አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 03 July 2017

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2009 መገናኛ ብዙኃን የኅብረተሰቡን የመረጃ ፍላጎት ለማርካት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የኢፌዴሪ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት "የአገሪቷ የሚዲያ ተልዕኮ፣ ችግሮች፣ መፍትሄዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች" በሚል መሪ ሃሳብ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን፣ የመገናኛ ብዙኃንና ኮምዩኒኬሽን አመራ አባላትና ባለሙያዎችን ዛሬ አወያይቷል።

በአገሪቷ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ አመራር አባላትና ጋዜጠኞች ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ ያሉባቸው ችግሮች፣ በቀጣይ ሊወስዷቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ጥራቱን የጠበቀና ወቅታዊ መረጃዎችን ኅብረተሰቡን በሚያረካ መንገድ እያቀረቡ እንዳልሆነ በሰነዱ ላይ ተዳሷል።

ዘርፉ ለብልሹ አሰራር መጋለጥ፣ የፋይናንስ እጥረት፣ የባለሙያዎች የአቅምና ክህሎት ውስንነት፣ የመረጃ እጥረት፣ ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ይልቅ በማስታወቂያ ላይ ማተኮር፣ የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ያሉባቸው ተግዳሮቶች እንደሆኑ በሰነዱ ተገልጿል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በሰጡት አስተያየት፤ የመገናኛ ብዙኃን ለኅብረተሰቡ ጥራትና ተዓማኒነት ያለው መረጃ እንዲያደርሱ ተቋማት የተደራጀ መረጃ ሊያቀርቡላቸው እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

ተቋማት የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት በመዘርጋት ለተጠየቁት ጥያቄ ትክክለኛና በቂ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ አርዓያ ጌታቸው እንዳሉት፤ መንግስት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባልሆኑ የተቋማት አመራር አባላት ላይ እርምጃ አለመውሰዱ መገናኛ ብዙኃን ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን መረጃ እንዳያገኙ አድርጓል።

የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች መረጃ ከልክለው ወይም በሙስና ወንጀል ተጋልጠው ተጠያቂ ከመሆን ይልቅ ሌላ ኃላፊነት እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ጋዜጠኛ ብሩክ ያሬድ፤ የመንግስት ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት የመገናኛ ብዙኃኑን ነፃነት እየተጋፋ መሆኑን ጠቁሟል።

የመንግስት ተቋማት መገናኛ ብዙኃኑን የሪፖርት ማቅረቢያ አድርገውታል፣ ለኅብረተሰቡ ጥቅም የማይሰጡ የፕሮቶኮል ዜናዎች እንዲሰሩ ባለስልጣናት ጫና ያሳድራሉ የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃኑ ሪፎርም ተግባራዊ ተደርጎ ችግሮች እስከሚፈቱ ድረስ ያለውን አቅም በመጠቀም ኅብረተሰቡ የጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

መገናኛ ብዙኃን በአገሪቷ በተመዘገበው የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስርዓት ላይ ድርሻቸው የጎላ ቢሆንም፤ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ ለመራመድ ከዚህ በተሻለ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ለዚህ ስኬታማነት የመንግስትና የመገናኛ ብዙኃን አመራር አባላት፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት በቅድሚያ አመለካከት መቀረፅ እንዳለበት የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "መገናኛ ብዙኃኑም  በዚህ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2009 የአፍሪካ ህብረት በጅቡቲና ኤርትራ መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት ትኩረት እንዲያደርግ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አሳሰበ።

57ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።  

በስብባው የወቅቱ የምክር ቤቱ ሊቀ-መንበርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም አህመድ፣ የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃመድ አሊ የሱፍና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ጋራድ ኦማር ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳም ኩቴሳ፣ የኬኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ አምባሳደር ካትሪን ሙዋንጊና ሌሎችም የአባል አገራቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አህጉራዊና አለምአቀፋዊ ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።   

የጁቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃመድ አሊ የሱፍ በጅቡቲና ኤርትራ ድንበር አዋሳኝ ዱሜራ በተሰኘው አካባቢ የተፈጠረው ውዝግብ አሳሳቢና መፍትሄ የሚያሻው ጉዳይ ነው ብለዋል። 

