አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 16 July 2017

አዲስ አበባ ሃምሌ 9/2009 ኢትዮጵያ በዓለም ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በአምስተኛ ደረጃ አጠናቀቀች።

ለአምስት ቀናት በኬኒያ መዲና ናይሮቢ ሲካሄድ የቆየው የዓለም ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ተጠናቋል።

ዛሬ ከሰዓት በተካሄደው 3 ሺህ ሜትር የወንዶች ፍጻሜ ውድድር አትሌት ሰለሞን ባረጋ በአንደኝነት በማጠናቀቅ ለአገሩ አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።

በበርካታ ተመልካች የተሞላው ካሳራኒ ስታዲየም አትሌት ሰለሞን በውድድሩ የመጨረሻ ዙር ከኬኒያውያን አትሌቶች ጋር ከፍተኛ ፉክክር አድርጓል።

አትሌት ሰለሞን ውድድሩን ለመጨረስም ሰባት ደቂቃ 47 ሰከንድ  ከ16 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት የራሱን ሰዓት በማሻሻል ነው ያሸነፈው።

በዚሁ ውድድር ሁለተኛና ሶስተኛ ኬኒያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ለአገራቸው ማስገኘት ችለዋል።

ለሰለሞን ማሸነፍ እገዛ የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ምልኬሳ መንገሻ አራተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

በ800 ሜትር የሴቶች ፍጻሜ ውድድር አትሌት ሂሩት መሸሻ ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

ለአምስተኛ ወርቅ ይጠበቅ የነበረው በሁለት ሺህ ሜትር የወንዶች መሰናክል የፍጻሜ ውድድር በኬኒያዎቹ የበላይነት ተጠናቋል።

በመጨረሻው ዙር በኬኒያዊያንና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ፉክክር የኬኒያ አትሌቶች አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

አትሌት አለሙ ኪቴሳ ደግሞ ውድድሩን በሦስተኝነት በማጠናቀቅ የመጨረኛውን የነሐስ ሜዳሊያ ለአገሩ ማስገኘት ችሏል።

ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፣ ሦስት ብርና አምስት ነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ኢትዮጵያ ከዓለም አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

በመሆኑም በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት ታሪክ ከፍተኛው ሜዳሊያ የተመዘገበበት ከመሆኑም በላይ በመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ውድድር ሆኗል።

በዚሁ ሻምፒዮና ደቡብ አፍሪካ በአምስት ወርቅ በሦስት ብርና በሁለት ነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ አስር ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ በመሆን አጠናቃለች።

ቻይና እና ኩባ በተመሳሳይ አምስት ወርቅና ሁለት ብር ያገኙ ቢሆንም ቻይና አራት ነሐስ ኩባ አንድ ነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት እንደቅደም ተከተላቸው ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አዘጋጇ ኬኒያ በአራት ወርቅ፣ በሰባት ብርና በአራት ነሐስ በድምሩ 15 ሜዳሊያዎች ወደ ካዝናዋ በማስገባት በአራተኝነት ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

ከ159 አገሮች የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ አትሌቶች በተሳተፉበት አስረኛው ዓለም አቀፍ ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በስድስት የውድድር ዓይነቶች 12 ወንዶችና 11 ሴቶች በድምሩ በ23 አትሌቶች ተወክላለች።

የልዑካን ቡድኑ ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ስፖርት

ባህር ዳር ሃምሌ 9/2009 በአማራ ክልል የሚገነቡ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ግንባታ መጓተትና የጥራት ችግር አስፈፃሚው አካል ተገቢውን ክትትል በማድረግ ሊፈታው እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት ገለፁ።

የመንገድ፣ የውሀና የመብራት ሃይል አቅርቦት እጥረት  ህዝቡን ክፍኛ እያማረሩት እንደሆነ ተጠቁሟል።

የምክር ቤት አባላቱ እንደገለፁት በየአካባቢው የሚገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማት ተገቢውን ደረጃ ያልጠበቁ፣ ከሚፈለገው ጊዜ በላይ የተጓተቱ፣ የድልድይ ስራቸው ያልተጠናቀቁና የአዳዲስ መንገድ ግንባታም ችግር አለ ብለዋል።

