አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 14 July 2017

አዲስ አበባ ሃምሌ 7/2009 ለሳዑዲ ተመላሾች የሚደረገው ድጋፍ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል መሆን እንደሚገባው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሳዑዲ ተመላሾችን ለማቋቋም ያዋቀረውን ኮሚቴ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለኮሚቴው አባላት በሰጡት የሥራ መመሪያ እንደተናገሩት፤ የንግዱ ማህበረሰብ ተመላሾቹ በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ በስልጠናና ምክር መንገድ ማሳየት አለበት፡፡

የመንግስት የድህነት ቅነሳ ፖሊሲ ለብዙ ተመላሾች የሥራ እድል እንደሚፈጥር የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በተለይ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ለብዙ ሴቶች የሚፈጥረውን እድል ተመላሾቹ እንዲጠቀሙበት ምክር ቤቱ በስልጠናና ተያያዥ ሁኔታዎች ላይ ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፤ ገንዘብ ይዘው የሚመጡ ተመላሾች መሰማራት የሚችሉበትን ዘርፍ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲጠቁማቸውና ምክር እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሠለሞን አፈወርቅ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የንግዱ ማህበረሰብ ወገንተኝነቱን ለማሳየትና በዋናነት ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል መደገፍ ነው፡፡

የባለሀብቱ ገንዘብ ለወገን መድረስ ካልቻለ ትርጉም እንደሌው የተናገሩት አቶ ሠለሞን፤ ተመላሾቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ስልጠና ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ተመላሾቹ ተቸግረው ተደስቶ መኖር የሚከብድ በመሆኑ ወገንተኝነትን ማሳየቱና ማገዙ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኮሚቴው አባል አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ናቸው፡፡

ኮሚቴው የሳዑዲ ተመላሾችን በቅርቡ በሚያዘጋጀው የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ከመደገፍ ባሻገር በስልጠና ለማገዝ የገንዘብ አቅም ያላቸው ቢሰማሩበት ደግሞ አዋጪ የሆኑ ሥራዎችን ለመጠቆም ቃል ገብቷል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

ጅማ ሃምሌ 7/2009 በኢትዮጵያ የሚሰጠው የድህረ ምረቃ ስርዓተ ትምህርት ከሀገሪቱ የዕድገት ደረጃና ከሌላው አለም የላቀ ቴክኖሎጂ ጋር ባገናዘበ መልኩ ለመከለስ የሚያግዝ  አውደ ጥናት በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

በአውደ ጥናቱን ያዘጋጀው የጅማ ዩኒቨርሲቲ  ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታዬ ቶለማሪያም እንዳሉት የሀገሪቱና የአለምን ቴክኖሎጂ ዕድገት  ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ስርዓተ ትምህርት መኖር አስፈላጊ ነው ፡፡

በስራ ላይ ያለውን የድህረ ምረቃ ስርዓተ ትምህርት በመገምገም ከሀገራዊ እድገታችንና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ተዋህዶ በሚኬድበት መልኩ ለመከለስ አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ለሀገሪቱን  ሁለተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክተውን የድህረ ምረቃ ትምህርት ደረጃውን በጠበቀ ስርዓተ ትምህርት እንዲመራ ለማድረግ በተጀመረው ዓውደ ጥናት ላይ  ምሁራን የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ስራቸውን ያቀረቡት ዶክተር ስሜነህ የሀገቱን ዕድገት ለማስቀጠል የሚያስፈልግ  የሰው ኃይል በጥራትና በብዛት ማፍራት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ደግሞ አስፈላጊውን ስርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ለአስፈጻሚው አካል በግብአትነት ማቅረብ የምሁራን ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሁን በሀገሪቱ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ እየተሰጠ ያለው ትምህርት ላይ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የገለጹት ደግሞ  የጅማ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ፕሮፌሰር ተፈራ በላቸው ናቸው፡፡