የአፍሪካ ህብረት በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደከፋ ደረጃ ሳይደርስ እልባት እንዲያገኝ መስራት እንደሚገባውም ምክር ቤቱ  አሳስቧል። 

ምክር ቤቱ የኳታር ጦር ዱሜራን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በአካባቢው የተፈጠረውን ውዝግብ በቅርበት እንደሚከታተለው ገልጾ የአውሮፓ ህብረት፣ የጸጥታው ምክር ቤት፣ ቻይናና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለችግሩ መፈታት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል። 

ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ችግር መከታተል የሚያስችለውን ውሳኔ በዛሬ ሰብሰባው አሳልፏል። 

Published in ፖለቲካ

ጎንደር/ደብረማርቆስ ሰኔ26/2009 በሰሜን ጎንደርና  በምስራቅ ጎጃም ዞኖች 18 ወረዳዎች የተከሰተውን ጸረ ሰብል  ተምች ለመቆጣጠር  ህብረተሰብ አቀፍ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ አድና አበበ ለኢዜአ እንዳሉት ከ350ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በተባይ አሰሳና ቁጥጥር ስራ እየተሳተፉ ናቸው፡፡

በዞኑ አስር ወረዳዎች በሚገኙ 487 ቀበሌዎች ውስጥ  ከ500ሺህ  ሄክታር በላይ  የእርሻ መሬት ላይ የተባይ አሰሳ ስራ ተከናውኗል፡፡

በዚህም በተምቹ ተወሮ የነበረ 8ሺ 647 ሄክታር የበቆሎና የማሽላ ሰብልን በባህላዊ የመከላከል ዘዴ   6ሺ ሄክታርን ከተባዩ ነጻ ማድረግ መቻሉን ባለሙያዋ ጠቁመዋል።

እንዲሁም 247 ሄክታር ሰብል ደግሞ የኬሚካል ርጭት በማካሄድ የመከላከል ስራ ተከናውኗል፡፡

በተባይ መከላከል ስራው አርሶአደሮች፣  የመንግስት ሰራተኞች ፣ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም የግብርና ሙያተኞችና አመራሮች ተሳታፊ ናቸው።

የጭልጋ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ ወይዘሮ ፈንታዬ ማዘንጊያ በወረዳው ተምቹ ወሮት የነበረውን 630 ሄክታር የበቆሎ ማሳን የህብረተሰቡን ጉልበት በመጠቀም ከተባዩ ማፅዳት ማቻሉን ተናግረዋል።

ከ29ሺ በላይ የወረዳው አርሶ አደሮችና የመንግስት ሰራተኞች በመከላከሉ ስራ  ተሳታፊ እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡

"በቀበሌና በጎጥ ግብረሃይል በማቋቋም ከ28ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተባይ አሰሳና መከላከል ስራዉ አሳትፈናል" ያሉት ደግሞ የአለፋ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ባለሙያ አቶ የኑስ ወርቁ ናቸው፡፡

በ30ሺ ሄክታር ማሳ ላይ አሰሳ በማድረግ በ9 ቀበሌዎች በ27 ሄክታር የበቆሎ አዝመራ ላይ የተከሰተውን ተምች በባህላዊ የመከላከያ ዘዴ ማስወገድ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይም  በምስራቅ ጎጃም ዞን  ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ይበልጣል አለምነህ እንደገለጹት በስምንት ወረዳዎች በሚገኙ 26 ቀበሌዎች ውስጥ 280 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ ተምቹ ተከስቷል፡፡

ከዚህም ውስጥ በህብረሰተቡ  ተሳትፎ 211 ሄክታር ማሳ  ከተባዩ መከላከል መቻሉን ጠቅሰው ከተዘጋጀው  990 ሊትር ኬሚካል ውስጥ 135 ሊትር  ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

ከባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ   ማሳቸውን በማሰስ  ተባዩ እንዳይከሰት ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን  መከላከል እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ በአዋበል ወረዳ የየገሽ ቀበሌ አርሶ አደር ደረበ ምትኩ ናቸው፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2009 የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ የአገር ውስጥ ባለኃብቱን ተሳትፎ የማጎልበት ስራ እየተሰራ መሆኑን የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዘርፉ የባለኃብቱን ተሳትፎ በተመለከተ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አገሪቱንም፤ ባለሃብቱንም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

መንግሥት ለባለኃብቱ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማቅረብ የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ጥረት ቢያደርግም እድገቱ የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም አብዛኛው ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች እሴት ሳይጨመርባቸው ስለሚላኩ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት እንዳልቻለች አስረድተዋል።

በመሆኑም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ  የባለኃብቱን ተሳትፎ በማሳደግ በአንድ በኩል አገሪቱ በሌላ በኩል ደግሞ ባለኃብቶቹ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ያሉት ዳይሬክተሩ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የባለኃብቶች ተሳትፎ አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ ሊጎለበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት በኩል የማምረቻ ቦታዎች፣ የብድር አገልግሎት፣ የአቅም ግንባታ ድጋፎች እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩም ትኩረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ባለኃብቶች በተቀናጀ የቡና፣ የሰሊጥ፣ የበቆሎ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንዲሁም በቆዳ ምርት፣ በጨርቃጨርቅ፣ በወረቀት ምርቶች ግብዓት ማምረት ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አብራርተዋል።

በመድረኩ የታደሙ ባለኃብቶች በበኩላቸው መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የሚያበረታታና ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል።

ከባለሃብቶቹ መካከል አቶ አሰፋ ካሳ መንግሥት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወጣቶችንና ባለኃብቶችን ለማሳተፍ ቁርጠኛ መሆኑን ተረድቻለሁ ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአትክልትና ፍራፍሬ ማምረትና እሴት መጨመር ሥራ ላይ ለመሰማራት በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸው መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ሊሟሉ እንደሚገባም አስተያየት ሰጥተዋል።

ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ሃዋ ጡፋ በበኩላቸው'' በመድረኩ ላይ በመገኘቴ በዘርፉ በቂ እውቀት እንዲኖረኝ አስችሎኛል፤ይህም አሁን ካለሁበት የሆቴል ንግድ በተጨማሪ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት አድሮብኛል'' ብለዋል።

በዘርፉ የሚሳተፉትን ኢንተርፕራይዞች ለማበረታታት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከ41 ቢሊዮን ብር በላይ መድቦ በመላ አገሪቱ 110 ቅርንጫፎችን በመክፈት እየተንቀሳቀሰ ነው ።

በሌሎች በተመረጡ ዘርፎች ላይ ከ500 ሺህ እስከ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ላላቸውና ከስድስት በላይ ሠራተኛ ላላቸው ኢንተርፕራይዞች በልማት ባንክ በኩል የካፒታል እቃዎች ኪራይና የዱቤ ግዥ አገልግሎት እንዲሁም 75 በመቶ የብድር ድጋፍ ተዘጋጅቷል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2009 ኢትዮጵያና ሱዳን የሁለትሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ መከሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሱዳኑ አቻቸው ኢብራሂም ጋንዱር ጋር አገራቱ የነበራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚያጠናክሩበትና በጋራ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ተመካክረዋል፡፡

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ በመጠናከር ላይ ይገኛል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የማስቀጠል ዓላማ ያለው ውይይት እንዳደረጉ የተናገሩት ሚኒስትሩ በፕሬዝዳንት አልበሽር የኢትዮጵያ ጉብኝት ውጤት አፈጻጸሞችና ቀጣይ ሁኔታዎች ላይም ተወያይተናል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ፤ የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ላይ መነጋራቸውንም ገልጸዋል፡፡

በህብረቱ ጉባኤ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውንም ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ ሱዳን በበጎ ጎኑ እንደምትመለከተው ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

መቱ ሰኔ 26/2009 በኢሉአባቦራ ዞን ለመኸሩ እርሻ  በግብኣትነት የሚውል ከ35 ሺ ኩንታል የሚበልጠው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ደርሷል፡፡

እጅ በእጅ ሽያጭ ለአርሶ አደሩ የደረሰው ለምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው 39 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገልጿል።