የውሃ ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት የማይሰጡ፣ የአገልግሎት ጀምረው የሚያቋርጡ፣ ተደራሽ ባልሆነባቸው የግንባታ አለመኖር፣ ግንባታቸው በጊዜው ተሰርቶ ለአገልግሎት አለመብቃት የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን የምክር ቤት አባላቱ ገልፀዋል።

የመብራት ሃይል አቅርቦት እጥረትም ከሁሉም ችግሮች የከፋውና በቀላሉ መፍትሄ ለመስጠትም ያልተቻለበት የአሰራር ዝርክር ክነት የሚስተዋልበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በዚህ እጥረትም የትምህርት ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችና ተጠቃሚው ማህበረሰብ ክፍኛ እየተጎዳ መሆኑን ተዘዋውረው ባደረጉት የህብረተሰብ ውይይት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት የሆኑትን ችግሮች ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በፍጥነት ሊፈቱ እንደሚገባ ባቀረቡት ሪፖርት አሳስበዋል።

የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ዛንጥራር አባይ በበኩላቸው ከመንገድ ዝርጋታ ጋር በተያያዘ በዚህ በጀት ዓመት በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ፕሮግራም አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር መስራት ተችሏል።

መሰራት ካለባቸው 300 ድልድዮችም በዚህ ዓመት 78 ድልድዮች እየተሰሩ መሆናቸውንና አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ለማካሄድም 60 መንገዶች ዲዛይን መሰራቱንና የክልል የበጀት አቅም እየታየ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጥራት ችግር ያለባቸውን መንገዶችም ተገቢውን ክትትል በማድረግ የማስተካከል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና በፌደራል የሚገነቡ መንገዶችም ክትትል በማድረግ ማስተካከያ እንዲደረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዲዛይን መቀያየር፣ የኮንትራክተሮች አቅም ውስንነት፣ የመብራት አቅርቦት እጥረትና የኤሌክተሮ ሜካኒካል እቃዎች አቅርቦት እጥረት ለውሃ ተቋማት መጓተት መሰራታዊ ችግሮች መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሞላ ፈጠነ ናቸው።

በተለይም የወረታ፣ የአዲአርቃይ፣ የደብረታቦር፣ የጎንደርና ሌሎች አነስተኛና ከፍተኛ ከተሞች ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ  ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት ቢደረግም ችግሮች እንቅፋት ሆነው መቆያታቸውን ጠቁመዋል።

የእነዚህንና የሌሎች የውሃ ተቋማትን በተቻለ መጠን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ ሁሉም ለተቋማቱ ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው የኢንዱስትሪዎች በፍጥነት መስፋፋት የከተሞች እድገታና መሰል ተያያዝ ምክንያቶች ለኤሌክትሪክ ሃይል እጥረትና መቆራረጥ ምክንያት ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ቢሆንም ችግሩን በቀላሉ በአጭር ጊዜ መፍታት አለመቻሉን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ ያስገባ ንቅናቄ ይደረጋል ብለዋል።

በመሆኑም ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ የህዝቡን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ ችግሮችን በመከታተልና በማስተካከል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም አቶ ገዱ አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ በእምቦጭ አረም፣ በሁሉን አውዳሚ የተምች ወረርሽኝ፣ የጎልማሶች ትምህርት እንቅስቀሴና የቀን ገቢ ግምት ትመናውን በሚመለከት በልዩ ሁኔታ መክሯል።

ምክር ቤቱ በርዕስ መስተዳደሩ የቀረበውን የ11 ወራት የእቅድ አፈጨፃፀም ሪፖርት ገምግሞ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን በነገው እለትም የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር ሪፖርቶችን ገምግሞ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሀምሌ 9/2009 የኦሮሚያ ጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልሉ መንግስት 320 ተቋማት ላይ ባካሄደው የሂሳብ አሰራር ኦዲት ክንውን ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ጉድለት ማግኘቱን ገለጸ።

