አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 15 July 2017

ሰመራ ሀምሌ 8/2009 እየተዳከመ የመጣው የሀገሪቱን የኦሎምፒክ ውጤት ለመሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ኮሚቴው በስፖርቱ ልማት ዙሪያ   ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራት በሚቻልበት ዙሪያ ትናንት በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተወያይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊወርጊስ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት  በአለም የኦሎምፒክ መድረክም ሆነ በሌሎች ውድድሮች ላይ ሃገሪቱ እያሰመዘገበች ያለው  ውጤቶች እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ለዚህም የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ያህል ተቀራርበው አለመስራትና ለስፖርተኞች በቂ ማበረታቻ  አለመኖሩ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡

ችግሩን  ለመፍታት ኮሜቴው ከሚመለከታቸው  አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመው በሰመራ የተዘጋጀው ውይይትም መቀራራብን የሚያጠናክር ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱን  ሰንደቅ-ዓላማ በተለያዩ የአለም  አደባባዮች ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማስቻል ከፍተኛ የገጽታ ግንባታ እየበረከተ የሚገኘውን ስፖርት መንግስት  መደጎምና መደገፍ እንዳለበት ዶክተር አሸብር ጠቁመዋል፡፡

እየተዳከመ የመጣው  የኦሎምፒክ ውጤት ለመሻሻል  በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የስፖርት መሰረተ-ልማትን  በጥራትና በብዛት ተደራሽነት በማሳደግ በኩል ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ  በተለይም የአፋር ክልል የተሻለ ውጤት ሊያሰመዘግብ በሚችልባቸው ስፖርቶች   አስፈላጊውን የድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኃለፊ አቶ መዐር አሊሴሮ የክልሉን ስፖርት ለማሳደግ ብሎም ወጣቶች ከአልባሌ ቦታ ርቀው ብቁ ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ በ8 የስፖርት ዓይነቶች 69  ታዳጊ ወጣቶች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክልሉ በተለይም በእግር ኳስና አትሌቲክስ መስክ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራበት ክልሉና ሀገር መወከል የሚችሉ ውጤታማ  ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ  ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በውይይቱ  ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት  ስፖርቱን ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበለጠ ተቀራርበው በቅንጅት መስራት አስፈላጊ ነው፡፡

የክልሉ መንግስት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ስቴዲዮም ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ስፖርቱ ለመደገፍ የሚያስፈልጉ  ሌሎችንም የስፖርት መሰረተ-ልማቶችን በየደረጃው  ለመገንባት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ከክልሉ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን  የሰመራ ስታዲዮምን የግንባታ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሐምሌ 8/2009 በአዲስ አበባ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት በተለያዩ መስኮች የሰለጠኑ ተመራቂዎች በሙያቸው ለጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ለኢንዱስትሪዎች ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምሀርት ሥልጠና ቢሮ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 8 ሺ 837 ሰልጣኞች  ዛሬ አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ ውስጥ  34 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ፣ ከደረጃ አንድ እስከ አምስት በቀን፣ በማታና በተከታታይ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ዘርኡ ስሙር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ ተመራቂዎቹ ያገኙትን ሥልጠና በሙያ ብቃት ምዘና በማረጋገጥ ሕብረተሰቡን የክህሎትና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ተመራቂዎቹ በሰለጠኑበት የሙያ መስክ በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀትና በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች በመቀጠር ለአገሪቷ የኢንዱስትሪ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ አቶ ዘርኡ ጠይቀዋል።

በቀጣይም በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ለመካከለኛና ዝቅተኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ሥልጠናዎች በስፋት እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የሥልጠና ተቋማቱ 471 ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፣ ተመራቂዎቹንም ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ዶክተር ታቦር ገብረመድኅን ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎቹ በሙያቸው ለሀገሪቷ ሕዳሴ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሰልጣኞች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 8/2009  ተመራቂዎቹ  በሰለጠኑበት የሙያ መስክ በመሰማራትና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ለአገራቸው እድገት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ስልጠና  ተመራቂዎች ተናገሩ።

በሮው በከተማ  አስተዳደሩ  በሚገኙ   ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ስልጠና  ተቋማት ከደረጃ አንድ እስከ አምስት በቀን፣ በማታና በተከታታይ ትምህርት በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 8 ሺ 837 ሰልጣኞች  ዛሬ አስመርቋል።