" ስርዓተ ትምህርቱ ሀገሪቱ  ከምታደርገው የኢንዱስትሪ ሽግግር ጋር አብሮ መሄድ የሚችል መሆን አለበት "ብለዋል ።

ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ጀማል አህመድ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች  ርዕሳቸው  ከይዘታቸው ጋር እንደማይመሳሰሉ  በጥናት እንዳረጋገጡ ተናግረዋል ።

በቀጣይ ስርዓተ ትምህርቱ ተከልሶ በድህረ ምረቃ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ርዕሳቸው ከይዘታቸው ፣  ከተሰጣቸው ጊዜ ፣ከተቀመጠላቸው አላማና ግብ ጋር የሚጣጣሙ መሆን እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል ።

በጅማ ዩኒቨርስቲ እየተካሄዳ ባለው የድህረ ምረቃ ስርዓተ ትምህርት ግምገማ ከሀገሪቱና ከውጭ  የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ናቸው፤  ከ40 በላይ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተመልክቷል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

ሀረር ሃምሌ 7/2009 በሐረር ከተማ የሚገኘው የጁገል ሆስፒታል ከበጎ ፈቃደኛ ህክምና ባለሞያዎች ጋር በመተባበር የዓይን ሞራ ግርዶሽ ላለባቸው ሰዎች ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ያሲር ዮኒስ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ የነጻ ህክምና አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው የሐረር ቀን መከበር ከጀመረበት ከግንቦት 28 ቀን 2009 ጀምሮ ነው።

ለበዓሉ ዝግጅት ከአውስትራሊያ የመጡት ዶክተር ጀማል ኡስማኢልና ሌሎች በውጭ አገር የሚገኙ  በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች የሙያና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

''የክልሉ መንግስትም ተጨማሪ ከፍተኛና ረዳት የህክምና ባለሙያዎች በመመደብ ህሙማን አስፈላጊው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው'' ብለዋል።

እስካሁን በተከናወነው የነጻ ህክምና አገልግሎት 90 የክልሉና የአጎራባች ክልል ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

እስከ ሃምሌ 14 ቀን 2009 በሚከናወነው የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎት 250 ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

አገልግሎቱ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ ሁለት ጊዜ በነጻ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት የሸንኮር ወረዳ ነዋሪ አቶ ግዛቸው ተካ ''በአቅም ማነስ ምክንያት ለ11 ዓመታት መታከም ያልቻልኩት አሁን በነጻ ህክምና በማግኘቴና በድሉ በመጠቀሜ ደስ ብሎኛል'' ብለዋል፡፡

''በተደረገልኝ የዓይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ህክምና ለሰባት ዓመት ከቆየው ህመሜ ለውጥ አይቻለሁ ለዚህ ላበቁኝ የህክምና ባለሙያዎችና የክልሉ መንግስት ምስጋና  አቀርባለሁ'' ያሉት  የአሚር ኑር  ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አኒሳ ሰዲቅ ናቸው።

የጁገል ሆስፒታል ባለፈው ሚያዚያ ወር ከበጎ ፈቃደኛ ህክምና ባለሞያዎች ጋር በመተባበር ከ400 ለሚበልጡ ሰዎች ነፃ የአጥንት በሽታ ህክምና መስጠቱ ይታወሳል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 7/2009 የ'አሜሪካ መጤ ተምች' በሰብል ምርታማነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በባህላዊ መንገድ የተከናወኑ የመከላከል ተግባራት ውጤታማ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠላቸውን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ።

እስካሁን ከተሸፈነው ሁለት ሚሊዮን ሄክታር የበቆሎ ሰብል ማሳ መካከል 455 ሺ ሄክታር ወይም 22 በመቶው በተምች ተጠቅቷል።

ባለፈው መስከረም ለመጀመሪያ ጊዜ በናይጄሪያ የተከሰተው ‘አሜሪካ መጤ ተምች’ በ25 የአፍሪካ አገሮች ተሰራጭቷል።

ይህም በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ለምግብነት በሚውለው የበቆሎ ሰብል በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ላይ ጉዳት ማድረሱን የቅርብ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተባዩ መከላከል ላይ ለመምከርም ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ የግል ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት፣ በተባዩ የተጠቁ አገሮችና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የተሳተፉበት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በተምች ከተጠቁ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያም 455 ሺ ሄክታር የበቆሎ ሰብል ማሳ በመጤ ተምቹ መያዙ ተገልጿል።

በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሳላቶ፤ ‘አሜሪካ መጤ ተመች’ በስድስት ክልሎች አጠቃላይ በበቆሎ ሰብል ከተሸፈነው ሁለት ሚሊዮን  ሄክታር ውስጥ 22 በመቶው ላይ መሰራጨቱን ተናግረዋል።

ተምቹ የ’እሳት እራት’ ከተሰኘው ደረጃ ሲደርስ ወደ ሌላ አካባቢ በነፋስ ስለሚዛመት ተፈጥሯዊ ሥርጭቱን መቀነስ እንጂ መከላከል እንደማይቻልም ገልጸዋል።

"ዋና ዓላማው መዛመቱን መከላከል ሳይሆን ሰብል ምርት ላይ ዓይነተኛ ጉዳት እንዳይደርስ በተለይ የምግብ ዋስትናን የሚፈታተን ችግር እንዳይመጣ እየተረባረብን ነው" ብለዋል።

የተምቹ ስርጭት በአዳዲስ የበቆሎ ሰብሎች እየተዛመተ ቢሆንም፤ እስካሁን የተከናወኑ በተለይም ከጸረ - ተባይ መከላከል በበለጠ ባህላዊ የመከላከል ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ውጤት ያስገኙ የመከላከል ልምዶችን በመውሰድም በሁሉም አዳዲስ አካባቢዎች የመከላከል ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችንና የዕጽዋት ጥበቃ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት በመሰጠቱም ተምቹ የመጉዳት ደረጃ ሳያድግ የመከላከል ሰራው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የአሜሪካ መጤ ተምች እስካሁን በበቆሎ ሰብል ላይ ቢዛመትም በተወሰኑ አካባቢዎች በማሽላ ሰብሎች፣ በግጦሽና በጫካ እጽዋት ላይ በመታየቱ ጉዳቱን ለመከላከል አሰሳ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

እስካሁን በተባዩ ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ የወደመ ወይም የተገለበጠ የበቆሎ ሰብል ማሳ አለመኖሩን ገልጸው፤ " በሰብል ምርታማነት ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ የሚያጠና የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁማል" ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የነፍሳት ስነ ሕይወትና ስነ ምሕዳር ማዕከል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ተፈራ በበኩላቸው፤ "ከህንድ አገር የእሳት ራት ማጥመጃ ኬሚካሎችን በማምጣት በአምስት ክልሎች አሰራጭተን ውጤት እያገኘን ነው" ብለዋል።

ማዕከሉ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል እስካሁን ባለመኖሩም በተባዩ ላይ ምርምር የሚያካሂዱ ባለሙያዎች እየሰለጠኑ መሆኑን አብራርተዋል።

የዓለም አቀፉ የተቀናጀ ነፍሳት ሥራ አመራር የኢኖቬሽን ቤተ ሙከራ ዳይሬክተር ዶክተር ሙኒ ሙኒያፓን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያይት፤"ከ80 በላይ ሰብሎችን የሚያጠቃው ተባይ በቆሎን በስፋት ለምግብነት በሚጠቀሙ የሰሃራ በታች አገሮች መከሰቱ አሳሳቢ ነው" ብለዋል።