የመስሪያ ቤቱ ዋና ኦዲተር አቶ ኤሌማ ቃምጴ በአዳማ አባገዳ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ላለው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ የ2009 ዓ ም የኦዲት ክንውን ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ በዚሁ ሪፖርታቸው እንደገለፁት ተቋሙ በ428 የክልሉ መንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ የገቢና ወጪ ሂሳብ አጠቃቀምን ጨምሮ በፋይናንስ አሰራር፣ የንብረት አያያዝና አስተዳደር ላይ የሂሳብና የአይነት ኦዲት አድርጓል።

በዚህም አብዛኛው ተቋማት ህጋዊ የፋይናንስ አሰራር የተከተሉ ቢሆንም 54 የሚሆኑት በገቢና ወጪ ሂሳብ፣ በፋይናንስ አጠቃቀም፣ በንብረት አያያዝና አስተዳደር ላይ የጎላ ችግር እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ከክልል ጀምሮ በዞን፣ ከተሞችና ወረዳዎች ድረስ ባሉ 320 ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ በተካሄደው የፋይናንስ ኦዲት ክንውን ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ የሂሰብ ጉድለትና የሂሳብ አጠቃቀም ችግር ማግኘቱን አመልክተዋል።

በዚህም ወደ መንግስት ካዝና መግባት ሲገባው ያልገባ 414 ሚሊዮን ብር በአዳማ፣ ሰበታ፣ ለገ ጣፎ ለገዳዲ ከተሞችና የሰበታ ሀዋስ ወረዳ የገቢዎች ባለስልጣን ላይ የታየ ጉድለት መሆኑን ገልፀዋል።

በአንዳንድ ተቋማት ላይ በሚታየው የወጪ ሂሳብ አስተዳደር አሰራር ግልፅነት የጎደለውና ለምዝበራ የተጋለጠ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኤሌማ በዚህም ከ628 ሚሊዮን ብር በላይ የሂሳብ  ጉድለት በኦዲት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

ይህ የሂሳብ ጉድለት ከታየባቸው መስሪያ ቤቶች መካከል ደግሞ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የኦሮሚያ ህንፃዎች አስተዳደር፣ የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ገንዝብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር፣ የቦቆጂ ከተማ አስተዳደር፣ የምስራቅ ሐራርጌ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ጽሕፈት ቤት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

አሳማኝ መስረጃ ሊቀርብበት ያልቻለ፣ ያለአግባብ ወጪ የሆነና የልተወራረደ 551 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ሂሳብ ደግሞ በኢሉአባቦራ፣በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ በኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅትና በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ማግኘቱን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የመንግስትን የወጪ አሰራር ሳይከተል ክፍያ የተፈፀመ 595 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር አስፈላጊው ሰነድ ካልቀረበበት ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ ሃሳብ መሰጠቱንና ለሚመለከታቸው አካለት ሪፖርት መደረጉን አመልክተዋል።

የኦዲት መስሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ በየደረጃው በሚገኙ የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ በተደረገው የንብረት አያያዝና አጠቃቀም፣ የግዥ አሰራር ላይ ችግር መኖሩን ለጨፌው በቀረበው ሪፖርት አመልክተዋል።

በዚህም የአዳማ ከተማ ጤና መምሪያ፣ የቡራዩ ከተማ ውሃና ፍሳሽና ገቢዎች ባለስልጣን፣ አዳሚ ቱሉ ግብርና ምርምር ማእከል፣ የሰበታ ከተማ ውሃና ፍሳሽ፣ የመንግስት ግዥ ኤጄንሲ፣ የክልሉ ጤና ቢሮና የመንገዶች ባለስልጣን እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡

