አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 04 July 2017

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2009 ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የጀመረችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ29ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ ከመጡት የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ዴንግ ጋይ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳይ ላይ መክረዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለፃ የደቡብ ሱዳን አለመረጋጋት ለቀጣናው አገራት ሠላም ፈተና ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነትና በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አጠናክራ እንደምትቀጥል መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በኩል ለአገሪቱ ሠላም መስፈን ለሚደረገው ጥረት የቀዳሚነት ሚናዋን ትጫወታለች ብለዋል።

ደቡብ ሱዳን ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የፈረመችውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንድትቀጥል ለአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ዴንግ ጋይ ጥሪ አቅርበውላቸዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንት ዴንግ ጋይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአገራቸው ወደ ቀድሞ ሠላሟ መመለስ እያደረገች ላለው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ደቡብ ሱዳን የተናጠል ተኩስ አቁም ከማድረግ ባለፈ ብሔራዊ ምክክር እያካሄደች እንደሆነና የአፍሪካ አገራትም ይህን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

በፕሬዚዳንት ሳልቫኬር ዲንካናና በቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሬክ ማቻር መካከል ከሶስት ዓመት በፊት በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ በጁባ የእርስ በእርስ ጦርነት መጀመራቸው ይታወሳል።

በእነዚህ ኃይሎች የተቆሰቆሰው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናዊያንን ለሞትና ለስደት ዳርጓል።

ኢትዮጵያም በጦርነቱ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናዊያንን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።

በደቡብ ሱዳን ሠላም እንዲሰፍን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ተፋላሚ ወገኖች እርቅ እንዲያወርዱም የበኩሏን ስትወጣ ቆይታለች። 

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2009 የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት የሚሰጣቸው ስልጠናዎች ተደራሽና ጥራትን መሰረት ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባ ባለድርሻ አካላት ተናገሩ።

ኢንስቲትዩቱ በበኩሉ ለስልጠና ተደራሽነት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቋል።

ኢንስቲትዩቱ ዛሬ ለባለድርሻ አካላት የ2009 በጀት ዓመት ሪፖርቱን አቅርቦ ውይይት አካሂዷል።

የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ተወካይ ኢንጂነር ጳውሎስ አንጀሎ ኢንስቲትዩቱ የሰው ኃይሉን በእውቀትና በክህሎት ለማሳደግ እያከናወነ ያለው ተግባር ሊበረታታ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ካለው የስልጠና ፍላጎት አንፃር የሚታዩ ውስንነቶችን ሊቀርፍ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በተለይም ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ የአመራር ኃላፊነት የተሰጣቸውን አካላት ብቃትና አመለካከት በማጎልበት የህዝብ አገልጋይነት ስሜት ተላብሰው እንዲሰሩ ኢንስቲትዩቱ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። 

በተጨማሪም በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰልጥነው ወደ ስራ የሚገቡ ባለሙያዎችን ለማብቃት ለሚቀርቡ የስልጠና ፍላጎቶች በቂ ምላሽ መስጠት አለበት ብለዋል።

የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የተወከሉት ወይዘሮ መሰረት በሻህ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የሚቀርቡለትን የስልጠና ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ ከመመለስ ባሻገር ለባለድርሻ አካላት ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ውስንነቶች እንዳሉበት ተናግረዋል።

ተደራሽና ጥራቱን የተጠበቀ ስልጠና ለመስጠት በሰው ኃይልና በፋይናንስ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ ስራ አመራርና ካይዘን ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ አወቀ ለገሰም ተቋሙ የክልል አመራሮችና ፈፃሚዎችን በማብቃት በኩል አበረታች ስራ እንዳከናወነ ጠቅሰው፤ የተደራሽነት ውስንነቶቹ ላይ በትኩረት መስራት አለበት ብለዋል።