የተምቹን መዛመት ለመከላከልም አዋጭነት ያለው "የተቀናጀ የመከላከል ሰራ ያስፈልጋል" ነው ያሉት።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው አውደ ጥናቱም በወረርሽኙ የተጠቁ አገሮችን ጨምሮ በርካታ የምርምር ተቋማትና ለጋሽ ድርጅቶች በመኖራቸው ለግንዛቤ ፈጠራና ለልምድ ልውውጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በቅርብ ወራት በደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን የተከሰተው 'አሜሪካ መጤ ተምች' በአሁኑ ወቅት ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በመዛመት በቆሎ አምራች አካባቢዎች ላይ ጥቃት እያደረሰ ይገኛል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሃምሌ 7/2009 የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በዘርፉ ተወዳዳሪና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተናቦ መሥራት እንዳለበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አሳሰበ። 

ምክር ቤቱ በተጨማሪም በዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት፣ የአካባቢያዊ የንግድ ግንኙነትና ድርድር ጉዳዮች መመሪያ፣ በሲልካ ሳንድ ማዕድን ማምረት ፈቃድ ስምምነት ረቂቅ ደንብ ላይ ውሳኔ ማሳለፉን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። 

ምክር ቤቱ 35ኛውን መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት አካሂዷል።

የኤርፖርቶች ድርጅት በፋይናንስ አቅም፣ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በአደረጃጀት፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በውስጥ አሰራር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ልምድ በመውሰድ የአገልግሎት አሰጣጡን ማሳለጥ እንዳለበት ምክር ቤቱ አሳስቧል።

በተጨማሪም በመንገደኛ መስተንግዶ፣ በአፈጻጸም ሥራ አመራር እና ኮንትራት ማኔጅመንት ዘርፎች ከአየር መንገዱ ልምዶችን መውሰድ እንደሚገባም ምክር ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል።

ምክር ቤቱ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት እና የአካባቢያዊ የንግድ ግንኙነትና ድርድር ጉዳዮች መመሪያ ላይም መክሯል። 

በዚህም ሀገሪቷን ከዓለም አቀፍ ንግድ ተጠቃሚ ለማድረግና የዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት አባል ሂደትን በማስተባበር የአካባቢያው የንግድ ግንኙነቶችና ድርድሮች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የሚያስችል መሆኑም ተመልክቷል። 

በዚህም ግንኙነትና ድርድር በእውቀትና በክህሎት እንዲመራ መመሪያ ቀርቦና ማሻሻያዎች ታክሎበት ሥራ ላይ እንዲውል ምክር ቤቱ ወስኗል።

ኒውኤራ ማይኒንግ ፒ.ኤል.ሲ ለተባለ የሀገር ውስጥ ኩባንያ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ልዩ ስሙ ኬላ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የሲልካ ማዕድን የማምረት ፈቃድ ስምምነት ሥራ ላይ እንዲውል ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ባደረገቻቸው አስር የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይም መክሯል።

በዚህም በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በስታንዳርድ የባቡር ኔትወርክ ዝርጋታ አሰራርና አስተዳደር፣ በሞያሌ ድንበር ጣቢያ የጋራ ቁጥጥር ሥነ-ሥርዓት አገልግሎቶችና አስተዳደር ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

በተጨማሪም በአየርና በመንገደኞች ትራንስፖርት፣ በቱሪዝም ዘርፍ እና የጠቅላላ ትብብር ስምምነቶች ላይ ሀገሪቷ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትስስሩን ለማጠናከር እንደሚያስችል ታምኖበት ስምምነቶቹ እንዲፀድቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሀምሌ 7/2009 የቱርክ ባለሀብቶች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በአዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንደሚሰማሩ ተገለጸ።

በአሁኑ ወቅት ቱርክ በኢትዮጵያ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ኢንቨስትመንት እያከናወነች ትገኛለች።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩት ድርጅቶች 165  እንደሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ። አብዛኛዎቹ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ሚስተር ፋቲህ ዩሉሶይ ዛሬ በኤምባሲያቸው በተካሄደ መርሃ ግብር ላይ እንደተናገሩት፤ የቱርክ ባለሀብቶች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በአዳዲስ ኢንቨስትመንት መስኮች ማለትም በግንባታ ግብአቶች፣ በቤትና ቢሮ ቁሳቁሶች፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በታዳሽ ሀይል፣ በግብርና፣ በማዕድን ቁፋሮና በትምህርት ዘርፎች ይሰማራሉ።  