በኦሮሚያ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ግንባታን ለማፋጠን በ2004  እና በ2005 ዓ.ም ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ግዥ የተፈፀመባቸው ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ማሽነሪዎች ለወረዳዎች ስለመድረሳቸው የሚያረጋግጥ ሰነድ እንዳልተገኘም የኦዲት ሪፖርቱ አመልክተዋል።

በኦዲት ግኝቱ ላይ የተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ አፈፃፀም እስካሁን 25 በመቶ ብቻ መሆኑንም ዋና ኦዲተሩ አቶ ኤሌማ በሪፖርታቸው ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሂሳብ አያያዝና አሰራር፣ የንብረት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የግዥ ሂደቱ ግልፅነት የተላበሰ ለማድረግና ለልማት የተመደበ በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አዳዲስ አሰራሮች መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም አሳስበዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ደብረ ብርሃን ሀምሌ 9/2009 የደብረብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለዘጠነኛ ጊዜ በተለያዩ  የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 1ሺህ  227 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ፡፡  

ተመራቂዎቹ ከአንድ እስከ ሶስት ዓመት ተኩል  ከደረጃ አንድ እስከ አምስት የተሰጣቸውን ትምህርት ተከታትለው  ያጠናቀቁ መሆናቸውንና ከመካከላቸውም  653  ሴቶች እንደሚገኙበት የኮሌጁ ዲን አቶ ድረሴ እሸቱ  ገልጸዋል፡፡

ዲኑ እንዳሉት ተማሪዎቹ የሰለጠኑት  በማኑፋክቸሪንግ ፣ ግንባታ  ፣አውቶ ሞቲቭ ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝምና ሆቴል ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጨምሮ  በ11 ዓይነት የሙያ ዘርፎች ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት ኮለጁ ከመማር መስተማሩ በተጓዳኝ  የማህበረሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ከ12በላይ የግብርና ቴክኖለጂዎችን  ለተጠቃሚዎች ማሰራጨቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም በበጋ መስኖ በስፋት የሚለማውን የቲማቲም  ምርት ሳይበላሽ  በማቆየት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን  እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ዲኑ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ለመስጠት ባለ ሶሰት ፎቅ ህንፃ ከ12 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለመገንባት ስራው መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡

ከተመራቂዎች መካከል አይናለም በጋሻው ሰልጥና በተመረቀችበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  ዘርፍ  ስራ ፈጠራ ለመስራት መዘጋጀቷን በሰጠችው አስተያየት ገልጻለች፡፡

በማንፋክቸሪንግ ዘርፍ የሰለጠነው ተመራቂ ክፍሌ  ሸዋንግዛው በበኩሉ በተማረው ሙያ ሰርቶ ለመለወጥ እንደሚተጋ ተናግሯል፡፡

ለተመራቂዎቹ ሰርተፊኬትና በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ሽልማት የሰጡት የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ታገል አምሳሉ ናቸው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ሀምሌ 9/2009 የጋምቤላ ግብርና ምርምር ተቋም የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግር የሚፈቱ 48 የምርምር ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ፡፡

ለአካባቢው  ሥነ  ምህዳር ተስማሚ የሆኑና ቀደም ሲል ተቋሙ በምርምር ያወጣቸው  የሰብል ዝርያዎችን  በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የማባዛት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ  ኮንግ ጆክ ለኢዜአ እንደገለጹት እያካሄዱ ያሉት የምርምር ፕሮጀክቶች የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን መሰረታዊ የቴክኖሎጂ ችግሮች ይፈታሉ ባላቸው የምርምር ዘርፎች ነው።

ሰብል፣እንስሳት፣ተፈጥሮ ሀብትና በሌሎችም  ማህበራዊና  ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ምርምሩ ያተኮሩባቸው ፕሮጀክቶች መሆኑን አመልክተዋል።

የምርምር ፕሮጅክቶቹ  33 ዘንድሮ የተጀመሩ አዲስ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 15  ደግሞ  ነባር  ናቸው፡፡