ሴቶችን ለአመራርነት ያለማብቃት፣ ስልጠናዎችን በተግባር ያለማስደገፍ፣ ወቅቱን ጠብቆ ተደራሽ ያለማድረግና የስልጠና መመሪያዎች ጥራት መጓደል በተሳታፊዎች ከተነሱ ክፍተቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ ይትባረክ ኢንስቲትዩቱ በሚቀርቡለት ጥያቄዎች መሰረት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተገቢውን ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ተቋማት ከቀረቡለት የስልጠና ጥያቄዎች መካከል ምላሽ መሰጠት የቻለው 60 በመቶ ለሚሆኑት ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል።

የስልጠና ፍላጎቶችን ማሟላት ያልተቻለው መንግስት የፋይናንስ ድጋፍ ባለማድረጉና የማሰልጠኛ ግንባታ ቦታ ባለመስጠቱ ነው ብለዋል።

ለስልጠና ተደራሽነት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ27/2009 የአገሪቱ የህዳሴ ጉዞ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲገነባ የመንግሥት ሠራተኛው የሥነ- ምግባር መርሆዎችን ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበት የፌዴራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስትር ካሣ ተክለብርሃን አሳሰቡ።    

የሚኒስቴሩ ሠራተኞች የሲቪል ሠርቪስ ቀንን ''በሥነ-ምግባሩ የተመሰገነ ፐብሊክ ሰርቫንት ለኢትዮጵያ ህዳሴ'' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ አክብረዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አገልግሎት ሰጪዎች የሥነ-ምግባር መርሆዎችን ከሥራቸው ጋር በማዋሃድ መተግበር ላይ ሰፊ ክፍተት ይስተዋልባቸዋል።

''ለዚህ ምክንያቱ መርሆዎቹ ከወረቀትና ከንድፈ ሀሳብ የዘለለ ትርጉም የላቸውም የሚል ግንዛቤ መኖሩ ነው'' ያሉት አቶ ካሣ ይህም ተገልጋዩ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዳያገኝ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል። 

የአገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ አገልግሎት ሰጪዎች የሥነ ምግባር መርሆዎችን ከስብዕናቸው ጋር አዋህደው የተሻለና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መትጋት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

''ሥራውን በጥራት የሚከውን፣ የተቋሙ ተልዕኮ ሲሳካ የሚኮራ ሠራተኛ በሥነ ምግባሩ የተመሰገነ አገልጋይ መገለጫ ነው'' ያሉት ሚኒስትሩ የህዝብ እርካታ ለመፍጠር መሠል አመለካከት ያለው አገልጋይ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።         

የሚኒስቴሩ የሰው ኃይል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ምትኩ በ12ቱ የሥነ ምግባር መርሆዎች ዙሪያ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ጹሁፍ አቅርበዋል።

የህዝብ ጥቅም ማስቀደም፣ ሥልጣንን በአግባቡ መጠቀም፣ ህግን ማክበር፣ ለህዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት፣ ታማኝነትና ሀቀኝነት በአገልጋዩ ውስጥ ሊሰርጽ ይገባል ብለዋል።    

አገልግሎት ሰጪው ለሚሰራው ሥራ ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባው አመልክተው ሠራተኛው ሁሌም ለእውነት መቆም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።   

የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ መድህን ገብረሥላሴ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የታማኝነትና ሀቀኝነት መርሆዎችን ተከትለው ለመስራት ዝግጁ ናቸው።   

''በውይይቱ የተደረገው ገለጻ ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለመካስ ትልቅ ስንቅ ሆኖኛል'' ያሉት ደግሞ ሌላኛው ሠራተኛ አቶ አበበ መለሰ ናቸው። 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሰኔ 27/2009 የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከውሳኔ ሰጪነት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት ገለጹ፡፡

ሁለተኛው የኦሮሚያ ሴቶች ኮንፈረንስ ዛሬ በአዳማ ከተማ ሲካሄድ ፕሬዘዳንቱ አቶ ለማ መገርሳ እንደገለጹት መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ፖሊሲና የልማት ፓኬጅን በመከለስ  አዲስ ስትራቴጅ ቀርፆ ወደ ተግባር ተሸጋግሯል።