"ቱርክ በአፍሪካ ከምታከናውነው ኢንቨስትመንት ከፍተኛው መጠን የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው። ይህም የሆነው በአጋጣሚ ሳይሆን በአገሪቷ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመኖሩ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት ከኦቶማን ተርክሽ አገዛዝ ጀምሮ ቢሆንም፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት ግን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1926 ቱርክ ስድስተኛ አገር በመሆን በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን በከፈተችበት ወቅት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ሃምሌ 7/2009 በአማራ ክልል የ2009 ዓ.ም ክልል አቀፍ የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ በይፋ ተጀመረ።

የአማራ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ስቡህ ገበያው እንዳሉት ባለፉት አስር ዓመታት በተካሄደ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶችን በመሙላት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በዘንድሮው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎትም በክልሉ ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።

''የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል ያደረገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው'' ያሉት አቶ ስቡህ በተለይ ወጣቶች በአከባቢያቸው የልማት ስራዎች ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

''ወጣቶቹ በየዓመቱ በሚያካሂዱት የችግኝ ተከላ አገሪቱ የተያያዘችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና አለው'' ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎች በራሳቸው መልካም ፈቃድና ተነሳሽነት የልፋታቸውን ዋጋ ሳይጠይቁ በየአከባቢያቸው የሚታዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችል ነው።

በደቡብ ወሎ ዞን በተያዘው የክረምት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ለመሰማራት ተለይተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ትናንት ሲጀምር ወጣቶቹ በደሴ ዙሪያ ወረዳ 017 ቀበሌ ልዩ ስሙ ጠባሲት በተባለ ስፍራ ከ3 ሺህ በላይ ችግኝ ተክለዋል።

በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት ተማሪ ጀማል መሐመድ እንዳለው በአካባቢው ላለፉት አራት ዓመታት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠቱን ገልጿል።

የአከባቢው የአስተዳደር አካላት ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ልዩ ትኩረትና ዝግጅት እያደረጉ መምጣታቸውን ከዚህ ዓመት አጀማመር መገንዘብ ይቻላል ብሏል።

Published in ማህበራዊ

ነገሌ ሃምሌ 7/2009 በጉጂ ዞን 375 ሺህ አርብቶአደር ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሦስት ሆስፒታሎች ግንባታቸው በመፋጠን ላይ መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የግንባታ ሥራ ሂደት ተቆጣጣሪ አቶ አስጨንቅ ታምሩ እንዳሉት በዞኑ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ሲገነቡ ከነበሩ ሦስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል ።

ላለፉት አራት ዓመታት በግንባታ ላይ ከነበሩ ሦስት ሆስፒታሎች መካከል ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነው የቦሬ ሆስፒታል ነው።

የኡራጋ ሆስፒታል ግንባታ 90 በመቶ እንዲሁም የሰባ ቦሩ ሆስፒታል 60 በመቶ መድረሳቸውን የገለጹት ተቆጣጣሪው፣ ሆስፒታሎቹን ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ ግንባታቸውን የማፋጠን ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። 

እንደ አቶ አስጨንቅ ገለጻ፣ የሆስፒታሎቹ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገቡ 375 ሺህ የዞኑ አርብቶአደርና ከፊል አርሶአደሮች የጤና አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።

ሆስፒታሎቹ የተሟላ የቤተሙከራ፣ የራጅ፣ የድንገተኛ ሕክምና፣ የምርመራ፣ የመኝታና የመድኃኒት አገልግሎት መስጠት በሚያስችል መልኩ በመገንባት ላይ መሆናቸውን አቶ አስጨንቅ አስረድተዋል ።

