አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 02 July 2017

ሚዛን ሰኔ 25/2009 ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸው ከአንድ ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች ትናንትና ዛሬ አስመረቀ፡፡

የምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተገለጸው፣ ዩኒቨርሲቲው በ38 የትምህርት ዘርፎች አሰልጥኖ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 443ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶከተር ፋሪስ ደሊል የእለቱ ምሩቃን ወደሥራ ሲሰማሩ ታታሪና ሥራ ወዳድ በመሆን በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ላይ የበኩላችውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወንድሙ ገብሬ በበኩላቸው፣ ምሩቃን መንግስት የሚያመቻቻቸውን የሥራ ዕድል እንደ አንድ አማራጭ በመጠቀምና የራሳቸውም ሥራ በመፍጠር ሀገራቸውንና ወገናቸውን መጥቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለሀገር ዕድገት የተማረ የሰው ኃይል መሰረት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድሙ፣ ሀገሪቱ የጀመረችውን የህዳሴ ጎዞ ለማፋጠንና ለማረጋገጥ ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ በትጋት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በሲቪል ምህንድስና  የትምህርት ክፍል በከፍተኛ ውጤት የተመረቀው  ከፍታው ሀብታሙ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በንድፈ ሀሳብና በተግባር የቀሰመውን  የምህንድስና ሙያ ተግባር ላይ በማዋል ሀገሩን ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በ1999 ዓ.ም በአንድ ኮሌጅና በሦስት የትምህርት ክፍሎች 215 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በስድስት ኮሌጆች በ38 የትምህርት ክፍሎች ከ13 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል፡፡

የዘንድሮ ተመራቂዎችን ሳይጨምር 11 ሺህ 489 ተማሪዎችን ቀደም ሲል ማስመረቁን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሰኔ 25/2009 የተደራጁ ሴቶችን በግብርና የኢንቨስትመን ዘርፍ ለማሰማራት እንቅስቃሴ መጀመሩን የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስትሯ አስታወቁ፡፡                 

ሚኒስቴሩ ከፌዴራል ሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የሴቶችን ኢኮኖሚ  ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል አገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል፡፡                    

መድረኩን የመሩት የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትሯ ደሚቱ ሀምቢሳ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ከ2010 በጀት ዓመት ጀምሮ የሴቶች ማህበራትና ዩኒየንን በየደረጃው በማቋቋም በግብርና የኢንቨስትመን ዘርፍ ለማሰማራት ዝግጅት እየተደረገ ነው።        

በልማቱ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሴቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ እንዲቆጥቡ በተደረገው ጥረትም በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት 5 ቢሊዮን ብር መቆጠባቸውን ገልጸዋል።                     

ይህን ከፍተኛ ሀብት ወደግብርና ዘርፍ ለማስገባት ሴቶች እንደየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ተግባራትና እሴት በሚጨምሩ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ስራዎች እንዲሰማሩ የሚደረግ መሆኑንም ሚኒስተሯ ገልጸዋል።            

ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች በተመረጡ ዞኖች ሥራው እንደሚጀመር ጠቁመው፣ በቀጣይ የተገኙ ተሞክሮዎችን የማስፋፋት ሥራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።           

በአሁኑ ወቅትም ሥራውን ለመጀመር ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል።                

እንደ ወይዘሮ ደሚቱ ገለጻ፣ ኮሚቴው እስከታችኛው እርከን መዋቅሩን በመዘርጋት በወረዳ ደረጃ የሚገኙ ሴቶችን የማደራጀትና ወደ ምርት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ያከናውናል።                       

መድረኩ በዕቅዱ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ከመያዝ ባለፈ በየደረጃው የሴቶች የሕብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየን እንዲመሰርቱ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ማድረግ በሚቻልበት ላይ በጋራ ለመምከር ያለመ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡                   

የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው፣ የግብርና ኢንቨስትመንት በትንሽ ጉልበትና ወጪ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡             

በተለይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ሰፊ የገበያ እድልን ለመፍጠርና ግብርናን ለማዘመን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡                

በመሆኑም ሴቶች የቆጠቡትን ገንዘብ መልሰው በመበደርና  ለሥራቸው በማዋል የላቀ ውጤት ለማምጣት የሚችሉበትን ሁኔታ ይፍጥራል።              

በገጠር በአነስተኛ ቦታ ላይ እንስሳትን ማድለብና ማርባት፣ የጓሮ አትክልትና ቅመማ ቅመም ማምረትና ማቀነባበር ከፍተኛ ጥቅም እንደሚገኝበት በተግባር ተረጋግጧል።                     