በኮንፍረንሱ  ሴቶች በፍትህ ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ለተነሳው ጥያቄ ፕሬዘዳንቱ በሰጡት ምላሽ  መንግስት ይህን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት ከፖሊስ ኮሚሽን ጀምሮ በአቃቢ ህግና በዳኞች አሰራር ላይ ማስተካከያ እያደረገ እንደሚገኝ  ተናግረዋል።

በውሃ፣ጤና፣ትምህርት፣መንገድ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ የሚነሳውን ጥያቄ ለመመለስ እንዲሁም በፀጥታና ድህንነት ማስከበር ላይ በቀጣዩ ዓመት  በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

መንግስት ከመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በመቀነስ የሴቶችና የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት 6 ቢሊዮን ብር መመደቡን የጠቀሱት አቶ ለማ ይህ ሀብት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል።

የእናቶችና የህፃናት ሞት ለመቀነስ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ወረዳዎች የአምቡላንስ ግዥ መከናወኑንም ጠቁመዋል።

እንደፕሬዝደንቱ ገለጻ በሁሉም የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወደ አመራር በማምጣት ከውሳኔ ስጪነት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አዚዛ አብዲ በበኩላቸው ሴቶች ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ተያይዞ የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት ለመከላከል  ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ በክልሉ ግንባር ቀደም ሴቶችን ያካተተ የቁጠባ ዘመቻ በማካሄድ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አመልክተው በዚህም ከ3 ሚሊዮን በላይ ሴቶች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።

የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳ "የገጠርና የከተማ ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማላቀቅ፣ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በእኩልነት እንዲከበሩ ለማስቻል የተደረጉ ጥረቶች የተፈለገውን ያህል ለውጥ አላመጣም "ብለዋል።

ኮንፈረንሱም  በመንግስት አስተዳደራዊ እርከኖች በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የመብት  ጥሰቶችን በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

"የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ የዘርፉ አደረጃጀቶችና የመንግስት ርብርብ ወሳኝ ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ኮንፍረንስ ላይ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ራሳቸውን ለማላቀቅ ባደረጉት ጥረት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 432 የክልሉ ሴቶች ተሸልመዋል፡፡

ከክልሉ ፕሬዝደንት እጅ ከተሸለሙት  መካከል የልብስ ስፌት ማሽን፣የውሃ መሳቢያ ሞተር፣  ጄኔሬተርና  ሜዳሊያ ይገኙበታል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2009 ኢትዮጵያ በ13ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስመዘገበችው ውጤት በቀጣይ ለሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሚሆን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ገለጸ።

በአልጄሪያ በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 38 ሜዳሊያዎች ያመጡት የኢትዮጵያ ልዑካን አባላት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል ተደረጎላቸው።

በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ተገኝተዋል።

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በዚህ ወቅት፤"በሻምፒዮናው በርካታ አትሌቶች ሜዳሊያ ይዘው መምጣታቸው  የሚያስደስት ነው።በተለይም ኢትዮጵያ በማትታወቅባቸው የስፖርት ዓይነቶች ውጤት መመዝገቡ የሚደነቅ ነው" ብላል።

የተገኘው ውጤት በቀጣይ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሚሳተፉ አትሌቶች "ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆናል" በማለት ገልጿል አትሌት ኃይሌ። 

ይህ ማለት ግን በአትሌቲክስ ስፖርት ሊደረስበት የታሰበው ግብ ላይ ተደርሷል ማለት እንዳልሆነም ነው አትሌት ኃይሌ የተናገረው።

ስለሆነም በቀጣይ ውድድሮች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት መስራት እንደሚጠበቅ አስገንዝቧል።

ከተመዘገበው ውጤት በላይ በቡድኑ መካከል የነበረውን ወዳጅነትና እና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከምንም በላይ አስደሳች መሆኑን አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ተናግሯል።