ከምርምር ፕሮጀክቶቹ መካከል በተለይ በቆሎ፣ ማሽላ፣ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ ቲማቲም፣ የእንስሳት ማድለብ፣ የአሳ ሃብትና ዶሮ እርባታ ላይ የማሻሻል ስራዎች ይገኙበታል።

በመካሄድ ላይ ያሉት እነዚሁ የምርምር ፕሮጀክቶች እስከ ሶስት ዓመት ባለው ጊዜ በማጠናቀቅ  ለተጠቃሚዎች የሚደርሱበት ሁኔታ እንደሚመቻች ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ተቋሙ ከምርምር ሥራዎች በተጓዳኝም  ቀደም ሲል በምርምር ያገኛቸውን አራት የሰብል ዝርያዎች በአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ማሳ ላይ የማባዛት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

እየተባዙ ያሉት የሰብል ዝርያዎቹ በሄክታር በቆሎ 33፣ ማሽላ 25፣ ለውዝ 30 ፣ሰሊጥ ደግሞ10 ኩንታል እንደሚያስገኙና ከተለምዶው  ዝርያዎች በእጥፍ ብልጫ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የምርምር ተቋሙ ድርቅን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን በማውጣት ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ለማዳረስ የሚያደረገውን የምርምር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም   አቶ  ኮንግ አውስተዋል፡፡

በተቋሙ የማህብረሰብ ኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ቻንኳት ካን በበኩላቸው "ተቋሙ በምርምር የተገኙ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ የማስፋትና የማስረጽ ስራዎችን እያከናወነ ነው" ብለዋል።

በተያዘው የምርት ዘመን በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ከአንድ ሺህ 700 በሚበልጡ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ማሳ ላይ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኩቶች ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጅካዎ ቾል በሰጡት አስተያየት በግብርና ምርምር ተቋም  በኩል የቀረበላቸው  የበቆሎ  ምርት ዘር ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ  መሆኑን ገልጸዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዮድ ፖች በበኩላቸው በግብርና ምርምር በኩል የተሰጣቸው  ምርጥ ዝርያዎች  ቀደም ሲል ከሚዘሯቸው  በቁመና ደረጃ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ግብርና ምርምር ተቋም ለክልሉ ተስማሚ የሆኑ የሰብልና የእንሰሳት ዝርያዎችን በመለየት የአካባቢውን አርሶና ከፊል አርብቶ አደር ተጠቃሚ ለማድረግ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

 

 

ፍቼ/ነቀምቴ ሀምሌ 9/2009 በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ከ264 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸው ተገለፀ፡፡

ከሐምሌ ወር መግቢያ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ ጳጉሜ  መጨረሻ ድረስ ይካሄዳል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያደታ ጭምደሳ እንዳስታወቁት በዞኑ17 ወረዳዎች በተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ170 ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

የዘንድሮው በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከኦሮሚያ ልማት ማህበር ጋር በቅንጅት የሚከናወን መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩት ወጣቶች  የማጠናከርያ ትምህርት፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገን፣ የአካባቢ ጽዳት እንዲሁም ለኤች አይቪ ህሙማን የቤት ለቤት ድጋፍና እንክብካቤ ጨምሮ በ14 ዋና ዋና የስራ ዓይነቶች  መሳተፍ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታዬ በበኩላቸው በዞኑ 13 ወረዳዎች ከ94 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል፡፡

ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው መስኮች መካከል የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የጤናና ሥነ-ተዋልዶ አገልግሎት፣ የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ፣ ችግኝ ተከላና አካባቢ ጥበቃ ይገኙበታል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ተማሪ ወጣት መገርሳ ፈዬ እንደሚለው ሳይማር ያስተማረውን ህብረተሰብ ባለው እውቀት ለመርዳት በፍቼ ሪፈራል ሆስፒታል እያገለገለ ነው።

''በተለይ  የኤች. አይ. ቪ ኤድስ እና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ ለህሙማን ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ሙያዊ እገዛ እያደረኩ ነው'' ብሏል።