በጽህፈት ቤቱ የግብአት አቅርቦትና አጠቃቀም ስራ ሂደት መሪ አቶ ተፈሪ ረጋሳ ዛሬ እንደገለጹት የቀረውንም ማዳበሪያ በተመሳሳይ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ የማሰራጨቱ ስራ ቀጥሏል።

በምርት ዘመኑ ለዞኑ የቀረበው ማዳበሪያ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ10 ሺ ኩንታል በላይ ብልጫ አለው።

አርሶ አደሩ በግብዓት አጠቃቀም ዙሪያ ግንዛቤውን እንዲያሳድግ በተሰጠው ትምህርትና ኢኮኖሚያዊ አቅሙ እየጎለበተ መምጣቱ የግብአት ፍላጎቱን እንዲጨምር አድርጎታል።

ከማዳበሪያው በተጨማሪ ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ዘር የተሰራጨ ሲሆን ከ70 ኩንታል በላይ የጤፍና የስንዴ ዘር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

 አርሶ አደር አብዱልቃድር አወል በዞኑ ዳሪሙ ወረዳ የቤና ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በተያዘው የምርት ዘመን ባላቸው ሁለት ሄክታር ይዞታቸው ላይ በቆሎና ሩዝ ለማልማት እየሰሩ መሆናቸውንና  እስካሁን ግማሽ ሄክታር  በዘር መሸፈናቸውን  ገልጸዋል።

በኢሉአባቦራ በተያዘው የመኽር ወቅት 133 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት  ታቅዶ  እየተሰራ  መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ሰኔ 26/2009 በምስራቅ አማራ የህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህል እያደገ በመምጣቱ በህሙማን ላይ ይደርስ የነበረው መጉላላትና አላስፈላጊ ወጭ መቀነሱን የደሴ ደም ባንክ ገለጸ፡፡

የደሴ ደም ባንክ ኃላፊ አቶ ታደሰ ሲሳይ እንደገለጹት የደም ባንኩ በሚንቀሳቀስባቸው የደቡብና ሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የደም ለጋሾች ቁጥር እያደገ መጥቷል፡፡

ባለፉት 11 ወራት በተደረገ እንቅስቃሴ ከ1 ሺ 281 መደበኛ ደም ለጋሾችና ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች 5 ሺህ 715 ዩኒት ደም ተሰብስቦ በምስራቅ አማራ ለሚገኙ 22 ጤና ተቋማት ተሰራጭቷል፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት በዓመት ውስጥ ከ2 ሺህ ዩኒት ደም በላይ እንደማይሰበሰብ ኃላፊው አስታውሰው "በደም አቅርቦት ምክንያት ጤና ተቋማት ድንገተኛ ህሙማንን በተፈለገው ፍጥነት አያስተናግዱም ነበር" ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ህሙማን ህክምና ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ እስከ 15 ሺህ ብር ያወጡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በተለያዩ አካባቢዎች የግንዛቤ ማሳደጊያ መድረክ በማዘጋጀት የህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህል እንዲሻሻልና የደም ለጋሾች ቁጥር እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የጤና ተቋማትም የደም አቅርቦት ችግር መቀረፉንና በህሙማን ላይ ይደርስ የነበረው ውጣ ውረድና አላስፈላጊ ወጭ መቀነሱን ጠቁመዋል፡፡

የመካነ ሰላም ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ከተማ አብተው በበኩላቸው ቀደም ሲል በአካባቢው በቂ የደም አቅርቦት ስላልነበር ህሙማን ወደ ደሴና አዲስ አበባ ይላኩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በደም እጥረት ምክንያት በሆስፒታሉ የሚሰጠው የቀዶ ጥገናና ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች የሚቋረጡበት አጋጣሚ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ደም መለገስ በጤና ላይ የሚያመጣው ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ በቀበሌዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በመንግስታዊ ተቋማት ግንዛቤ በመሰጠቱ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጀት ዓመት በሁለት የዘመቻ እንቅስቃሴ ብቻ 276 ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