ለኢዜአ አስተያይታቸውን የሰጡ ተመራቂዎች እንደገለጹት፤ በሰለጠኑበት የሙያ መስክ በመሰማራትና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ለአገራቸው እድገት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ተዘጋጅተዋል።

ሰላማዊት ደጀኔ አቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሜካቶኒክ በተሰኘ የትምህርት ዘርፍ በደረጃ አራት ተመራቂ ስትሆን በአውቶማቲክ ድሪሊንግ ማሽን  ቴክኖሎጂን በመፍጠርም የሜዳሊያ ተሸላሚ ናት።

በቀጣይም ያላትን የክህሎት ትምህርት ከማጎልበት በተጨማሪ ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር ማለሟን ትገልጻለች።

በህንጻ ኮንስትራክሽን ሥራ አመራር ከአዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጂ የደረጃ አራት ተመራቂው ወጣት ያቤጽ ክፍሌ ለተመራቂ ተማሪዎች በቀረበ የምዘና ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በተመሳሳይ ለሜዳሊያ ሽልማት በቅቷል።

በትምህርት ቆይታው ወደፊት መስራት የሚገባው ነገር ላይ አቅሙን መገንባቱን በመግለጽ አገሪቷ ከእርሱ የምጠብቀውን ነገር በሙያው ለማበርከት መዘጋጀቱን ገልጿል።

ሌላኛው አስተያይ ሰጭ በጨርቆስ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ በህንጻ ኮንስትራክሽን ሥራ አመራር በደረጃ አራት ተመረቂው ወጣት አብርሃም አባተ ነው።

እንደ አብርሃም ገለጻ "በኮሌጁ ሲሰጡ የነበሩ የንድፈ ሃሳብም ሆነ የተግባር  ስልጠናዎች በቂ ግንዛቤ ማግኘት የሚያስችሉ ናቸው።"

ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀትም በህንጻ ማስጌጥና ማጠናቀቅ ስራዎችን ተኮናትሮ ለመስራት መዘጋጀታቱን አመልክቷል።

በንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ አሰልጣኙ አቶ ማስረሻ ፈቃደና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አሰልጣኙ አቶ ዚያድ ከማል በማሰልጠን ብቃታቸው የሜዳለያ ተሸላሚ ናቸው።

የኮሌጃቸው ሰልጣኝ ምሩቃኑ በውጤት ተኮር ክህሎት የቀሰሙና ኢንዱስትሪው በሚፈልገው ደረጃ የበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማቱ ለኢንዱስትሪው የሰለጠነ የሰው ኃይል ማቅረብ የሚያስችል ውጤት ተኮር ስልጠና ስርዓት እንዲዘረጉ ተደርጓል።

 

በዚህም ኢንዱስትሪዎች የስልጠና ማዕከላት እንዲሆኑ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠናዎች 70 በመቶውን በኢንዱስትሪዎች 30 በመቶው ደግሞ በማሰልጠኛ ተቋማቱ እንዲሆን መደረጉን የቢሮው መረጃ ይጠቁማል።

 

ሰልጣኞቹ ብቁ ሆነው እንዲመረቁ በተዘረጋው አገር አቀፍ ምዘና ተመዝነው ብቁ የሆኑ ሰልጣኞች ቁጥር ከሶስት ዓመት በፊት ከነበረው 63 በመቶ ወደ 76 በመቶ ከፍ ብሏል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2009 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ2018 የቻን ማጣሪያ ውድድር  ጀቡቲን 5 ለ 1 አሸነፈ፡፡

ዋልያዎቹ እና የጂቡቲ አቻቸው የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በጅቡቲ አል ሃጂ ስታዲየም ነው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በትዊተር ገጻቸው ለተከታዮቻቸው ኢትዮጵያ በጌታነህ ከበደ አራት ጎሎችና በሙሉዓለም መስፍን አንድ ጎል ጅቡቲን 5 ለ 1 ማሸነፏን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2018 የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ማጣሪያ በመጀመሪያ ጨዋታው ከሜዳው ውጭ ድል ቀንቶታል፡፡