ለታዳጊ ወጣቶች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆኑን የሚናገረው ደግሞ እጩ መምህር ተሻለ ድርብሳ ነው።

የ3ኛ ዓመት የስነ-ልቦና ተማሪ ብሌን ጉተማ በበኩሏ ፍቼ ከተማን ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግ ተናግራለች፡፡

Published in ማህበራዊ

አርባምንጭ ሀምሌ 9/2009 በአርባምንጭ ከተማ ባለ ሁለት ፎቅ ህንጻ  ተደርምሶ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ11 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የከተማው  ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ተመስገን አንጁሎ ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው ዛሬ ጠዋት ላይ የደረሰው በከተማው ዓባያ ክፍለ ከተማ ኩልፎ ቀበሌ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው መንደር ነው፡፡

በመንደሩ ንብረትነቱ የአቶ ወልደ ሰንበት ጋጋ የሆነ ባለሁለት  ፎቅ መኝታ ቤት ተደርምሶም  በመኝታ ቤቱ አልጋ ይዘው የነበሩ የአራት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ደግሞ በአርባምንጭ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ምክትል ኮማንደሩ አመልክተዋል፡፡

በህንፃው ፍርስራሽ ውስጥ ቀሪ ሰዎችን ለማግኘት ቁፋሮና የነፍስ አድን ስራው እንደቀጠለ  አስታውቀዋል፡፡

የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በበኩላቸው ግለሰቡ ህንፃውን የግንባታ ፈቃድ ሳያገኝ እየገነባ መሆኑ በመረጃ ተደርሶበት በህግ መጠየቁን ገልጸዋል፡                                                                          

ደረጃውን ሳይጠብቅ በድብቅ ማታ ማታ ግንባታውን በማካሄድ በህገ ወጥ መንገድ የመኝታ ቤት ኪራይ አገልግሎት  ሲሰጥ መቆየቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ህገ ወጥ ተግባሩ ቀደም ሲል ክስ ተመስርቶበት በህግ ሂደት ላይ እያለ አደጋው መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉንም አመልክተዋል፡፡       

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 9/2009 የመከላከያ እጅ ኳስ ክለብ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር አሸነፈ።

ከጥር 2009 ዓ.ም  ጀምሮ በ11 ክለቦች  መካከል ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።

በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ጅምናዚየም በተደረገው የመጨረሻ ውድድር መከላከያ ፌዴራል ፖሊስን በማሸነፍ ነው ዋንጫውን ያነሳው።

መከላከያ ፌዴራል ፖሊስን 34 ለ 31 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሻምፒዮን ሲሆን፤ ኮልፌ ቀራኒዮ በፕሪሚየር ሊጉ ፌደራል ፖሊስን ተከትሎ ሦስተኛ  ሆኖ አጠናቋል።

ኮልፌ ቀራኒዮ ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ፌዴራል ማረሚያ ቤትን 29 ለ 27 አሸንፎ ነው።

Published in ስፖርት

አዳማ ሀምሌ 9/2009 በዘጠኝ ወራት ውስጥ አዲስ አበባን የጎበኙ 650 ሺህ የውጭ አገር ቱሪስቶች በቆይታቸው ለተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ ከ31 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ሃጎስ እንደገለፁት በዓመቱ 675 ሺህ የውጭ ቱሪስቶች አዲስ አበባ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ እቅድ የተያዘ ቢሆንም እስከ ሶስተኛው ሩብ ዓመት ድረስ በ650 ሺህ  ቱሪስቶች ጎብኝተዋል፡፡

ቱሪስቶቹ ከጎበኙዋቸው የመስህብ ስፍራዎች መካከል ብሄራዊ ሙዚየምና እንጦጦን ጨምሮ 13 የአዲስ አበባ ባህላዊና ታሪካዊ ስፍራዎችና መዳረሻዎች ይገኙበታል ።