ለሁለት ቀናት በተካሄደው አገር አቀፍ መድረክ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የሴቶች አደረጃጀቶች፣ የሕብረት ስራ ማህበራትና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2009 ኢትዮጵያ፣ ከቦትስዋናና ከዚምባብዌ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቷን ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለጸች።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከዚምባብዌና ቦትስዋና አቻዎቻቸው ጋር በሁለትዮሽና በአፍሪካ ጉዳዮች ዙሪያ በተናጠል ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱን የተከታተሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለሰ አለም እንደገለጹት፤ አገሮቹ በሁለትዮሽ የጋራ ስምምነቶች ላይ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በአፍሪካ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያ ለዚምባብዌ  ያላትን ልምድ ለማካፈልና ታሪካዊ ግንኙነት ለማስቀጠል  በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውንም ተናግረዋል።

የዚምባብዌው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሲምበራሼ ሙምበንጋዊ በወቅቱ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ለዚምባብዌ  ነጻነቷን እንድታገኝ ከማገዝ ጀምሮ እስካሁን በርካታ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን አንስተዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን እድገት አድንቀው፤ ዚምባብዌም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማጠናከር በጋራ እንደምትሰራ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ከቦትስዋና አቻቸው ፔሎኖሚ ቬንሶን ሞይቶይ ጋር በሁለትዮሽና በዓለምአቀፋዊ  ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅትም የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለመመስረት መስማማታቸውን ነው ቃል አቀባዩ አቶ መለሰ  የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያና ቦትስዋና ከአዲስ አበባ ጋቦሮኒ ቀጥታ የአየር በረራ ለመጀመር እ.ኤ.አ በ2013 መስማማታቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም ከዚምባብዌ ጋራ በቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመስራት እ.ኤ.አ በ2014 የመግባቢያ  ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2009 ኢትዮጵያ ለቀጣናው አገሮች የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማስፋት ጠንክራ መስራት እንደሚጠበቅባትና ድጋፍም እንደሚያደርግ የአፍሪካ ኅብረት ገለጸ።

በኅብረቱ የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ጉዳዮች የኃይል ዘርፍ ዳይሬክተር ራሺድ አብደላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በውሃ ኃይል በመጠቀም ስኬታማ ሥራ ማከናወን ላይ ትገኛለች።

ዳይሬክተሩ ሚስተር አብደላ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሌሎች ጎረቤት አገሮች ማቅረብ ጀምራለች። በቀጣይም የቀጣናው አገሮች ከኢትዮጵያ ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት የሚጠብቁ በመሆኑ የበለጠ ልትሰራ ይገባል። ለዚህም ኅብረቱ የተለያዩ ድጋፎች ያደርጋል።

 “ኢትዮጵያ በዚህ ብቻ ሳይሆን በእንፋሎት ኃይልም እምቅ አቅም አላት” ያሉት ሚስተር አብደላ፤ የአፍሪካ ኅብረት ለስምንት የእንፋሎት ፕሮጀክቶች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ አፍሪካን በኤሌትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር እንደ አህጉር ለሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ጥሩ ማሳያ ናት።

አፍሪካን በሁሉም መስክ ለማስተሳሰር የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ኅብረቱ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ዘርፉን በበለጠ ለማሳደግ ባለኃብቶችም እንዲሳተፉ ማድረጉ አዋጭ መሆኑን ሚስተር አብደላ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ27 የኤሌትሪክ ኃይል ልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ ያደርጋል።  

ኢትዮጵያ ከውሃ 45 ሺ ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ ኃይል 20 ሺ ሜጋ ዋት፣ ከእንፋሎት ደግሞ ከአምስት ሺ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም እንዳላት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

አገሪቷ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ማብቂያ ከውሃ 17 ሺ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት አቅዳ እየሰራች መሆኑም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘ መረጃ ያሳያል።   

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2009 በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ወዳ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲቻል የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ተግተው እንደሚሰሩ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የሚያሰለጥናቸው ከፍተኛ አመራር አባላት ተናገሩ።

አመራር አባላቱ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ቦሌ አራብሳ የሚገኙ 20/80፣10/90 እንዲሁም ሃያት የሚገኘው 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከጎበኙዋቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ የአማራ፣ የሐረሪ፣ የኦረሚያ ክልሎች ከፍተኛ አመራር አባላት ለኢዜአ ሪፖርተር እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ እነዲደርስ የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ።

የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ እስማኤል እንደገለጹት፤ጉብኝቱ በቀጣይ በአገሪቷ የእድገት ጉዞ ላይ የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል።   

እንደ አቶ እድሪስ ገለጻ፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፈላጊ ሰው እጅግ ከፍተኛ እንደመሆኑ ቤቶቹ ተገንብተው በፍጥነት ለዜጎች እንዲደርሱ ማስቻል ላይ የላቀ ትኩረት ይጠይቃል። 

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል አሰፋ በበኩላቸው፤ ''መንግሥት ለቤት ልማቱ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ባደረግነው ጉብኝት ተመልክተናል'' ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን ከበለጸጉት አገሮች ተርታ ማሰለፍ የከፍተኛ አመራር አባላትን ጨምሮ የሁሉም ዜጋ የተቀናጀ ስራ መሆኑን መገንዘባቸውን ነው የተናገሩት።

የሐረሪ ክልል ባህል ቢሮ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሀሰናት አቡበከር እንዳሉት፤ ግንባታው ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ባሻገር ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎችና አረጋዊያን ማዕከላትን የመሳሰሉ መሰረተ ልማትን ያሟላ መሆኑ ለሌሎች አካባቢዎች ጥሩ ተሞክሮ ይሆናል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የኢኮኖሚ እድገቱ ማሳያ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሯ፤ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን እድገት ለማስቀጠል የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።   

የኦሮሚያ ክልል ሮቤ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታጁዲን መሀመድም በበኩላቸው፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት መርሃ ግብር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ከፍተኛ አመራር አባላት ቦሌ አራብሳ ፍሳሽ ማጣሪያን፣ የአዲስ አበባ ሙዝየምና የሰማዕታት ሀውልትንም ጎብኝተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ሐረር ሰኔ 25/2009 በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ጥንታዊና ባህላዊ ቅርሶችን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የጥናትና ምርምር ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን የሐረማያ፣ ድሬዳዋና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ። 

በምስራቅ ኢትዮጵያ ጥንታዊና ባህላዊ ቅረሶች ላይ አተኩሮ ለሁለት ቀናት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ የነበረው ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ትናንት ተጠናቋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የሐረማያ፣ ድሬዳዋና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር መሳፍንት ታረቀኝ እንደተናገሩት፣ ምስራቁ የአገሪቱ ክፍል የበርካታ ባህላዊና ጥንታዊ ቅርሶችና ታሪኮች ባለቤት ነው።

በአካባቢው በሚገኙ ቅርሶችና ባህላዊ ትውፊቶች ላይ ብዙ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ባለመከናወናቸው ከዘርፉ መገኘት ያለበት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሳይገኝ ቆይቷል።

ድሬዳዋ ከንግድ ማዕከልነቷ ባለፈ የታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ ዩኒቨርሲቲው በቅርስ አጠባበቅና አያያዝ ላይ የጥናትና ምርምር ሥራ በማከናወን በተለያዩ ጆርናሎች ከማሳተም ባለፈ የማስተዋወቅ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር አቶ ተስፋሚካኤል ተሻለ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በኢትዮ ሶማሌ ባህል፣ ታሪክና በአካባቢው ባሉ የመስህብ ስፍራዎች ላይ የጥናትና ምርምር ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ መምህሩ ገለጻ፣ በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ መከናወን የብሔሩ ተወላጆች የኋላ ታሪካቸውን ተረድተው ለሌሎች እንዲያስተላልፉና ታሪካዊና ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎችን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው።

"ምስራቅ ኢትዮጵያ የዘመናዊ ስልጠኔ በርና ባህላዊና ሃይማኖታዊ የእርቅ ስነ ስርዓት የሚከናወንበት ስፍራ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ጥናት አልተካሄደበትም" ያሉት ደግሞ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ ናቸው።

በአካባቢው የሚገኙትን ባህላዊና ጥንታዊ ቅርሶችን ከቱሪዝም ልማቱ ጋር አቆራኝቶ ለኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር የጀመረውን የጥናትና ምርምር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ የኦጋዴን ሕዝብ አኗኗርና ሌሎች ትውፊቶች ላይ የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ መመርቂያ ጽሁፋቸውን የሰሩትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ባልደረባ ዶክተር ሳሙኤል ነጋሽ በበኩላቸው፣ ምስራቁ የአገሪቱ ክፍል በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍ ትልቅ ሀብት እንዳለው ገልጸዋል።

