አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 13 July 2017

ባህር ዳር ሐምሌ 6/2009 በአማራ ክልል አዲሱ የቀን ገቢ ግብር ግምት ኃላፊነት በተሞላበትና የነጋዴውን ትክክለኛ ገቢ መሰረት አድርጎ መሰራቱን የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ።

በተደራጀ አግባብ በተደረገ እንቅስቃሴ በክልሉ ከ274 ሺህ በላይ የሚሆኑ የደረጃ "ሀ"፣ "ለ" እና "ሐ" ግብር ከፋዮች እንዲጠኑ መደረጉ ተመልክቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር  አቶ የደሜ የሻለም ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት ነጋዴዎች በሚያገኙት ገቢ ልክ ግብር እንዲከፍሉ የመለየት ሥራ ተከናውኗል።

ለዚህም በየደረጃው ከአራት ሺህ 100 በላይ አባላትን የያዘ 860 ኮሚቴ ተቋቁሞ የነጋዴውን የቀን ገቢ ግምት ማጥናትና መለየት መቻሉን አብራርተዋል።

በጥናቱም ከዚህ በፊት በግብር መረቡ ውስጥ ያልነበሩ 50 ሺህ 490 ነጋዴዎች መገኘታቸውንና ወደ ግብር መረቡ እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።

ከ274 ሺህ 700 በላይ የደረጃ "ሀ"፣ "ለ" እና "ሐ" ግብር ከፋዮችን በጥናቱ በመለየት በሚመጥናቸው ደረጃና በሚያገኙት ገቢ ልክ ግብር እንዲከፍሉ የመለየት ሥራ መከናወኑን አቶ የደሜ አስታውቀዋል።

እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ፣ አዲሱ የገቢ ግምት ጥናት በታክስ አስተዳደሩ የሚነሱ የግብር ፍትሃዊነት ችግሮችን ለማስተካከል፣ የታክስ አስተዳደሩን ቀላልና ምቹ ለማድረግ እንዲሁም የግብር ከፋዮችን የህግ ተገዠነት የማሳደግ ዓለማ አለው።

ከዚህ በተጨማሪ ኢኮኖሚው እያመነጨ የሚገኘውን ገቢ በትክክል በመሰብሰብ የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለመመለስ፣ የግብር መሰረቱን ለማስፋትና አዳዲስ ግብር ከፋዮችን ወደ ግብር መረብ ለማስገባት ጠቀሜታ አንዳለው ገልጸዋል።

በጥናቱ ወቅት አንዳንድ ነጋዴዎች ድርጅታቸውን ዘግተው የመጥፋት፣ ህጻናትን የማስቀመጥ፣ እቃዎችን የማሸሽና መሰል ችግሮችን በመፍጠር የግምት ስራው በአግባቡ እንዳይከናወን ሲያደርጉ እንደነበር አቶ የደሜ አስታውሰዋል።

በቀጣይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ የግመታ ስራው እንደሚከናወንም አብራርተዋል።

ከሚያዚያ 23 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ግመታው የተሰራላቸው ነጋዴዎች ውጤቱን በማስታወቂያ ሰሌዳ በማሳወቅ የንግዱ ማህበረሰብ እዲገመግምና ፍትሃዊነቱን እንዲያረጋግጥ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከግንዛቤ እጥረት የቀን ገቢ ግምቱን አለአግባብ በዓመት በማባዛት ውዥንብር ውስጥ የገቡ ነጋዴዎች  መኖራቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣   በቅርቡ ትክክለኛው ግብርና ታክስ ለነጋዴው በደብዳቤ እንደሚገለጽ ተናግረዋል።

የቀን ገቢ ግምቱን በተቻለ መጠን በጥንቃቄና የነጋዴዎችን የገቢ መጠን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መከናወኑንም አስታውቀዋል።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን በቀጣዩ በጀት ዓመትም ከ10 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2009 በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት የሚቀርቡ ሸቀጦች በተለይም የዘይት፣ ስኳርና ዱቄት አቅርቦት እጥረት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳሳደረባቸው አንዳንድ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በመዲናዋ በንፋስ ስልክ፣ ልደታ፣ ጎማ ቁጠባ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሸቀጦቹ አቅርቦት ለሁሉም ነዋሪ ተደራሽ ባለመሆኑ ኢኮኖሚያቸው ላይ ካሳደረው ጫና በተጨማሪ በማህበረሰቡ መካከል አለመግባባት እየፈጠረ ነው።