በዞኑ በመንግስት የተገነቡ አምስት ሆስፒታሎች ፣ 59 ጤና ጣቢያዎችና 300 ጤና ኬላዎች  በአሁኑ ወቅት ለሕብረተሰቡ  አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸው ተመልክቷል ።

የቦሬ ከተማ ነዋሪ አቶ ገመዳ ኡዶ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ግንባታው በሆስፒታል ደረጃ ሕክምና ለማግኘት ይርጋለም፣ ሻሸመኔና ወላይታ ድረስ በመሄድ ይባክን የነበረውን ወጭና ጊዜ ያስቀራል የሚል ተስፋ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ አርፋሶ በበኩላቸው፣ በቦሬ ከተማ አገልግሎት የሚሰጥ ጤና ጣቢያ ቢኖርም ተኝቶ ለመታከምና የተሟላ የቤተሙከራ ምርመራ ለማከሄድ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የሆስፒታሎቹ መገንባት ለእነዚህ ችግሮች እልባት ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ገመዳ ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ነገሌ ሀምሌ 7/2009 በጉጂ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ማህበራት የተደራጁ 31 ሺህ 561 ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን የዞኑ የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምከትል ኃላፊ አቶ አብዱራዛቅ ሁሴን እንዳሉት ወጣቶቹ በዋናነት ወደ ሥራ የገቡት በግንባታ፣ በንግድና በግብርና የሥራ ዘርፎች ነው፡፡

መንግስት ለወጣቶቹ 840 ሄክታር የእርሻ መሬት፣ ዘጠኝ የእርሻ ትራክተሮች፣ አንድ የህትመት መሳሪያና 56 የመሸጫ ሱቆች ሰጥቶአቸዋል።

በመንግስት ከተፈቀደ የወጣቶች ተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድር 78 ሚሊዮን 310 ሺህ ብር እንዲሁም ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ባንክ 29 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር ለወጣቶቹ በብድር መለቀቁን አቶ አብዱረዛቅ ተናግረዋል።

ወደሥራ የገቡ ወጣቶችም እስካሁን ድረስ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠብ እንደቻሉ ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

አንደ አቶ አብዱራዛቅ ገለጻ፣ በዚህ ዓመት ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡ ወጣቶች መካከል ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው ።

መንግስት ለዞኑ ወጣቶች የፈቀደው 220 ሚሊዮን ተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድር ሙሉ በሙሉ ባለመለቀቁ አሁንም በማህበር የተደራጁ 17 ሺህ 577 ወጣቶች ገንዘቡን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ምክትል ኃላፊው አያይዘው ገልፀዋል።

በነገሌ ከተማ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ተደራጅተው የህንጻ መሳሪያ መሸጫ ሱቅ መክፈታቸውን የገለጸው ወጣት ሳሙኤል መዝገቡ፣ በእዚህ ዓመት 250 ሺህ ብር ብድር ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጿል፡፡

ወጣቱ ከባልደረቦቹ ጋር ሥራ ከጀመረ ሁለት ወር ቢሆነውም በቀን ከሚያገኙት አንድ ሺህ ብር ትርፍ 500ብር እየቆጠቡ መሆናቸውን ተናግሯል ፡፡

ቀደም ሲል በቀን ዘጠና ብር እየተከፈለው በጉልበት ሥራ ይተዳደር እንደነበር ያስታወሰው ወጣቱ፣ አሁን በተፈጠረለት የሥራ እድል የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደጀመረ ተናግሯል ።

ሌላው የነገሌ ከተማ ወጣት ይድነቃቸው ክፍሌ በበኩሉ ከባልደረቦቹ ጋር ከመንግስት ባገኙት የገንዘብ ብድር የሱቅ ንግድ ሥራ ቢጀምሩም ለሚሰሩበት ቤት ኪራይ 1ሺህ 200 የሚከፍሉ መሆናቸው ብዙም ትርፋማ እንዳላደረጋቸው ገልጿል፡፡