"ይሁንና የእነዚህ ሕዝቦች ጥንታዊና ባህላዊ ቅርሶች እንዲሁም ታሪኮቻቸው አልተጠኑም፤ አልተዳሰሱም" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መስፋፋት ተረስተው የቆዩ ታሪካዊና ጥንታዊ ሀብቶችና ቅርሶች እንዲታወሱ አድርጓል።

ለአገርና ለህዝብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኙና ሌሎች እንዲያውቃቸው እየተደረገ ያለው ጥረትም አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

በጥናትና ምርምር ስራውም የፌዴራልና የክልል መንግስታት ባለድረሻ አካላትና ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከተቋማቱ ጋር ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በምስራቅ ኢትዮጵያ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ታሪካዊ የጀጎል ግንብ፣ የባቢሌ ትክል ድንጋይ፣ ዋሻዎች፣ የዋሻዎች ስዕልና ፍል ውሃ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ባህላዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ የፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ራንቡ መኖሪያ ቤት፣ ሙዚየሞች፣ አድባራት፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የእርቅ ስነ ስርዓት፣ የጅብ ምገባ ትርኢትና ሌሎችም ቅርሶች ይገኛሉ፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ሰኔ 25/2009 የአማራ ክልል መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር የህዝብ ግንኙነት አደረጃጀት አማካሪ አቶ አለምነው መኮንን ገለጹ።

ከደቡብ ወሎ ዞን ሁሉም ቀበሌዎች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ 300 በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ ተካሄዷል፡፡

አቶ አለምነው መኮንን በውይይቱ ላይ እንደገለፁት የክልሉ መንግስት ለወጣቶች በሰጠው ልዩ ትኩረት በዚህ ዓመት ብቻ ከ600 ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡

የስራ እድሉ የተፈጠረው በክልሉ ከተመዘገቡት ከ930 ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶች መካከል ነው፡፡

በዓመቱ የተፈጠረው የስራ እድል አበረታች ቢሆንም ከወጣቶቹ ፍላጎትና ብዛት እንጻር ግን ገና መከናወን ያለባቸው ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

በተለይ በአንዳንድ ቦታ የሚስተዋሉ የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስና የወጣቱ የስራ ተነሳሽነት ማነስ እቅዱን ሙሉ በሙሉ ላለመሳካቱ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

መንግስት ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ  ድጋፎች ባሻገር ወጣቶች በራሳቸው ቁርጠኝነትና የይቻላል መንፈስ በመነሳሳት የተሻለ እምርታ ለማስመዝገብ ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አቶ አለምነው አስገንዝበዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እጅኩ መላኬ በበኩላቸው የወጣቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የተሄደበት መንገድ ረጅም ቢሆንም አሁንም በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ችግሩ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚሻም ገልፀዋል፡፡

መንግስትና አጋር አካላት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ወጣቶች ከአፍራሽ ኃይሎች እንቅስቃሴ ራሳቸውን በመጠበቅ እና ልማታዊ አስተሳሰብ በመገንባት አገራቸውን በማልማት ራሳቸውን ለመጥቀም ቆርጠው መነሳት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የቃሉ ወረዳ 02 ቀበሌ ወጣት ዳዊት አሰፋ በሰጠው አስተያየት መንግስት ከመቸውም ጊዜ በተሻለ መልኩ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም አሁንም ቀላል የማይባሉ ችግሮች አሉ።

በዚህ አመት ከወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር መለቀቅ ጋር ተያይዞ የተሻለ ተሰፋ የነበራቸው ቢሆንም የብድሩ መዘግየት በጠበቁት መልኩ ለመንቀሳቀስ እንዳላስቻላቸው ተናግሯል፡፡

ከመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የመጣችው ወጣት ዘውድዓለም አማረ በበኩሏ መንግስት በተለይ ለሴቶችና ወጣቶች በሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ ሴቶች በሁለንተናዊ መልኩ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

ወደፊት በተለይ ሴቶች የይቻላል መንፈስ በማሳደግ በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በራሳቸው ላይ እምነት ማሳደር እንደሚጠበቅባቸውም ገልጻለች።

ላለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደው የውይይት መድረክ በፌዴራሊዝም ስርዓት ግንባታ፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በ2009 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2009 የአፍሪካ አገሮችን ለማስተሳሰር የተጀመሩ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ።