በኮምቦልቻ የሚገኘውና ''2 ሺህ 312 '' የሚል መጠሪያ ያለው የደም ለጋሾች ማኅበር መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ይርጋ በበኩላቸው ላለፉት 20 ዓመታት 76 ጊዜ ደም በመለገስ በአገር አቀፍ ደረጃ 2ኛ በክልሉ ደግሞ ቀዳሚ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

የችግሩን ስፋትና የአቅርቦቱን እጥረት በመገንዘብ በርካቶችን ተሳታፊ ለማድረግ ማኅበሩን እንዳቋቋሙ አመልክተው፤ የማህበሩ አባላት በየሶስት ወሩ ከ300 ዩኒት በላይ ደም እንደሚለግሱ ተናግረዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2009 የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለማገዝ የፈጠራ ስራዎቻቸውን እያስተዋወቁ መሆኑን በአይሲቲ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ገለጹ።

ባለሙያዎቹ እንዳሉት ቴክኖሎጂዎቹ የትምህርት፣ የጤና፣ ግብርና፣ ፋይናንስና ሌሎች ዘርፎችን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉ ናቸው።

የአይቲ ከፍተኛ ፕሮግራመር የሆነው ወጣት ታምሩ ኃይሉ እንደተናገረው የተማሪዎች መረጃ፣ የተሽከርካሪዎች ስምሪት መቆጣጠሪያ ሌሎች የአስተዳደር ስራዎችን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ሶፍትዌር በአገር ውስጥ ተሰርቷል።

ድርጅታቸው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ጠቁሞ በዚህም የተቋማቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ውጤታማ  ማድረግ መቻሉን ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅት ከመቀሌ፣ ከአርሲ፣ ከአዳማና ከኮተቤ ዩኒቨርስቲዎች ጋር እየሰሩ እንደሚገኙም አስታውቋል።

ወጣት ያፌት ብርሃኑ ደግሞ የባንክ አገልግሎትን ቀልጣፋ የሚያደርጉና በአቅራቢያ የሚገኙ ታክሲዎችን ሙሉ መረጃ በመስጠት የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል ሶፍትዌር መሰራቱን ጠቁሟል።

የአይሲቲ ማህበር ስራ አስኪያጅ  ወጣት ወንድማገኝ አባተ በዘርፉ በተሰማሩ ባለሙያዎችና ድርጅቶች የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከመንግስት ተቋማት ጋር እየሰራን ነው ብሏል።

በአገሪቱ በተለይም በጀማሪ ባለሙያዎች የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’ የሚል የንግድ ምልክት በመጠቀም ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ እያደረጉ መሆናቸውንም ነው የጠቀሰው።

ማህበሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ የአይ ሲቲ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው ድርጅቶች ጋር የሚገናኙበትን መድረክ በማመቻቸት የቴክኖሎጂ ሽግግር  እየተፈጠረ እንደሚገኝም ገልጿል።

ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተመራቂዎች የተግባር ስልጠና የሚሰጠው የገበያ ዶት ኮም ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ወይዘሪት መርከብ መንግስቱ እንዳሉት የአይሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ያሉትን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ሀሳቦችን ያመነጫሉ።

''ለአብነትም አስቸኳይ ህክምና ማግኘት ያለባቸው ህመምተኞች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ያሉበትን የጤና ሁኔታ መረጃ ለመስጠት የሚያስችል እጃቸው ላይ የሚታሰር ሴንሰር በአይሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ተሰርቷል'' ብለዋል።

እንዲሁም የቆሻሻ ገንዳዎች ላይ የሚገጠሙ ቆሻሻ ሲሞላ በማንሳት ስራ ላይ ለተሰማሩ መልዕክት የሚልክ በሴንሰር የሚሰራ ሶፍትዌሮች መሰራታቸውንም ገልጸዋል።

ድርጅቱ በተለይም ለሴቶች ነጻ ትምህርት እድል እንደሚሰጥና ስልጠና ያጠናቀቁ ተማሪዎችን ከድርጅቶች ጋር በማገናኘት የስራ እድል እንደሚያመቻችም ገልጸዋል።