የቱሪስቶቹ ቆይታ በአማካኝ  12 ቀናት መድረሱንና ለአልጋ ፣ ለሆቴል መስተንግዶ ፣ ለአስጎብኚዎች ክፍያ ፣ ለባህላዊ ቁሳቁሶች ግዥና ለሌሎች አገልግሎቶች ከ31 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገዋል ።

የቱሪዝም ፍሰቱን ለማሳለጥ ቢሮው  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 720 ጎብኚዎች የሚመሩበት መፅሃፍና ካርታ  አዘጋጅቶ አሰራጭቷል ።

ወደ ከተማዋ የሚገባ ቱሪስት ያለማንም አስጎብኚ ጭምር ከተማዋን መጎብኘት እንዲችል የአዲስ አበባን የተለያዩ ቦታዎች የሚያሳይ የቱሪስት ካርታ በተመረጡ 17 ቦታዎች ላይ ተተክሎ ስራ ላይ መዋሉን ጠቁመዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ ቢሮው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የከተማዋን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን ለማበልጸግ ጥረት አድርጓል።

በተለይ ባህልና ኪነ-ጥበብን ዋንኛ የልማት ኃይል በማድረግ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

በቱሪዝም ዘርፍ ነባር ቅርሶችን የመጠገንና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት  አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ገብረፃዲቅ አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ እድሳት ተደርጎላቸው ስራ ከጀመሩት ነባር ቅርሶች መካከል የአዲስ አበባ ሙዚየም፣ የድልና የሰማእታት  ሐውልቶች ይጠቀሳሉ።

የራስ ቴያትር ቤትን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአዲስ መልክ ለመገንባት ቢታቀድም በወሰን ማስከበርና በተለያየ ምክንያት አለመጀመሩ በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ እጥረቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል ።

በቢሾፍቱ ከተማ ትናንት በተጀመረውና ለአራት ቀናት በሚካሄደው መድረክ ላይ ከወረዳ እስከ ማዕከል የሚገኙ የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሀምሌ 9/2009 ኢትዮጵያ በኬንያ እየተካሄደ ባለው የዓለም ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ነው።

ዛሬ የሚጠናቀቀው 10ኛው የዓለም ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዚህ በኋላ በአህጉር ደረጃ ብቻ እንዲካሄድ ተወስኗል።

እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች ሶስት ወርቅ፣ ሶሰት ብርና ሶሰት ነሐስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ኢትዮጵያ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በሻምፒዮናው ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፤ ከአራት ዓመት በፊት ዩክሬን ባስተናገደችውና የተሻለ ውጤት ከተገኘበት ስምንተኛው ሻምፒዮና በአንድ ነሐስ ይበልጣል። በቀሩት የፍጻሜ ውድድሮችም ተጨማሪ ሜዳሊያ እንደምታገኝ ይጠበቃል።

መለስ ንብረት በ800 ሜትር ወንዶች፣ ለምለም ሀይሉ በአንድ ሺ 500 ሜትር፣ አበራሽ ምንስዎ ደግሞ በሦስት ሺ ሜትር ሴቶች ወርቅ ያስገኙ አትሌቶች ናቸው።

የብር ሜዳሊያዎቹን ደግሞ ቶሎሳ ቦዲና በ800 ሜትር፣ አበበ ደሳሳ በአንድ ሺ 500 ሜትር ወንዶች፣ ስንዱ ግርማ በ1 ሺ 500 ሜትር ሴቶች አግኝተዋል።

በለጠ መኮንን፣ እታለማሁ ስንታየሁ እና ይታይሽ መኮንንደግሞ በ1 ሺ 500 ሜትር ወንዶች፣ በሁለት ሺ ሜትር መሰናክልና በሦስት ሺ ሜትር ሴቶች የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች ናቸው።

ዛሬ በሚጠናቀቀው የፍጻሜ ውድድር በ800 ሜትር ሴቶች ሂሩት መሸሻ፣ በሁለት ሺህ ሜትር መሰናክል እና ሦስት ሺ ሜትር ወንዶች ደግሞ ግርማ ድሪባና ሠለሞን ባረጋ ተጨማሪ ሜዳሊያ ያስገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በእነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወጣቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ በመገፋፋታቸው ይሄ "የተሻለ ውጤት" መምጣቱ ነው እየተገለጸ ያለው።