የወጣቶችና ስፖርት  ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የተመዘገበው ውጤት ለአትሌቶችም ሆነ ለመንግስት ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ ነው።

አሁን የተገኘው ውጤት በዓለም አቀፍ ወድድሮች ስኬታማ ለመሆን የሚያነሳሳና "ከፊታችንም ብዙ ስራ እንደሚጠብቀን ያሳየ ነው" ብለዋል።

"የዓለም ሻምፒዮናዎች በዚህ ስሜትና ወኔ መቀጠል ይኖርብናል፤ በቡድን ሰርተን ቀድሞ የነበረንን ዝናና ክብር ለመመለሰ መትጋት አለብን" ብለዋል አቶ ተስፋዬ።

የልዑካን ቡድኑ ዋና አስተባባሪና የረጅም ርቀት ዋና አሠልጣኝ ካሱ ዓለማየሁ "ውጤቱ ሊመጣ የቻለው አትሌቶች አንድነት እንዲኖራቸው በመሰራቱ ነው" ብለዋል።

አትሌቶች ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ውድድሩ ፍጻሜ በአንድነት ለአንድ ዓላማ መዘጋጀታቸው ውጤታማ ለመሆን እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

በአምስት ሺህ እና በስምንት መቶ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኙት አትሌት መስከረም ማሞና አትሌት ትዕግስት ከተማ በቂ ዝግጅት በማድረጋቸው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሻምፒዮናው ወርቅ ለማምጣት ዓልመው ማሳካታቸውን ነው አትሌቶቹ የገለጹት።

በቀጣይም ጠንክሮ በመስራት አገራቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስጠራት እቅድ እንዳላቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ13 ወርቅ፣ 13 ብርና 12 ነሐስ፣ በድምሩ በ38 ሜዳሊያዎች  ውድድሩን በበላይነት ማጠናቀቋ ይታወሳል።

ለልዑካን ቡድኑ  ዛሬ  ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሏል።

Published in ስፖርት

ሐረር ሰኔ 27/2009 የሐረርን ከተማ የቱሪዝም ልማት ለማሳደግ መንግስት ለመሰረተ ልማት ግንባታ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳዳር አስታወቁ።

ሐረር የተቆረቆረችበትን አንድ ሺህ 10ኛ ዓመት ዛሬ በከተማው በሚገኘው መለስ ዜናዊ መታሰቢያ የባህል ማዕከል ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ እንዳሉት፤ ሐረር በስልጣኔ፣ በንግድ እንቅስቃሴና በሃይማኖት ትምህርት ማዕከልነት ቀደምት ከመሆኗም በላይ የሰላም፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህልን ለበርካታ ዓመታት ይዛ ቆይታለች።

በዚህም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰላም፣ የመቻቻልና የአብሮነት ሽልማት እንደተበረከተላት አስታውሰዋል።

አቶ ሙራድ እንዳሉት፣ የሐረር ከተማ ጥንታዊ የስልጣኔ አሻራን ጠብቀውና ተንከባክበው ካቆዩ አንጋፋ የአገሪቱ ከተሞች አንዷ ስትሆን የባህል፣ የታሪክና የቅርስ ሙዚየም ባለቤትም ናት።

" በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ታሪኮች እንዲሁም የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን በአንድ ላይ መያዟም ከተማዋን ልዩ ያደርጋታል።" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነት ለማጎልበት የክልሉ መንግስት በመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

"በተለይ በሐረሪ ገጠር ወረዳዎች ከተሜነትን ለማስፋፋት ገጠርና ከተማውን የሚያገናኝ መንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በሁሉም አቅጣጫ በመከናወን ላይ ናቸው።" ብለዋል።

ከውጭ አገርና ከአገር ውስጥ ለበዓሉ የመጡ የክልሉ ተወላጆች በክልሉ የሚያከናውነውን የልማት ሥራ ከመደገፍ ጎን ለጎን መዋለ ንዋቸውን በክልሉ በማፍሰስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። 