ደብረ ብርሃን ሰኔ 26/2009 በሰሜን ሽዋ ዞን በተከናወኑ  የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በበጋ ወቅት በተካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ የላቀ አስተዋጾ ያበረከቱ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተሸልመዋል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ እንደገለፁት በዞኑ ባለፉት ሰባት ዓመታት አንድ ሺህ የሚሆኑ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ተካሂዷል ።

ልማቱ በተካሄደበት አካባቢዎች ከ21 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራጅተው በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ ስራዎች  ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።

በተፋሰሶቹ ውስጥ በተካሄደ የንብ ማነብ ስራ ዘንድሮ ከተመረተው 494 ቶን ማር ሽያጭ 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በዘንድሮ በጋ ወቅት በነባርና አዲስ ተፋሰሶች ውስጥ 494 ሺህ ህዝብ ያሳተፈ የእርከን፣ የክትር፣ የእርጥበት ማቆያ የመሳሰሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተከናውነዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተከናወነባቸው ቦታዎች የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው 323 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቱ በበኩላቸው በተፋሰስ ልማት የተመዘገበውን ተጨባጭ ውጤት በሰብል ልማት ለማስቀጠል አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በዘንድሮ የበጋ ወቅት በተካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ የመንዝ ማማ፣ መንዝ ጌራ፣  ሚዳ ወረሞ፣ አሳግርትና አፆኪያ ገምዛ ወረዳዎች ከ1ኛ እሰከ  5ኛ በመውጣት  ኮምፒዉተርና ፕሪንተር ተሸልመዋል ።

በየወረዳውም ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ የወጡ የገጠር ቀበሌዎችም ኮምፒዉተርና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርከቶላቸዋል ።

Published in አካባቢ

ደሴ ሰኔ 26/2009 በሱሰኝነት ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ  አላማ ያደረገ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ትናንት በደሴ ከተማ ተካሄደ፡፡

''ሱሰኝነት ልንከላከለውና ሊድን የሚችል ችግር ነው'' በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የሩጫ ውድድር በደሴ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ምክር ቤትና በአትሌት መልካሙ ተገኝ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ነው።

የውድድሩ ዓላማ ከሱሰኝነት የጸዳ አምራች ትውልድ ለመፍጠር፣ ህዝቡ ስፖርቱን እንዲደግፍ ለማስቻልና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሆነ የውድድሩ አስተባባሪ አትሌት መልካሙ ተገኝ ተናግሯል።

ቀደም ሲልም በአዲስ አበባ፣ በባህርዳርና በአዋሳ ከተሞች ተመሳሳይ ውድድሮች መካሄዳቸውን ጠቁሟል፡፡ 

ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረጉ ተመሳሳይ ውድድሮችም 15 ብቃት ያላቸው አትሌቶች በክለብ እንዲታቀፉ መደረጉን ገልፀዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ በየነ ፈንታው በበኩላቸው ''ውድድሩ በሱስኝነት ዙሪያ ህብረተቡ ግንዛቤ እንዲይዝና የመፍትሄው አካል እንዲሆን ለማነሳሳት ነው'' ብለዋል።

እንዲሁም በአካባቢው ብቃት ያላቸውና ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ጭምር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በእለቱ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር በወንዶች ሰይድ አለሙ ከተንታ በግል ቀዳሚ ሆኖ ሲገባ ገብረማርያም ሰጠው ከተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማአከል፣ ጥላሁን አበባው ከጉና አውስኮድ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል፡፡

በሴቶች አፀደማርያም አርአያ፣ አበበች ተክሌና ኢክራም ተሾመ ሶስቱም ከተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከል አሸናፊ ሆነዋል።

በውድድሩ ላይ ከ500 በላይ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በሌላ በኩል አንድ ጨዋታ እየቀረው ወደ ከፍተኛ ሊግ መግባቱን ላረጋገጠው የደሴ ከነማ እግር ኳስ ክለብ አትሌት መልካሙ ተገኝ የ10 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

አትሌት መልካሙ በተለያዩ የውጭ አገራት በተካሄዱ የግማሽ ማራቶንና የ10 ሺህ ሜትር ውድድሮች በመሳተፍና ውጤት በማስመዝገብ ይታወቃል፡፡

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