የአትሌቶችና የአሰልጣኞች ምርጫ ከሌላ ጊዜ በተለየ ከፍተኛ ቅሬታ ያልቀረበበትና ብቃትን መሰረት ያደረገ መሆኑም ለውጤቱ መገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ አንዳለው ተጠቁሟል።

በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአህጉር ደረጃ ብቻ እንዲካሄድ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ወስኗል።

የዓለም የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል ሥያሜ ሲካሄድ የነበረው ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ "የዓለም ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና" በሚል ሥያሜ ቢካሄድም መቀጠል አልቻለም።

በአፍሪካ ለሁለተኛ ጊዜ ከሰሃራ በታች ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ከሚያካሄዳቸው ውድድሮች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው እ.አ.አ. በ1999 በቢድጎስት፣ ፖላንድ ነበር።

ኢትዮጵያ ከተጀመረ ጀምሮ እየተሳተፈች ሜዳሊያ ስታገኝ እንደነበር ይታወሳል። በመጀመሪያው የፖላንዱ ሻምፒዮና አራት ብር በማግኘት ከዓለም 17ኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው።

በሀንጋሪ በተደረገው ሁለተኛው የዓለም ታዳጊ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ አንድ ወርቅ፣ ሁለት ብርና ሁለት ነሐስ አግኝታ ከዓለም 12ኛ ደረጃ ይዛ ስታጠናቀቅ፤

በካናዳ በተደረገው ሶስተኛው ሻምፒዮና አንድ ወርቅ፣ አንድ ብርና አንድ ነሐስ በማግኘት በድጋሚ 12ኛ ሆና ነበር የጨረሰችው።

ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ሞሮኮ ላይ የተካሄደውን አራተኛውን ሻምፒዮና ደግሞ በአንድ ወርቅ፣ በአንድ ብርና በአንድ ነሐስ 11ኛ ሆና አጠናቀቀች።

በቼክ ሪፐብሊክ በተካሄደው አምስተኛው ሻምፒዮና አንድ ወርቅ፣ አንድ ብርና ሁለት ነሐስ በመውሰድ 10ኛ ሆና ስታጠናቅቅ፤ በስድስተኛው የጣሊያኑ ሻምፒዮና በአንድ ወርቅ፣ በአንድ ብርና አራት ነሐስ ዘጠነኛ ሆና ነበር ውድድሩን ያጠናቀቀችው።

በፈረንሳዩ ሰባተኛው ሻምፒዮና ሁለት ወርቅ፣ ሁለት ብርና አንድ ነሐስ አግኝታ ስድስተኛ፤ በዩክሬኑ ስምንተኛው ሻምፒዮና ደግሞ ሶስት ወርቅ፣ ሶሰት ብርና ሁለት ነሐስ በመሰብሰብ ሶስተኛ ወጥታ ነበር።

ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው የኮሎምቢያው ዘጠነኛ ሻምፒዮና ደግሞ በሁለት ወርቅ፣ በሶሰት ብርና በሶስት ነሐስ አራተኛ ሆና ነበር የጨረሰችው።

በኬንያ ናይሮቢ ከ159 አገሮች የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ አትሌቶች እየተሳተፉበት ባለውና "የመጨረሻው ነው" በተባለው አስረኛው ውድድር ኢትዮጵያ በስድስት የውድድር ዓይነቶች 12 ወንዶችና 11 ሴቶች በድምሩ 23 አትሌቶች አሳትፋለች።

በታዳጊዎቹ እየተመዘገበ ያለው ውጤት በቀጣዩ የለንደን የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ ለሚወዳደሩ አትሌቶች ብርታት እንደሚሆን ተስፋ ተጥሏል። የልዑካን ቡድኑ ነገ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

 

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