አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 17 July 2017

ባህር ዳር ሐምሌ 10/2009 የአማራ ክልል ምክር ቤት ለ2010 በጀት ዓመት ከ37 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ።

በጀቱን በቁጠባ በመጠቀም የህዝቡን የልማት ጥያቄ መፍታት እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል።

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን እሸቴ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የበጀት ቀመር እንዳስታወቁት በጀቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው።

በጀቱ ጭማሪ ያሳየው በክልሉ ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ አቅም በማደጉና የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት በመሰጠቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የበጀቱ ምንጩም ከ11 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ የሚሆነው ከክልሉ የተለያዩ ገቢዎች፣ ከ24 ነጥብ 8 ቢሊዮን የሚበልጠው ከፌደራል መንግስት የበጀት ድጐማ ቀሪው ከተለያዩ ገቢዎች የሚገኝ ነው።

በዚሁ መሠረት ከተመደበው በጀት ውስጥ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚበልጠው ለገጠር መንገድ፣ ለመስኖና ንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ እንዲሁም ለከተሞች የስራ እድል ፈጠራና መሰረተ ልማት ማስፋፋት ይውላል፡፡

ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ለኢንዱስትሪ መንደሮች፣ ሸዶችና ፓርኮች ግንባታና በአበባ እርሻ ልማት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የመሬትና የመሰረተ ልማት ዝግጅትና ለአቅም ግንባታ ተመድቧል።

ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በልማት ወደ ኋላ በቀሩ አካባቢዎች ለሚቀረፁ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የተመደበ ሲሆን ሲሆን 775 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለድንገተኛ አደጋዎች መጠባበቂያ ይውላል።

በተጨማሪም 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለቢሮዎች መደበኛና ካፒታል ስራዎች፣ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለደመወዝ መመደቡን ተናግረዋል፡፡

ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ  አንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን ቀሪው በጀት ለትምህርት፣ ለጤናና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች እንደሚውል አስታውቀዋል፡፡

በበጀት ቀመሩ ድህነት ተኮር የሆኑ ዘርፎች ትልቁን የበጀት ድርሻ እንዲይዙ መደረጉንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው በጀቱ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚፈቱ የልማት ስራዎችን መሰረት ተደርጎ ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል።

በ''ጀት በመመደብ ዘላቂ ለውጥ አይመጣም'' ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ የተሻለ ገቢ መሰብሰብና ወጪን በቁጠባ በመጠቀም እንዲሁም የህበረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ በበኩላቸው የበጀት ድልድሉ ያለፈውን ዓመት ወጪና የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም የክልሉን ገቢ የመሰብሰብ አቅምና የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን  ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

በጀቱ በተቀመጠለት አግባብ ተግባራዊ እንዲሆንና ለኢኮኖሚ እድገቱ ተጨባጭ ለውጥ አንዲያመጣ ተጠያቂነት በሰፈነበት መንገድ ለስራ እንዲውል አስፈፃሚው አካል በልዩ ትኩረት ሊከታተል እንደሚገባ  አሳስበዋል።

የምክር ቤት አባላቱም የበጀት አጠቃቀሙን በየጊዜው ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ሚናቸውን እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።

የበጀት ቀመሩ በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የፍርድ ቤቶችንና የምክር ቤት ጽህፈት ቤቱን የ11 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሞ አፅድቋል።

የምክር ቤቱ 5ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ በነገው እለት የችግኝ ተከላ በማካሄድና የተለያዩ ሹመቶችን በማፅደቅ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።