራጁ አንቀሳቃሾች አቅም ቀጣይነት ባለው መልኩ  ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ከመከላከያ ኢንጅነሪንግ  ጋር የእውቀት ሽግግሩን የሚያፋጥኑ የስልጠና ፕሮግራሞች ማመቻቸታቸውንም አመልክተዋል፡፡

ከዲላ መምበኣ ፍሌክሴብል ማኑፋክቸሪንግ ማዕከል የመጣው ወጣት ዘርሁን ጄጎ "ቢሮው የዘርፉን ተግዳሮት በጥናት አስደግፎ ማወያየቱ ቢዘገይም ችግሩን ለመፍታት ያስችላል "ብሏል፡፡

ወጣቱ እንዳለው ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች ተቋማት ጋር ተቀናጅተው ለመስራት ጥረት ቢያደርጉም የገበያ ትስስር ያለመፈጠሩ፣ የግብአትና የእውቀት ክፍተት መኖሩ ውጤታማ አላደረጋቸውም፡፡

ትላልቅ ስራዎችን መወጣት የሚችሉ ማሽኖች ቢኖሯቸውም በተገቢው ለመንቀሳቀስ ችግር እንዳለባቸው የተናገረው ደግሞ የሆሳዕና ፍሌክሴብል ማኑፋክቸሪንግ ማዕከል አክዮሲን ማህበር ተወካይ ወጣት ሊሬ ዲላሞ ነው፡፡ 

የገበያ ትስስር ያለመፈጠሩና የገንዘብ እጥረት ውጤታማ እንዳይሆኑ ወጣቱ የጠቀሳቸው ችግሮች ናቸው፡፡

በሀገሪቱ ካሉት 37 ማዕከላት መካከል አምስቱ በደቡብ ህዝቦች ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2009 በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሐምሌ ቅጽበታዊና ጎርፍ የሚያስከትል ዝናብ ሊጥል ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደርግ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አሳሰበ።

በተያዘው ክረምት አብዛኞቹ የአገሪቷ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ኤጀንሲው ለኢዜአ የላከው የአየር ትንበያ መረጃ ያመለክታል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅና ሰሜን ሸዋ፣ አዲስ አበባ፣ አርሲና ባሌ ዞኖች፣ ጋምቤላ፣ ትግራይ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም በአማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ ባህር ዳር ዙሪያ፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ሀድያና ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ወላይታና ደቡብ ኦሞ ዞኖች፤ ከፋና ቤንች ማጂ በአብዛኞቹ ቦታዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊጥል እንደሚችል የኤጀንሲው ትንበያ ያመለክታል ።

በአንዳንድ ቦታዎች  "ቅጽበታዊ፣ ነጎድጓዳማና በረዶ አዘል ከባድ ዝናብ ያለማቋረጥ ሊዘንብ ይችላል" ያለው ኤጀንሲው፤ ኅብረተሰቡ ከወዲሁ አስፈጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።

በአንፃሩ በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብና በምስራቅ ሐረርጌ፣ በጅጅጋና ሲቲ ዞን፣ በድሬዳዋ፣ በሐረሪ፣ በአፋር ክልል ዞኖች 1፣3፣4 እና 5 በአብዛኛው መደበኛና አልፎ አልፎ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊጥል እንደሚችል ጠቁሟል።

በቀሪዎቹ የአገሪቷ አካባቢዎች በአብዛኛው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ሊያመዝን እንደሚችል የኤጀንሲ ትንበያ ያስረዳል።

መኸር አብቃይ በሆኑና ዘር መዝራት ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች ሰፊ የእርጥበት ስርጭት ስለሚኖር ለሰብል እድገት መልካም ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው የገለጸው።

ኤጀንሲው በመግለጫው እንዳመለከተው፤ ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚጥልባቸው አካባቢዎች በቡቃያ ደረጃ የሚገኙ ሰብሎች እንዳይጎዱ የማንጠንፈፊያ ቦዮችንና የጎርፍ መከላከያ እርከኖችን ማጠናከር ያስፈልጋል።

የክረምት ዝናብ በሚያገኙ የዓባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ተከዜ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛውና መካከለኛው አዋሽ፣ የላይኛው ዋቢ ሸበሌ፣ የላይኛው ገናሌዳዋ ወንዞች አካባቢዎች ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊኖር ስለሚችል ኅብረተሰቡ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ኤጀንሲው አሳስቧል።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2009 አፍሪካ ከውጭ ተፅዕኖ ተላቃ በፋይናንስ ራሷን እንድትችልና አጀንዳ 2063ን እንድታሳካ ሁሉም አባል አገሮች የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የ29ኛው የሕብረቱ ጉባዔ ተሳታፊዎች ጥሪ አቀረቡ።

በአጀንዳ 2063 ከተያዙት ጉዳዮች መካከል በአህጉሪቷ 70 በመቶ የሚሆነውን ወጣት የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታትም አገሮቹ ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ተሳታፊዎቹ ያሳሰቡት።

በዚህም ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ አገሮች የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብሮችን በመቅረጽ  ለአህጉሪቷ የተሻለ ዕድገት  ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አመልከተዋል።

በአፍሪካዋ መዲና አዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የ29ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ትናንት ተጠናቋል።

በጉባዔው ተሳታፊ የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኦውገስቲን ፕ.ማሂጋ በስብሰባው "መሪዎች በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መክረው ውሳኔዎችን አሳልፈናል" ነው ያሉት።