በኅብረቱ የመሠረተ ልማትና ኃይል ኮሚሽነር ዶክተር አቦ-ዘይድ አማኒ በመሠረተ ልማት፣ በኤሌትሪክ ኃይልና ዶት አፍሪካ የአተገባበር ሂደትን በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሯ አማኒ እንደገለጹት፤ ኅብረቱ በአህጉሪቷ የሚካሄዱ መሰረተ ልማቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከተቋራጮችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት የድጋፍና ክትትል ስራ ያከናውናል።

የአህጉሪቷ አጠቃላይ መሠረተ ልማት ግንባታ ተግዳሮቶች እንዳሉት ያስታወሱት ኮሚሽነሯ፤ ፕሮጀክቶቹ በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ኅብረቱ ጥረት እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

እንደኮሚሽነሯ ገለጻ፤ ቀደም ሲል የተከናወኑት መሠረተ ልማት ግንባታዎች ለአገሮቹ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቃሜታ በሚውል መልኩ አልነበረም። ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሱት ቅኝ ገዥዎች የአገሮቹን የተፈጥሮ ሃብቶች ለመቀራመት የዘረጉት መሆኑን ነው።

ስለዚህ የአፍሪካ አገሮች በመሠረተ ልማት ዳግም በመተሳሰር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲችሉ መምከራቸውን አውሰተው፤ አገሮቹ እ.ኤ.አ በ1991 በናይጄሪያ አቡጃ የተስማሙበትን "በተቀናጀ መሠረተ ልማት የአፍሪካ ትስስር" በ1994 ማጽደቃቸውን ነው ያስታወሱት።

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ፤ አገሮቹ ወደ ስራ ሲገቡ የአፍሪካ መሠረተ ልማት መርሃ ግብር መሪ እና የትግበራ እቅዶችን ይዘዋል።  

እ.ኤ.አ በ2012 በአፍሪካ በአዲስ አበባ በተካሄደው 24ኛው የኅብረቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ የአገሮቹ መሪዎች የአፍሪካ የመሠረተ ልማት መርሃ ግብር አተገባበርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል። 

በዚህም አገሮቹን በመንገድ በማስተሳሰር የትራንስፖርት ዘርፉን ለማጠናከር ማቀዳቸውን ያስታወሱት ዶክተር አማኒ፤ ኅብረቱ በአጉሪቷ ምቹ የንግድ ቀጣና ለመፍጠር ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል። 

እ.ኤ.አ በ2028 አህጉሪቷን በቀጣናዊ የተቀናጀ የትራንስፖርት መረብ ለማስተሳሰር የ172 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተይዞ እየተሰራ ነው።

በዚህም የትራስፖርት ዘርፉ ስለሚጠናከር በአገሮቹ መካከል ምቹ የንግድ ትስስር እንዲኖር ለማድረግ እንደሚያስችልም ከኅብረቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

አገሮቹ በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ታግዘው ምርቶቻቸውን በኢንተርኔት መገበያየት እንዲችሉ እ.ኤ.አ 2016 ያቋቋሙት ‘ዶት አፍሪካ’ ለአገሮቹ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

‘ዶት አፍሪካ’ "አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ" በሚል በ2016 የተቋቋመ፣ በኢንተርኔት በመታገዝ  ኩባንያዎች፣ ድርጅቶች እና ነጋዴዎችን ለመገበያየት የሚያስችል ነው።                  

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምቴ ሰኔ 25/2009 የአርጆ ዲዴሣ ስኳራ ፋብሪካ ያጋጠመውን የግብዓት እጥረት ለማቃለል በዘንድሮው የመኽር እርሻ 1 ሺህ 500 ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የፋብሪካው የእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚጀና ቢቅላ ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካው እስከዛሬ ሲያለማ ከነበረው 3 ሺህ 400 ሄክታር መሬት በተጨማሪ በተያዘው ክረምት 1 ሺህ 500  ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት እየሰራ ነው።

ፋብሪካው የግብዓት እጥረቱን ለመቋቋም በሸንኮራ አገዳ ለመሸፈን ካቀደው አዲስ መሬት ውስጥ 940 ሄክታር ታርሶና ለስልሶ የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 510 ሄክታር የሚሆነው በሸንኮራ ዘር ተሸፍኗል።

ቀሪውን መሬት እስከ ሰኔ መሸረጫ ድረስ ለማልማት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቁመዋል።

