አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 12 July 2017

አዲስ አበባ ሃምሌ 5/2009 የኤሮስፔስ ኢንስቲትዩት የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን ማፋጠን ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ምክር ቤት የመጀመሪያው መደበኛ ጉባኤ በአሰራር መመሪያና በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ምክረ ሐሳቦችን በማፍለቅ ዛሬ ተጠናቋል።

በጉባዔው ላይ እንደተገለጸው፤ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወቅታዊ የልማትና መልካም አስተዳድር ችግሮችን መፍታት ያስችላል። ለዚህ ደግሞ በዩኒቨርሰቲዎች ጥልቅ ምርምር መደረግ ይኖርበታል።

የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት፤ የስፔስ ሳይንስ በኢትዮጵያ ከ40 ዓመታት በፊት ቢጀመርም ዓለም ከደረሰበት የስፔስ ቴክኖሎጂ አኳያ ወደኋላ የቀረ ነው።

በማሳያነትም ከ20 ዓመታት በፊት የጀመረችው ናይጄሪያ የራሷን ሳተላይት ከማምጠቅ አልፋ ለጎረቤት አገሮች ለማከራየት መብቃቷን አውስተዋል።

ዘርፉን ለማጎልበትም በ2005 ዓ.ም የተመሠረተው የእንጦጦ ስፔስ ሳይንስ ጥናትና ምርምር ማዕከል "የኢትዮጵያ ኤሮስፔስ ኢንስቲትዩት" በሚል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር እንዲዋቀር ተደርጓል።

የሬጉላተሪ፣ የምርምርና የልማት ዘርፍን አጣምሮ እንዲይዝ የተደረገው ኢንስቲትዩቱ፤ የ12 ዓመት የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ እቅድ መዘጋጀቱን ነው ሚኒስትሩ የጠቆሙት።

የስፔስ ሳይንስ ዘርፈ ብዙ በመሆኑም ኢንስቲትዩቱን የሚመራ ከተለያዩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የተወከሉ አባላትን ያቀፈ ምክር ቤት ተቋቁሟል።

ዘርፉ ካለው ፖለቲካዊ ፋይዳ አኳያም ምክር ቤቱ የአገር መከላከያ ሚኒስቴርን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች እንዲካተቱ ተደርጓል።

ምክር ቤቱ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ የተሻለ እንቅስቃሴ ያላቸውን የአዲስ አበባ፣ የአዳማና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎችን በአባልነት ከማቀፉ በተጨማሪ በዘርፉ ሳይንቲስቶችንም ማካተቱ ተገልጿል።

በጉባኤውም የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት የአሰራር  ረቂቅ መመሪያ ለውይይት ቀርቦ የተለያዩ ምክረ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል።

ጉባኤውን የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢንስቲትዩቱ የሚከናወኑ ተግባራትና እቅዶች "ወቅታዊ የልማትና መልካም አስተዳድር ችግሮችን የምንፈታበት መሳሪያ ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል" ብለዋል።   

በዘርፉ እየሰሩ የሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎችም የተፈለገውን ግብ ሊያመጣ የሚያስችል የሰው ኃይልና ምርምር ተግባራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ስለሆነም ኢንስቲትዩቱ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የልማትና መልካም አስተዳድር ስራዎችን ማፋጠን ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም የምክር ቤቱ አባል በሆኑ ተቋማት መካከል የስራ ድግግሞሽ በማስቀረትና ድርሻን በመለየት ጠንካራ ቅንጅት እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት አሳስበዋል።

 

መቀሌ ሀምሌ 5/2009 የትግራይ ክልልና  የሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ምክር ቤቶች ግንኙነታቸውን  ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን  ለማጠናከር  በቅንጅት እንደሚሰሩ ገለጹ፡፡