የመጀመሪያውና በዋናነት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ አፍሪካ በፋይናንስ ራሷን እንድትችልና ከውጭ ተፅዕኖ እንድትላቀቅ  ለማድረግ የተካሄደው ውይይት መሆኑን ገልጸው፣ "እርሱም ፍሬያማ ነበር" ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ ደግሞ ሁሉም አገሮች በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ዶክተር ማሂጋ ገልጸው፤ "አገራቱ ያላቸውን ሃብት በማልማትና ለሕብረቱ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ የሚያደርጉ ከሆነ አህጉሪቷን ከውጭ ተፅዕኖ ማላቀቅ ይቻላል" ብለዋል።

ከአፍሪካ ሕዝብ 70 በመቶው በላይ የሆነውን ወጣቱን ኃይል ለማብቃት አገሮቹ ጥራት ያለውን ትምህርት በማዳረስ አምራች የሆኑ ወጣቶችን ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው ዶክተር ማሂጋ ገልጸዋል።

በዚህም ወጣቶቹ በመንግሥት፣ "አሊያም በግል ዘርፍ በተለያዩ ሥራዎች  በመሰማራት የኢኮኖሚውን ዘርፍ እንዲደግፉ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።

ከአጀንዳ 2063 እቅዶች መካከል የአንዳንዶቹ አፈጻጸም ውጤታማ አለመሆን የፋይናንስ እጥረቱ ዋና ምክንያት መሆኑን አንስተዋል.

መቀመጫውን ዚምባብዌ ያደረገው የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር አማኑኤል ናዶዜ እንደሚሉት፤ የአፍሪካ ሕብረት የፋይናንስ እጥረት ገጥሞታል። ይህ ደግሞ አህጉሪቷ ለረጅም ጊዜ በሌሎች የውጭ ተፅዕኖ ስር እንድትወድቅ አድርጓታል።

ጉባዔው መጠናቀቁን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ እያንዳንዱ አገር ከገቢ ዕቃ ታሪፍ ውስጥ ዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶ ሰብስቦ እንዲያስገባ የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጻ፤ አገራቱ በዚህ ቢስማሙም በተለያዩ ምክንያቶች አፈጻጸሙ  ላይ ክፍተት አለ።    

የሕብረቱን የፋይናንስ ምንጭ በተመለከተ ባለፈው ዓመት ታህሳስ  በአዲስ አበባ በተካሄደው የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ  0 ነጥብ 2 በመቶ ከአገሮቹ ገቢ ዕቃ ተሰብስቦ ለሕብረቱ እንዲገባ መወሰኑ ይታወሳል። 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2009 በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በክረምት የሚሰጠውን ማጠናከሪያ ትምህርት ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ገለጹ።    

ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ ትምህርት ቤቶች መካከል ዳግማዊ ምኒሊክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ መስከረም አፀደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና ምስራቅ ጎህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው።     

በየዓመቱ በክረምት ወራት ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡባቸው መስኮች መካከል የክረምት ማጠናከርያ ትምህርት አንዱ ነው።

ዘንድሮም በበጎ ፈቃድ የክረምት ትምህርት ለሚሰጡት አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው ትምህርት ቤቶቹ ለኢዜአ የገለጹት።

የምስራቅ ጎህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ  መምህር አቶ ግርማዬ ኪዳኔ እንደገለጹት የመደበኛ ትምህርት እየተጠናቀቀ በመሆኑ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የሚያስተምሩበት አስፈላጊ ግብአቶችን ትምህርት ቤቱ አሟልቷል። 

የመስከረም አጸደ ህጻናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ  ጸጋዬ ቀዲዳ በበኩላቸው፤ በክረምት ወራት የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የትምህርት አገልግሎት ለተማሪዎች ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።    

የመማሪያ ክፍሎችና ግብዓቶችን ከማሟላት ባለፈ የክረምት ትምህርት መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች ምዝገባ መካሄዱን ነው የተናገሩት።   

የዳግማዊ ምኒሊክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትም ከአንደኛ ደረጃ በላይ በሁለተኛ ደረጃ ያሉ ተማሪዎችንም ለማስተማር አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።                              

የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ጸጋዬ ገብረ መስቀል "ተማሪዎችን የመመዝገብና የግብዓት አቅርቦት ዝግጅት ተከናውኗል" ብለዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይለሥላሴ ፍሰሃ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚደግፉ በመደበኛው የትምህርት ጊዜ የሚሟሉ ግብዓቶች ለክረምት ትምህርቱም  እንዲሟሉ ተደርጓል።    

ወጣቶች በየዓመቱ በክረምት ወራት ደም በመለገስ፣ የክረምት ትምህርት በመስጠት፣ የአካባቢ ልማትና ችግኝ ተከላ በማካሄድና የመንገድ ትራፊክ ማሳለጥ ሥራዎችን ያከናውናሉ።

በተጨማሪም የጎዳና ወጣቶች የሥራ እድል የሚያገኙበት ሁኔታ የማመቻቸትና ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ፣ አረጋዊያንን መርዳት፤ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ግንዛቤ የመስጠት ተግባራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች የሚከናወን ነው።

ባለፈው ዓመት በበጎ ፈቃድ የክረምት ትምህርት አገልግሎት ዘርፍ 1 ሺ 375 ወጣቶች ተሳትፈው ፤ 78 ሺ ተማሪዎች ማስተማራቸው የሚታወስ ነው።

በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ደግሞ 31 ሺ ተማሪዎች ሥልጠና አግኝተዋል። 

ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በአጠቃላይ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ላይ እንደሚሳተፉ መረጃዎች ያመለክታሉ።  

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