ዋልያዎቹ በቀጣይ ሳምንት በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከጂቡቲ ጋር የመልስ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ የማጣሪያ ጨዋታ ለማለፍ ጨዋታውን በአቻ ማጠናቀቅ በቂዋ ይሆናል።

Published in ስፖርት

ሐምሌ 8/2009 በሳውዲ አረቢያ ህጋዊ የስራና መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚኖሩ ኢትዮጵያን የተቀመጠው ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ፡፡

በሳውዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን አስመልክቶ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡

በተለያየ ምክንያት ወደሀገራቸው መመለስ ያልቻሉ ዜጎች ለእስርና የገንዘብ ቅጣት ከመዳረጋቸው በፊት የቀረበላቸውን ወርቃማ እድል እንዲጠቀሙበት  የህዝባዊ ውይይቱ መሪዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን መክረውና ገስጸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ እንዲተባበሩም ነው የመድረኩ መሪዎች የጠየቁት፡፡

ህጋዊ የስራና መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ወገኖች ‹‹አይዟችሁ፤ እኛ እናስጥላችኋለን፤ አዋጁም ሊራዘም ይችላል… ›› በሚል አጉል ተስፋ ተታለው  ለችግር እንዳይጋለጡም ጥብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በህዝባዊ ውይይት መድረኩ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን መንግሥት ዜጎች ያለምንም እንግልት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረገውን ጥረት አድንቀው በቀሪዎቹ ቀናት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ዜጎች ለችግር ከመጋለጣቸው በፊት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

ህዝባዊ መድረኩን በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አሚን አብልቃድርን ጨምሮ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ፣ አምባሳደር ማህሙድ ድሪር እንዲሁም ዘመቻውን ለማገዝ ከኢትዮጵያ የተላከው ቡድን አስተባባሪ አምባሳደር ጊፍቲ አባስያ መርተውታል፡፡

የሳውዲ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠው ተጨማሪ ቀነ ገደብ  ሊጠናቀቅ ዘጠኝ ቀናት ብቻ ይቀሩታል፡፡

 

ምንጭ፡- በሳውዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ

Published in ማህበራዊ

ደብረ ማርቆስ ሀምሌ 8/2009 በምስራቅ ጎጃም ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ህጻናት ተገቢ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ መደረጉን የዞኑ ሴቶችና ሕጻናት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ አዲሴ ጫኔ ለኢዜአ እንደተናገሩት መንግስት ወላጆቻቸውን በሞት ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ሕጻናት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም በአስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ ላይ ለነበሩ ከ10 ሺህ በላይ ህጻናት ዘላቂ የሆነ የመቋቋሚያ ድጋፍና የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት መቻሉን ገልጸዋል።

ድጋፉን ማድረግ የተቻለው በዞኑ በተቋቋመው የማህበረሰብ ድጋፍ ጥምረት በኩል ከባለድርሻ አካላትና ከ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ከማህበረሰቡ በመሰብሰቡ ነው።

ድጋፉን ካገኙት ህጻናት መካከል ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮ አዲሴ፣ እርዳታው ህጻናት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲማሩ ከማድረግ ባለፈ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲወጡ የራሱን እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል።

በእዚህም ከአምስት ሺህ በላይ ሕጻናት በአሳዳጊዎቻቸው አማካኝነት እንስሳትን የሚያደልቡበትና የሚያረቡበት፣ በጓሮ አትክልት ልማት የሚሰማሩበትና ቋሚ ሃብት የሚያፈሩበት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ለቀሪዎቹ ሕጻናትም በየወሩ ከሦስት እስከ አራት መቶ ብር በመስጠትና የትምህርት ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ በማድረግ ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ መደረጉን ገልጸዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ ከ50 በላይ ወንድ ሕጻናት የሊስትሮ እቃዎችን ከመስሪያ ቦታ ጋር በማዘጋጀት ማስረከብ መቻሉን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ሀምሌ 8/2009 የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሰው ኃይል ልማትና የምርምር ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ለሀገሪቱ የልማትና የሕዳሴ ጉዞ ስኬታማነት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

ዩኒቨርሲቲው በመደበኛና በማታው የትምህርት መረሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 473 ተማሪዎች ዛሬ በመጀመሪያ ድግሪ ለሦስተኛ ጊዜ አስመርቋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢሰቢ አቶ ሰናይ አኩዎር በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን የሰው ሀብት ልማትና የምርምር ሥራዎች በማጠናከር በአገሪቱ ለተጀመሩ የልማትና የህዳሴ ጉዞ እውን መሆን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