የሸንኮራ አገዳ ልማቱ እየተካሄደ ያለው በዝናብ ውሃ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፣ ከሰባት ዓመት በፊት የተጀመረው የመስኖ ግድብ ግንባታ መጓተቱንና እስካሁንም ግንባታው 48 በመቶ ላይ ብቻ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተለይ በዲዴሣ ወንዝ ግራና ቀኝ ባለ 90 እና 70 ኪሎ ሜትር የካናል ሥራ አለመጀመሩ ፋብሪካው በመስኖ የሸንኮራ አገዳ ልማቱን እንዳያስፋፋ እንቅፋት እንደሆነበት ተናግረዋል።

የፋብሪካው ዋና ችግር የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ መጓተት ብቻ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ሚጀና፣ የኤሌክተሪክ ኃይልና የመሬት አቅርቦት ችግር መኖሩንም ገልጸዋል።

ፋብሪካው በውጭ ባለሀብት በነበረበት ጊዜ ይዞታው በውል ደረጃ 28 ሺህ ሄክታር መሬት ነው ቢባልም መሬቱ ተከልሎ ወሰኑ አለመታወቁን ጠቁመዋል።

ባለሀብቱ ፋብሪካውን ለመንግስት ሲያስተላልፉ በሸንኮራ አገዳ የለማው ሦስት ሺህ 400 ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑንም አመልክተዋል።

ይህም በመሬት አቅርቦት ላይ ችግር እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት ከኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቢሮ፣ ከምስራቅ ወለጋ፣ ከቡኖ በደሌ እንዲሁም ከጅማ ዞኖች ጋር በመሆን የፋብሪካው ይዞታ የሚከበርበትን ሁኔታ ለማመቻት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፋብሪካው የሕዝብ ተሳትፎና ልማት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ፋንታሁን በበኩላቸው፣  ፋብሪካው እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ካለማው 2 ሺህ 73 ሄክታር መሬት ላይ 126 ሺህ 265 ቶን የሸንኮራ አገዳ ምርት በመሰብሰብ ከ118 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር አምርቷል።

ፋብሪካው ያለበትን የግብዓት፣ የመስኖ ፕሮጀክት መጓተትና የኃይል አቅርቦት እጥረት ለማቃለል ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ደብረ ብርሃን/ወልዲያ ሰኔ 25/2009 የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 231 ተማሪዎች ዛሬ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ አስመረቀ፡፡

የወልዲያ መምህራን ከሌጅ ደግሞ አንድ ሺህ 269 እጩ መምህራን በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተፈራ በስነ ስርዓቱ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 66ቱ በሁለተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ ናቸው፡፡

ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል ደግሞ አንድ ሺህ 200 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ተመራቂዎችም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ወገናቸውንና ሃገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት 14 ሺ 800 ተማሪዎችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሰልጥኖ በማስመረቅ የተጣለበትን ሃገራዊ ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

ከፍተኛ ውጤት በማምጣ የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ተመራቂ ማህሌት ጌታሁን በበኩሏ ''ሳይማር ያስተማረኝን ወገኔን ከአድሎና ከሙስና በፀዳ መልኩ በታማኝነት ለማገልግል ተዘጋጅቻለሁ'' ብላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ የወልድያ መምህራን ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን አንድ ሺህ 269 እጩ መምህራን በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡

የኮሌጁ ዲን አቶ ግርማይ ሹምየ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በቋንቋ፣ በሂሳብ፣ በተፈጥሮና በማህበራዊ ሳይንስ፣ በሥነ ውበትና በሥነ ትምህርት ሰልጥነው ከተመረቁት መካከል 563ቱ ሴቶች ናቸው።

እጩ መምህራኑ የሙያዎች ሁሉ እናት በሆነው የመምህርነት ሙያ ሲገቡ ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች በመስጠት መንግስትና ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የኮሌጁ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበባው ሲሳይ በበኩላቸው መምህራኑ ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በተለይም የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንኑ ለማሳካት ተመራቂዎች በኃላፊነት መንፈስ መስራትና ማሳከት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከኮሌጁ አንደኛ በመሆን የዋንጫና የገንዘብ ተሸላሚ የሆነው እጩ መምህር አበበ ባህሩ በበኩሉ በሙያው መልካም ዜጎችን ለማፍራት ተግቶ እንደሚሰራ ገልጿል።     

የወልድያ መምህራን ኮሌጅ ባለፉት ሰባት ዙሮች ከ8 ሺህ 200 በላይ እጩ መምህራንን አሰልጥኖ ወደ ስራ ማሰማራቱ ታውቋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