የበዓሉ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪም አብዱረሀማን በበኩላቸው፣ የሐረር ከተማ አንድ ሺህ 10 ኛ ዓመት የምስረታ በዓልና ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን የማስቀጠልና ገጽታን የመገንባት ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።

በዓሉ ዛሬ ሲከበር የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የአጎራባች ክልል ከንቲባዎችና የምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የክልሉ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2009 የማዕቀፍ ግዥ ስትራቴጂ ጥራት ያለው እቃ በሚፈለገው ፍጥነት በማቅረብ ረገድ ክፍተት እየተስተዋለበት መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

አሰራሩ በጠንካራ አደረጃጀት የሚመራ ከሆነ በዘርፉ የሚስተዋለውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመከላከል ስትራቴጂው ጥሩ አማራጭ መሆኑንም የጥናቱ ግኝት አሳይቷል።

የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በዘርፉ ላይ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ዙሪያ ዛሬ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራት ካላቸው አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ከግማሽ በላይ ለንብረት ግዥ ሲውል በኢትዮጵያም ከ15 በመቶ በላይ የሚሆነው ለዚሁ ተግባር እንደሚውል መረጃዎች ያሳያሉ።

በመሆኑም ዘርፉ ለሙስና ያለውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የግዥ ሥርዓቱን ከሙስናና ብልሹ አሰራር ይታደግ ዘንድ ወጥ የግዥ ሥርዓት መዘርጋት አስፈልጓል።

የፌዴራል የግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎትም የማዕቀፍ ግዥ ስትራቴጂ አውጥቶ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያቀርባል።

ይህም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚጠቀሙባቸውን ተመሳሳይ እቃዎችና አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ፣ በጥራትና በፍጥነት የማቅረብ ውጥን ያለው ነው።

ይሁንና ኮሚሽኑ ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ስትራቴጂው የሚፈለገውን እቃ በጥራት፣ በፍጥነት እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ላይ ክፍተት ይታይበታል።

በማዕቀፍ ግዥ የሚገዙ እቃዎች በተለይም የኤሌክትሮኒክስ፣ የህትመት፣ ፈርኒቸሮች፣ ፋይል ካቢኔቶችና አልባሳት ከፍተኛ የጥራት ጉድለት እንደሚታይባቸው ጥናቱ አሳይቷል።

ዕቃዎች በሚፈለገው ጊዜ ተገዝተው ስለማይቀርቡም የተመደበላቸውን በጀት ሳይጠቀሙ በጀት ዓመቱ ስለሚጠናቀቅ የተቋማቱን የበጀት አጠቃቀም እያቃወሰም ነው ብሏል ጥናቱ።

እቃዎቹ በተፈለጉ ጊዜ አለመቅረባቸውም በዋጋ ጭማሪ ምክንያት ለተጨማሪ ወጪ እየተጋለጡ መሆኑን አመልክቷል።

በፍጥነት ይወገድ የተባለን ንብረት በወቅቱ ያለማንሳትና ለሚገዙ እቃዎች የአገልግሎት ጊዜ ገደብ አለመበጀት ክፍተትም ተጠቅሷል።

የማዕቀፍ ግዥውን የሚፈጽመው ተቋም ጠንካራ አደረጃጀት አለመዘርጋቱ፣ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል አለመኖሩና የአቅራቢ ድርጅቶች የንግድ ሥነ-ምግባር አለማክበር ለችግሩ ምክንያቶች ተብለዋል።

የአሰራሩ ቀልጣፋ አለመሆንና በጠንካራ ቁጥጥር አለመመራቱ ለሙስና በር የሚከፍት ነው የሚል ግምታዊ ሃሳብም በጥናቱ ተመላክቷል።

ያም ሆኖ የግዥ ማዕቀፉ በአገሪቱ በተተገበረ አጭር ጊዜ ውስጥ ሃብትና ንብረት ከመቆጠብ አኳያ ጥሩ ጅምሮች አሳይቷል ነው የተባለው።