ዩኒቨርሲቲው በልማት ሥራዎች የሚሳተፍ ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፈራት ጎን ለጎን ወደ ሕብረተሰቡ ዘልቆ በመግባት ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን በሚያደረገው ጥረት የክልሉ መንግስት የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ክልሉ ሰፊ መሬትን ጨምሮ የእንስሳት፣ የደንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉት ቢሆንም ሀብቱ በተፈለገው ደረጃ ባለመልማቱ ህዝቡ በተፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን አቶ ሰናይ ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ ብሎም በአገሪቱ ለተጀመረው የልማትና የፀረ- ድህነት ትግል ስኬታማነት ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸውን የሰብአዊ ሀብት ልማትና የምርምር ሥራዎች አጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የዕለቱ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲው ቆይታቸው በተግባርና በንድፈ ሀሳብ የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም በአገሪቱ የተጀመረውን የልማትና የሕዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የዩኒቨርሰቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኦፒዮው ኡሞት በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ከእዚህ ጎን ለጎን የምርምር ሥራዎችን በማከናወን በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ የድርሻውን ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸውን የሰው ኃብት ልማትና የምርምር ሥራዎች በተሟላ መልኩ ለማከናወን የሚያስችሉትን የማስፋፈያ ግንባታ ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ እያከናወነ ይገኛልም ብለዋለ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቤል ቢቾክ በኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ያስመረቃቸው 473 ላለፉት ሦስት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ፋካሊቲዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ናቸው።

ተማሪዎቹ ከሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች መካከል እንስሳት ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ ዕጽዋት ሳይንስ፣ የሰው ሀብት አስተዳድር እንደሚገኙባቸው ጠቁመዋል።

ከዕለቱ አጠቃላይ ተመራቂዎች መካከልም 227ቱ ሴቶች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሦስት ዓመታት አደረጃጀቱን ሲያጠናክር መቆየቱን የገለጹት ዶክተር ቤል፣ በመጪው የትምህርት ዘመን ተጨማሪ የትምህርት ክፍሎችን በመክፍት በቅድመና ድህር ምርቃ መረሃ ግብር ተማሪዎችን ተቀበሎ ለማሰልጠን መዘጋጀቱን ጠቁመዋል ።

ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል ብስራት ኃይሌና ሙሉቀን አለሙ በየበኩላቸው በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት በሰለጠነበት የሙያ መስክ ራሳቸውንና አገራቸውን ለመለወጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።  

Published in ማህበራዊ
Saturday, 15 July 2017 22:25

የእናት ጥሪ

                                                                      መኳንንት ካሳ /አሶሳ ኢዜአ/

 

‹‹ሌቱንም ቀኑንም በሃሳብ ነው የማሳልፈው፡፡ አካሌ እዚህ ቢሆንም ሩሄ ግን እዚያው ልጆቹ ካሉበት ነው፡፡ የሚበላውም የሚጠጣውም ከሰውነቴ ሊጠጋኝ አልቻለም፡፡ በሚነገረው ችግር የተነሳ በሃሳብ አለቅን፡፡››

የተቀመጥንበት የሳር ፍራሽ ላይ ያሉ ቋጠሮዎችን በእጃቸው እያፍተለተሉ፤ አንገታቸውን ያቀረቀሩት  ወይዘሮ ኩሌ ሁሴን የሚተናነቃቸው ሲቃ ድምፃቸውን እየቆራረጠው ንንግራቸውን ቀጠሉ፡፡

‹‹ ልጆቼ በጤና ብቻ አገራችሁ ግቡልኝ፡፡ ምን ይዘን እንምጣ ብላችሁ አታስቡ፡፡ ሃሳባችን በደህና መጥታችሁ አገራችሁ እንድትኖሩ ነው፡፡ ብንሞት እንኳን ከጎናችን ሳትሆኑ መቅረታችሁ ነው፡፡ ስለእናንተ ማሰቡና ጭንቀቱ ጎድቶናል፡፡›› 