"መንግስት ብድር በመስጠት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረው ጥረት መልካም ቢሆንም አሁንም የማምረቻና የመስሪያ ቦታ  ችግር እያጋጠመ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል" ብሏል ወጣት ይድነቃቸው።

ወጣቱ ከባልደረቦቹ ጋር ለግለሰብ የቤት ኪራይ እየከፈሉ ቢሰሩም ከሚያገኙት ገቢ ላይ በማህበር 30 ሺህ ብር መቆጠብ እንደቻሉና የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ቢሰጣቸው የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግሯል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ሃምሌ 7/2009 በጋምቤላ ክልል "ሚሞሳ" ተብሎ የሚጠራው መጤ አረም በሰብልና በግጦሽ ማሳቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ አርሶና ከፊል አርብቶደሮች ገለጹ።

የክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም በበኩሉ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውና በአካባቢው አጠራር "እትንኩኝ" ተብሎ የሚጠራውን ይህን አረም ለመከላከል የምርምር ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ አርሶና ከፊል አርብቶአደሮች በሰጡት አስተያየት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከሰተው "አትንኩኝ" የተባለው መጤ አረም በእርሻና በግጦች መሬት ላይ በፍጥነት እየተዛመተ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአቦቦ ወረዳ የመንደር 13 ነዋሪ አርሶአደር ኑርዬ አንሸቦ እንደገለጹት፣ አረሙ እሾሀማ ከመሆኑ በተጨማሪ ስርጭቱ ፈጣን በመሆኑ በሰብልና በግጦች መሬት ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

"አትንኩኝ የተባለው መጤ አረም በሰብል ላይ በተለይ በሰሊጥ፣ በሩዝና ሌሎች ቁመት በሌላቸው ሰብሎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና የምርት መቀነስ ከፍተኛ ነው" ያሉት ደግሞ የዚሁ መንደር አርሶና ከፊል አርብቶአደር ታሪኩ በሊሁን ናቸው።

አረሙ ምርታማነታቸውን ከመቀነስ ባለፈ በከብቶቻቸው የግጦሽ መሬት ላይም ጭምር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

አርሶና ከፊል አርብቶአደሮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የሚመለከተው አካል ችግሩ የሚቃለልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ኮንግ ጆክ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ተቋሙ መጤ አረሙ በክልሉ በሰብልና በግጦች መሬት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በዳሰሳ ጥናት በመለየት ለመፍትሄው የምርምራ ሥራዎችን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት መጤ አረሙ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች  መሰራጨቱን ጠቁመው ፣በተለይም በአራት ወረዳዎች ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

ተቋሙ ባካሄዳቸው የምርምር ስራዎች አረሙን በሰው ጉልበት ከመከላከል ባለፈ ኬሚካሎችን በመጠቀም ማጥፋት እንደሚቻል አመላካች ውጤቶች መገኘታቸውና በቅርብ ጊዜም ጥናቱ ተጠቃሎ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በተቋሙ የሰብል ዘርፍ ተመራማሪ አቶ ዘሪሁን በላቸው በበኩላቸው "ሚሞሳ" ወይም ’’አትንኩኝ’’ ተብሎ የሚጠራው መጤ አረም የሰብልና የግጦሽ መሬትን በመሸፈን ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

እሾሀማ ከመሆኑ በተጨማሪ ጉበት የሚመረዝ ሚሞሲን የተባለ ኬሚካል የያዘ አረም በመሆኑ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የአረሙ አንዱ እግር እስከ 12 ሺህ የሚደርስ ፍሬዎችን ስለሚይዝ በከፍተኛ ፍጥነት የመስፋፋት ባህሪ ያለው መሆኑን አቶ ዘሪሁን ገልጸዋል።

ሚሞሳ በሳይንሳዊ ስሙ ዲፕሎራቲካ ተብሎ የሚታወቀው አረም ከአሜሪካ በናይጀሪያ በኩል ወደ አፍሪካ እንደገባ ከጋምቤላ ግብርና ምርምር ተቋም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