በመሆኑም ችግሮቹ የሚወገዱበት መንገድ ከተበጀተለት ግዥ ላይ የሚስተዋለውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመከላከል መልካም አማራጭ ነው ሲል ጥናቱ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።  

ጥናቱ በ55 ግዥ ፈጻሚ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና በስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ነው የተካሄደው።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2009 ኢትዮጵያ አህጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና በአገር ኢኮኖሚና በህዝቦች ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተጽዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት እንዳልተቀበለችው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ተግባራዊ ለማድረግ 48 አገሮች የተስማሙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት አገሮች ግን አልተስማሙም ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በአዲስ አበባ የተካሄደውን 29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መጠናቀቅ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አህጉራዊው ነጻ የንግድ ቀጣና በሚመሰረትበት ወቅት በአገልግሎቶች ብቻ ሳይሆን በዕቃዎች ላይ የሚጣሉ ታሪፎች የተመጣጠኑና "ለንግድና ኢንቨስትመንት የተመቻቹ መሆን አለባቸው" ብለዋል።

ስለሆነም አጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በፍጥነት መክፈት በአገሪቷ ኢኮኖሚና ህዝቦቿ ላይ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ ግምት ውስጥ መግባቱን ጠቁመዋል። በዚህ ምክንያት አለመቀበሏን ነው የተናገሩት።

ይሁንና "ኢትዮጵያ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከአፍሪካውያን ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት በጋራ ትሰራለች" ብለዋል።

አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናው እ.ኤ.አ በ2012 አዲስ አበባ በተካሄደው 18ኛው የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ ላይ መሪዎች የመሠረቱት ሲሆን፤ ይህም ስምምነት እ.ኤ.አ በ2018 ላይ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህም ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ የ55 አገሮች ህዝቦችን ወደ አንድ የሚያመጣና ከሦስት ነጥብ አራት ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት አጠቃላይ የአህጉሪቷ ምርት በንግድ ትስስሩ ላይ እንደሚቀርብ ከሕብረቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። 

በነጻ ቀጣና ተግባራዊ በመሆኑ ላይ ካልተስማሙት መካከል ከኢትዮጵያ ሌሎቹ  ይፋ አልሆኑም።

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ሰኔ 27/2009 ከህገ ወጥ ንግድ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የዋጋ አለመረጋጋት ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አስገነዘቡ።

''ዘመናዊ የንግድ እንቅስቃሴ ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት'' በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው የአማራ ክልል 5ኛው የንግድ ቀን የማጠቃለያ ኘሮግራም ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዚሁ ወቅት እንደገለፁት የተረጋጋና የህብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ የንግድ ስርዓት ለመገንባት መንግስት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው።

ባለፉት ዓመታት በተሰራው ጠንካራ ስራም በህግና ስርዓት የሚመራ የንግድ እንቅስቃሴ መፍጠር መቻሉንና ዘርፉ እየተመዘገበ ላለው የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በሚፈፅሙት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የንግድ ስርዓቱን እንዳይረጋጋ በማድረግ የዋጋ መዋዠቅና የሸቀጦች የአቅርቦት እጥረት ሲፈጥሩ ይስተዋላል።

ህገ ወጦችን ተከታትሎ በመያዝና ለመንግስት መክፈል የሚገባቸውን ግብር እንዲከፍሉ በማድረግ ከህገ ወጥ ተግባራቸው ለማስቆም የሚደረገውን የክትትልና ቁጥጥር ስራ በህብረተሰቡ ሊታገዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በንግድ ዘርፉ ሚስተዋለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር መፍታት እንደሚገባ ገለፁት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ናቸው።

ባለፉት ዓመታት ተሻሽሎ የወጣውን የንግድ ሪፎርም በመተግበር ስርዓቱ ዘመናዊና የተጠቃሚውን ማህበረሰብ የአቅርቦትና የዋጋ አለመረጋጋት ለመፍታት በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።