የሚተናነቃቸው ሲቃ ገንፍሎ ወጥቶ ፊታቸውን አጠበው፡፡ ሁለት ሴት ልጆቻቸው ሳውዲ አረቢያ የሚገኙት ወይዘሮ ኩሌ ሁሴን ልጆቻቸው ሲደውሉ ምን እንደሚሏቸው ጠይቄያቸው የነገሩኝ ነው፡፡

ልጆቻቸው ሳውዲ አረቢያ ከሄዱ አንደኛዋ አምስት ሌላኛዋ ደግሞ አራት አመት ሞልቷቸዋል፡፡ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ካለ ህጋዊ ፍቃድ በሃገሪቷ የሚኖሩ የሌላ ሃገር ዜጎች እንዲወጡ መመሪያ ካስተላለፈበት ጊዜ አንስቶ እኝህ እናት ልጆቻቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መጎትጎታቸውን አላቆሙም፡፡ 

የተወሰነ ሰርተው ለመምጣት በመፈለግ እንጂ አገራቸው መመለሱን ሁሌም እንደሚናፍቁ ልጆቻቸው እንደሚነግሯቸው ወይዘሮ ኩሌ ተናግረዋል፡፡ በሰው ሃገር በሰቀቀን ከመኖር ምንም ይሁን ምን በሃገር መኖርን የሚያህል እንደሌለ እኝህ እናት ገልፀዋል፡፡

ባምባሲ ወረዳ አምባ 49 ቀበሌ የሚኖሩት የወይዘሮ ኩሌ ሁሴን የእናትነት ጥሪ የበርካታ እናቶችም ጥሪ እንደሚሆን እርግጥ ነው፡፡ የወለደ አንጀት አይችልም አይደል የሚባለው፡፡ 

ከወይዘሮ ኩሌ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ አንዲት ወጣት ከቅርብ ቀናት በፊት ከሳውዲ አረቢያ መመለሷን ስለሰማን በቀበሌው ስራ አስኪያጅ ወጣት አንሻ እንድሪስ መሪነት ወደ መኖሪያ ቤቷ አቀናን፡፡

ከተባለው ቤት ደጃፍ ደረሰን ። አንሻ ደጋግማ ብትጣራም ምላሽ በማጣታችን ወደ ግቢው ዘልቀን ገባን፡፡ በግቢው ከሚገኝ የጎጆ ቤት ሞቅ ያለ ጨዋታ የያዙ ሰዎች ድምጽ ይሰማል፡፡ የመጣችውን ወጣት ‹እንኳን ለሃገርሽ አበቃሽ› ለማለት የተሰበሰበ ዘመድና ጎረቤት ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፡፡

ጎጆ ቤቱን ቀረብ ብለን አንሻ አንድ ሁለቴ እንደተጣራች አንዲት እናት ብቅ ብለው ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ከሳውዲ አረቢያ የመጣችው ወጣት እናት ናቸው፡፡ ደስታቸው ከፊታቸው ላይ የሚነበበው እኝህ እናት ልጃቸው ከሳውዲ አረቢያ ከመመለሷ በፊት በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

ልጃቸው ወጣት ዘውዴ ጥላሁን ትባላለች፡፡ ሳውዲ አረቢያ የሄደችው በ2005 ዓ.ም ሲሆን በመሃሉ ወደ ሃገሯ መጥታ ዳግመኛ ተመልሳ በመሄድ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ እዛው ቆይታለች፡፡ በህጋዊ መንገድ ከሃገሯ ብትወጣም ከአሰሪዋ ጋር ባለመግባባቷ ከአሰሪዋ ቤት በመጥፋት ካለመኖሪያ ፍቃድ ስትሰራ ቆይታለች፡፡

ካለ መኖሪያ ፍቃድ መኖር ሁሌም ሰቀቀን የሚፈጥር መሆኑን የገለፀችው ወጣቷ ፖሊሶች ቤት ለቤት የሚያደርጉት አሰሳ ተረጋግቶ መኖር የማያስችል እንደሆነ ተናግራለች፡፡

ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኗ የቤተሰቧን ኑሮ የማሻሻል ኃላፊነቱ የእሷ መሆኑን በማመን ወደ አረብ አገር የወጣቸው ዘውዴ ከአራት ዓመት በላይ የአረብ አገር ቆይታ በኋላ የነበራት ውጥን አለመሳካቱን ተናግራለች፡፡ ዳግም በውጭ ሃገር የምትጥለው ተስፋ እንደሌላት በመግለጽ ከአሁን በኋላ በሃገሯ ሰርታ ለመለወጥ እንዳሰበች አጫውታኛለች፡፡ 

ከእነዘውዴ ቤት ስንወጣ ከቀበሌው ስራ አስኪያጅ ወጣት አንሻ እንድሪስ ጋር ስለዚሁ ስለ አረብ ሀገር ጉዞ ጉዳይ እየተጨዋወትን ስናዘግም እሷም በአባቷ ጥረት ከአረብ አገር ጉዞ መትረፏን ነገረችኝ፡፡ በወቅቱ የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በአካባቢዋ ወደ አረብ ሃገር የተጓዙ ወጣቶችን በመመልከት የመሄድ ፍላጎት አድሮባት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ነገር ግን አባቷ አጥብቀው ጉዳዩን በመቃወማቸው በወቅቱ ፍላጎቷ ሳይሳካ እንደቀረና ዛሬ ላይ ስታስበው አባቷን እንደምታመሰግን ነገረችኝ፡፡ አንሻ እንድሪስ ትምህርቷን በመቀጠል ከኮሌጅ በዲፕሎማ ተመርቃ ተወልዳ ያደገችበትን አካባቢ እያገለገለች ትገኛለች፡፡

በባምባሲ ወረዳ አምባ 49 ቀበሌ ህገወጥ የሠዎች ዝውውር እንደሚፈፀምባቸው ከተለዩ አካባቢዎች መካከል አንዱ መሆኑን የክልሉ ማህበራዊና ሰራተኛ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ባበክር ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚበዛባቸው አካባቢዎችን በመለየት የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ቁጥጥር ምክር ቤቶችና የቴክኒክ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን ኃላፊው አቶ አህመድ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከአረብ ሃገራ የተመለሱ ዜጎችን ለማቋቋም በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሳውዲ አረቢያ የተመለሱ የክልሉ ነዋሪዎችን ለማቋቋም ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ክልሉ የራሱን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

Published in ዜና ሓተታ

አዲስ አበባ ሐምሌ 8/2009 የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በመጪው ጥር  ግንባታው ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን ጨምሮ የመካኒሳ ቆጣሪ ያልተማከለ ፍሳሽ ማጣሪያ እና የአቃቂ ጥልቅ  የውሃ ጉድጓድን ለፖለቲካ ፓርቲዎች አስጎብኝቷል።

በባለስልጣኑ የውሃና ፍሳሽ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የፕሮጀክቶች ማስፋፊያና ልማት የምህንድስና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ብርሃነ ሀጎስ   የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በመጪው ጥር   ስራ ይጀምራል ብለዋል።

የፕሮጀክቱ የግንባታ 90 በመቶ እንደደረሰና የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮችም ጎን ለጎን እየተገነቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ከስድስት ክፍለ ከተሞች የሚመጣውን ፍሳሽ ቆሻሻ የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን በቀን 100 ሺህ ኪዩብ ሜትር ፍሳሽ ያጣራል።ይህም በአፍሪካ ከትላልቆች የፍሳሽ ማጣሪያዎች መካከል አንዱ ያደርገዋል ብለዋል አቶ ብርሃነ።

የተጣራው ውሃም ወንዞችን ከብክለት ከማዳን በተጨማሪ ለግንባታ ስራዎች፣ለአረንጓዴ ልማትና ለመስኖ ስራዎች ይውላል።

የውሃና ፍሳሽ ስራዎች የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ስራ በመሆኑ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያከናወኑ እንደሆነም ነው የገለፁት።

በመሆኑም የውሃና ፍሳሽ ስራዎች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ፣በምን ሁኔታዎችስ  ውስጥ አልፈው ነው ለአገልግሎት የሚውሉት የሚለውን ሁሉም የማህበረሰቡ ክፍል እንዲገነዘብ እያስጎበኘን ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹን የጎበኙት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው መንግስት ፍሳሽ ቆሻሻን በማጣራት በኩል የሚያከናውነው ተግባር  የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

በመንግስት መስሪያ ቤት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እንዲጎበኙ ጥሪ ሲቀርብላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንም ተናግረዋል።

የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ ቆሻሻን አጣርቶ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው በክልል በሚገኙ ትላልቅ ከተሞችም ሊከናወን ይገባዋል ብለዋል።

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ትግስቱ አወሉ በበኩላቸው ቆሻሻን አጣርቶ እንደገና ለመጠቀም ፕሮጀክቱ ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል። ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኋላም አጠቃቀሙ ላይ ግንዛቤ ግንዛቤ እንዲፈጠር አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ(ኢዴአን) ሊቀ መንበር አቶ ግኡሽ ገብረ ስላሴ ወደ ወንዝ እየገባ ይበክል የነበረውን ውሃ አጣርቶ መጠቀሙ የልማት እንቅስቃሴው አንድ አካል መሆኑን ገልፀው የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ በፍጥነት መጠናቀቅ አለበት ብለዋል።

ባለስልጣኑ በስምንት የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶች አስራ ሁለት ያልተማከሉ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያዎችን ግንባታ አጠናቆ ስራ ላይ አውሏል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሐምሌ 8/2009 ሃምሊን የአዋላጅ ነርሶች ኮሌጅ ኮሌጅ ለሰባተኛ ጊዜ በዲግሪ መርኃ ግብር ያሰለጠናቸውን 21 ባለሙያዎች አስመረቀ።

ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በአውስትራሊያዊቷ ዶክተር ሃምሊንና ዶክተር ሬይናልድ ሃምሊን በ1966 ዓ.ም የተቋቋመና በዓለም አቀፍ ደረጃ በወሊድና ፊስቱላ ዙሪያ የሚሰራ ተቋም ነው።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ባሉት አምስት ማዕከላቱ ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ባሻገር ፊስቱላን ለመከላከል ኮሌጅ ከፍቶ ሐኪሞችን እያፈራ ነው።

በ1999 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ በኋላ በዚህ ዓመት የተመረቁትን ጨምሮ 125 አዋላጅ ነርሶችን አስመርቋል።

ኮሌጁ ተማሪዎቹን በአዋላጅ ነርስነት ለአራት አመታት አስተምሮ  ካስመረቀ በኋላ ሁሉም ተመራቂዎች ክፍተት ባለባቸው በገጠራማ አካባቢዎች በሚገኙ ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ ያደርጋል።

የኮሌጁ ዲንና የሃምሊን ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም በለጠ በዚህ ጊዜ እንዳሉት  ኮሌጁ በትምህርት ሚንስቴር የቅበላ መስፈርት መሰረት በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሴት ተማሪዎችን  መልምሎ በአዋላጅ ነርስነት በዲግሪ እያሰለጠነ ያስመርቃል።

ድርጅቱ የወሊድና ፊስቱላ ተጎጂ ሴቶች ነጻና ሁሉን አቀፍ የህክምና አገልግሎት በመስጠት የእናቶችና የሴቶችን ጤና በመጠበቅ ረገድ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድም ጠቁመዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል 3.7 በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ  የሆነችው ተመራቂ ሃብታም ሙሉጌታ "እናቶች በጤና ተቋም ብቻ እንዲወልዱና በወሊድ ጊዜም የሚከሰተውን የፊስቱላ በሽታ አስቀድሞ በመከላከል የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የበኩሌን እወጣለው" ብላለች።

"በትምህርት ቆይታዬ ለ103 እናቶች የወሊድ አገልገሎት በመስጠት ተሸላሚ ሆኛለሁ፣ የአቅሜን ያክል ለእናቶች ድጋፍ በመስጠቴ የህሊና እርካታን አግኝቻለው" ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ተመራቂ  ነኢማ ከበደ ናት።

በቀጣይም በገቡት አገራዊና ሙያዊ ቃል መሰረት  ለእናቶች የጤና አገልግሎት እንደሚሰጡ ተመራቂዎቹ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ከ50 ዓመታት በላይ ባስቆጠረ አገልግሎቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በባህር ዳር፣መቀሌ፣ይርጋለም፣መቱና ሀረር ከተሞች ባቋቋማቸው አምስት ሆስፒታሎች ከ45 ሺህ በላይ በበሽታው ለተጋለጡ ሴቶች ነጻ የህክምና አገልግሎት  ሰጥቷል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