በማህበራቱ በኩልም ቁጥጥር የማድረግ ችግር በመኖሩ የተወሰኑ ነጋዴዎች ሸቀጦቹን በመግዛት በእጥፍ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ለሽያጭ እንደሚያቀርቡትም ነው የተናገሩት።

"ሸቀጦች በበቂ መጠን ሊቀርቡ ይገባል፤ በነጋዴዎች ላይም ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር መደረግ አለበት" ብለዋል።

የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ የሸቀጦች አቅርቦትና የሕብረተሰቡ ቁጥር አለመመጣጠን  በተለይም በዘይት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ እጥረት መኖሩን ይናገራሉ።

ሸቀጦችን የሚያቀርቡ ድርጅቶችም "በፍጥነት ምርቶቹን እያቀረቡ አይደለም" ብለዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልበር ደጋጋ እንደገለጹት ጥያቄውን በተደጋጋሚ ጠይቀናል ክፍለ ከተማም ማዕከልም ጠይቀናል ኮታ እንዲሻሻልልን የሕዝብ ብዛት በማየት ዘይትም ይሄን ያህል ብለን አስገብተናል ቢያንስ 62 ሺህ ሊትር እንደሚያስፈልገን በየ15 ቀኑ አሁን እየቀረበ ያው 32 ሺህ ነው ይሄ በቂ እንዳልሆነና በብዛት ከዛ በላይ በእጥፍ እንደሚያስፈልገን ነው ከሕብረተሰባችን ፍላጎት አንጻር የጠየቅነው ብለዋል ።

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የግብይት ተሳታፊዎች ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ  እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲል የዘይት አስመጪ ድርጅቶች ያጋጠማቸውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የወደብ መጨናናቅ ችግር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመፍታት ተችሏል።

አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት ያለሙ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ምርቶቹን የማሸሽ፣ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትም በፍጥነት ምርቶቹን ያለመረከብና ሌሎችም ከስርጭት ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በተወሰኑ ወረዳዎች ማህበራት ከነጋዴዎችና ነጋዴዎች ከሸማቾች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ በተጀመረው የሙከራ ስራ "የዘይት አቅርቦቱን ለማሻሻል ተችሏል ነው" ያሉት።

በመሆኑም በሁሉም ወረዳዎች ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ይህም በነዋሪው ቁጥር ልክ ያለውን ክፍተት ለመለየት ስለሚያስችል የኮታ ማሻሻያ ለማድረግና ችግሩን ለማቃለል እንደሚያስችል ነው የገለጹት።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2009 ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን የፍትህ አገልግሎት ቀልጣፋና ጥራት ያለው ለማድረግ የዳኞችን ቁጥር ማሳደግ የሚያስችል ሥራ መጀመሩን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ በሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ  ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንትና የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ዳኜ መላኩ እንደተናገሩት፤ ጉዳዮች ውሳኔ ሳያገኙ መቆየታቸው፣ የቀጠሮ መብዛትና መጉላላት እንዲሁም የፍርድ ሂደት ጥራት መጓደል ህብረተሰቡ ላይ ቅሬታ አሳድሯል።

ይህም ወደ ፍርድ ቤቶች የሚመጡት ጉዳዮች በሥራ ላይ ካሉት የዳኞች ቁጥር ጋር ባለመመጣጠናቸው የተፈጠረ መሆኑን ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።

በአዲሱ ዓመት የዳኞችንና ድጋፍ ሰጪውን ቁጥር በመጨመር በፌደራል ፍርድ ቤቶች ከ183 ሺ በላይ ለሚሆኑ መዛግብት እልባት ለመስጠት መታቀዱን ገልፀዋል።

ውዝፍ መዝገቦች  ወደ ቀጣዩ ዓመት እንዳይሸጋገሩም በዳኞች የእረፍት ጊዜ ተመርምረው ለውሳኔ ዝግጁ እንዲሆኑ መወሰኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስአበባ ሀምሌ 6/2009 መንግስት ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከቀረቡለት እስከ አንድ ቢሊዮን ብር መደገፍ እንደሚችል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አስታወቁ።

ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ምክር ቤት ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አገሪቷን ከድህነት የሚያወጣ እና ለልማት የሚበጅ ማንኛውንም የምርምር ስራ ለመደገፍ መንግስት ዝግጁ ነው።

መንግስት በአገሪቷ ችግር ላይ የተቃኘ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመው፤ እነዚህ ስራዎች ከቀረቡ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ በተፈለገው ጊዜ ማድረግ እንደሚችል ቃላቸውን ሰጥተዋል።

''በኢትዮጵያ የሚካሄደው የጥናትና ምርምር ችግር በሌሎች ፍላጎትና ቅኝት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሌሎች ፍላጎትና ገንዘብ የሚከናወን ምርምር አገር የማይጠቅም መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በርካታ የሰው ኃይል የማልማት ስራ አጽንኦት ሊሰጥው እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ ትስስሩም ቢሆን በጋራ ጥቅም ላይ መመስረት እንዳለበት ጠቁመው፤ ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ የሕግ ማዕቀፍ አቅጣጫና ምክረ ሐሳብ ይዞ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

የምክር ቤቱ ሴክሬቴሪያትና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፤ አገሪቷ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ኢኖቬሽን የምትመራበት በተመረጡ 20 መስኮች ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ፍኖተ ካርታው በጥናትና ምርምሩም ሆነ በሌላው መስክ ድግግሞሽን እንደሚያስቀር ተናግረው፤ "የአገሪቷ ሀብት እንዳይባክን የሚያስችል ከመሆኑም በላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎችን የሚስብ ነው" ብለዋል።

ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ሕጻናትና ወጣቶች ችሎታቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚያዳበሩበት ማዕከል በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ ለማስገንባት ጥረት መጀመሩንም አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ አደረጃጀቱን ለማሻሻል የቀረበለትን የአሰራር መመሪያ አዳብሮ ያጸደቀ ሲሆን፤ በአገሪቱቷ ዘርፈ ብዙ የምርምር ስራዎችን በጋራ ለማከናወን የሚያስችል ዋና ላብራቶሪና ብሔራዊ የመረጃ ቋት የመፍጠር ስራ እንዲሰራም ምክረ ሐሳብ አቅርቧል።

አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2009 ጊኒ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ተሞክሮ መውሰድ እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር አስታወቁ።

በኢትዮጵያ የጊኒ አምባሳደር ፋቱማታ ካባ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት "ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ካስመዘገበችው ስኬት አገሬ ልምዶችን መውሰድ ትፈልጋለች።"

ከ13 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ድርቅና ረሃብ ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት አምባሳደሯ "ከዚያ በኋላ ባሉ ዓመታት አገሪቷ ግብርናዋን ምርታማ በማድረግ ረገድ ስኬት አስመዘግባለች" ብለዋል።

ጊኒ ከዚህ ስኬት ጀረባ ካሉ ስልቶች  ልምድ መውሰድ እንደምትፈልግም  ገልጸዋል።

ጊኒ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ  80 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ በግብርና እንደሚተዳደር ገልጸው  በዘርፉ  ስኬት ካስመዘገበችው ኢትዮጰያ የምትወስደው ልምድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም አምባሳደር ፋቱማታ ተናግረዋል፡፡

ከግብርናው በተጨማሪ በትራንስፖርት መሰረተ ልማት  ጊኒ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ መውሰድ እንደምትሻ የገለጹት አምባሳደሯ፤ በአገራቸው የትራንስፖርት መሰረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ እንዳላደገ ጠቁመዋል።

በመሆኑም በለሃብቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ እንደፈለጉ ተዘዋውረው የንግድ እንቅስቃሴ ለማከናወን እንቅፋት እንደሆነባቸው አውስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከየካቲት 2009 ዓ.ም ጀምሮ በሳምንት አራት ጊዜ ወደ ጊኒ በረራ በመጀመሩ ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ትስስር በር እየከፈተ እንደሚገኝ አምባሳደሯ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሃብት በጊኒ 'የኢትዮጵያ  ሬስቶራንት' ለመክፈት እንቅስቃሴ እንደጀመረም ጠቁመዋል፡፡