በዚህም ከ350 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች ቋሚ የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 85 በመቶ የሚሆኑት በንግድ ምክር ቤት ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።

የተረጋጋና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት በመገንባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት  እየተደረገ ቢሆንም አሁንም ግን በዘርፉ የሚስተዋሉ ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

በተለይም መንግስት የሚያቀርባቸውን የስኳርና ዘይት ምርቶች መደበቅ፣ ባእድ ነገሮችን ቀላቅሎ መሸጥ፣ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት መፍጠር፣ ያለ ንግድ ፈቃድ መንቀሳቀስ፣ የኮንትሮባንድ ንግድና መሰል ችግሮች በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው።

በመሆኑም እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የንግድ ስርዓቱ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን በሚደረገው ርብርብ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በየዓመቱ የሚከበረው የንግድ ቀንም የተገኙ ስኬቶችን በማስፋት እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና በዘርፉ የተሻለ ተሞክሮ ላበረከቱ አካላትና ተቋማት እውቅና ለመስጠት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ቡላዶ በበኩላቸው በገበያ ላይ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት  ጠንካራና የተደራጀ የንግድ ልማት ሰራዊት ገንብቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የንግድ ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግና የተረጋጋ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር በአማራ ክልል በተደራጀ መንገድ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚመሰገንና ሌሎች ክልሎችም በተሞክሮ ደረጃ ሊወስዱት የሚገባ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል።

5ኛው የንግድ ቀን በወረዳና በዞን ደረጃ በፓናል ውይይት፣ በስፖርታዊ ውድድርና ለምስጉን ነጋዴዎችና ተቋማት እውቅና በመስጠት ሲከበር ቆይቷል።

በዛሬው እለት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ክልል አቀፍ የማጠቃለያ ፕሮግራም በዘርፉ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ተቋማት እንዲሁም ማህበራት የምስክር ወረቀት፣ ዋንጫና የቁሳቁስ ሽልማት ተሰጥቷል።

''ዘመናዊ የንግድ እንቅስቃሴ ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት'' በሚል መሪ ቃል በተከበረው የንግድ ቀን ላይ ከወረዳ፣ ከዞንና ከክልል እንዲሁም ከንግድ ሚኒስቴር የተውጣጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2009 ለአፍሪካ ህብረት መመስረትና የአህጉሩን ህዝብ ድምጽ በመወከል ከፍተኛ አስተዋጾኦ ላበረከቱት ለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊና ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ እውቅና ተሰጠ።

እውቅናው የተሰጠው 29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ ሲጠናቀቅ ነው።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጉባዔውን መጠናቀቅ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት እውቅና የመስጠቱ ሃሳብ የመነጨው ከአፍሪካዊያን መሪዎች ነው።

በዚህም ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊና ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እውቅና የተሰጣቸው የኢትዮጵያ መሪዎች ሆነዋል። 

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ጊዜያቸውን በመሰዋት፣ ሀሳብ በማፍለቅና በብዙ መድረኮች የአፍሪካን ድምጽ በማሰማት ላበረከቱት አስተዋጾኦ እውቅናው እንደተሰጣቸው ገልፀዋል። 

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት የአሸማጋይነት ሚና በመጫወት፣ የዲፕሎማሲ ሥራ በመስራት፣ ድርጅቱ ከተመሰረተ በኋላም እንዲቀጥል ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና የተሰጣቸው ሌላው የኢትዮጵያ መሪ ደግሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ናቸው። 

ይህ አገሪቷና ህዝቦቿ የአፍሪካን አጀንዳዎች በባለቤትነትና ቅድሚያ ሰጥተው መስራታቸውን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ህዝቦች መልማት፣ ማደግና መበልጸግ ሁሌም እየሰሩ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም።

የአፍሪካ ህብረት እውቅናውን አስመልክቶ ግልጽ የሆነ ዝርዝር አካሄድ እንዲኖር ውሳኔ ማሳለፉንም ጨምረው ገልፀዋል።

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