የሱዳን ገዳሪፍ ምክር ቤት የልኡካን ቡድን አባላት ከትግራይ ክልል አቻቸው ጋር ዛሬ የተሞክሮ ልምድ ልውውጥ አካሄደዋል፡፡

በመቀሌ ከተማ  በተካሄደው በዚሁ ስነስርዓት ወቅት የትግራይ ምክር ቤት  አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ የክልሉ ምክር ቤት  ህገ መንግስቱ  በሰጠው ስልጣን መሰረት በህዝብ ድምፅ የተወከሉ 152 የምክር ቤት አባላት እንዳሉት ለልኡካን ቡድኑ ገልጸዋል።

የክልሉ ምክር ቤት በወረዳና ቀበሌ ደረጃም የህዝብ ውክልና ያላቸው ምክር ቤቶች እንዳሉት ያመለከቱት አፈ ጉባኤዋ  በተዋረድ ባሉት ምክር ቤቶች የሴቶች ውክልና  50 ከመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

ህግ በማውጣት፤በጀት፣ አዋጆች፣ ደንቦችን በማፅደቅ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የፈፃሚውን አካል ስራዎች የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት እንዳለበት ነው ያስታወቁት።

የትግራይና የሱዳን ገዳሪፍ ምክር ቤቶች በህዝቦቻቸው መካከል ረጅም ዘመናት ያስቆጠ  የወድማማችነት ግንኙነት አላቸው፡፡

ይህን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር እየተባባሰ የመጣውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና ፀጥታ ማስከበርን ጨምሮ ሌሎችንም የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማጠናከር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ወይዘሮ ቅዱሳን አመልክተዋል፡፡

የገዳሪፍ  ምክር ቤት አባልና የልዑካን ቡድኑ አስተባባሪ ሚስተር መሓመድ ጠይብ አለበሽር በበኩላቸው "ከትግራይ ክልል ምክር ቤት የተጠያቂነት አሰራርን በመልካም ተሞክሮ ወስደናል" ብለዋል።

እንዲሁም ክልሉ ያስመዘገበው እድገት በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶችና ፈፃሚዎች ተቀናጅተው በመስራት  የተገኘ ውጤት እንደሆነ መገንዘብ እንደቻሉም ገልጸዋል።

ከክልሉ ያገኙትን መልካም ተሞክሮ ወደ ግዛታቸው ወስደው ተግባራዊ እንደሚያደርጉት የተናገሩት ደግሞ የገዳሪፍ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሚስተር ዓብደላ ራሕመተላ ናቸው፡፡

የትግራይ ምክር ቤት የተከተለው ነፃና ግልፅ አሰራር ክልሉ አሁን የደረሰበት  እድገት  ደረጃ ምስክር  መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ያገኙትን ልምድና ተሞክሮዎችን ከምክር ቤታቸው አሰራር ጋር  አጣጥመው ለመጠቀም ግብኣት እንደሚሆናቸው ነው ሚስተር ዓብደላ የተናገሩት፡፡

ግንኙነታቸውን  አጠናክረው በተለይም  ወጣቶች በህገወጥ አስኮብላዮች እየደረሰባቸው ያለውን ስቃይና እንግልት ለማስወገድ ተባብረው በቅንጅት ለመስራት ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ  አባላት በክልሉ መንግስትና ህዝብ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን፣ የሰማዕታት ሃውልትና  ታሪካዊው የአልነጃሺ መስጊድን ተመልክተዋል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

መቱ ሃምሌ 5/2009 በኢሉአባቦር ዞን ከ132 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የማልማት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ጥበቃና ልማት ቡድን መሪ አቶ ወንዴ ሳፎ እንዳሉት በአገዳ፣ ብርዕ እና የቅባት ሰብሎች ለማልማት እየተከናወነ ባለው የእርሻ ሥራ በ13 ወረዳዎች የሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ አርሶአደሮች ተሰማርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መሬቱ ሙሉ ለሙሉ የታረሰ ሲሆን ከ82 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬትም በዘር መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡

ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችንና ግበአትን በመጠቀም በኩል የአርሶአደሩ ልምድ እያደገ መጥቷል ያሉት ቡድን መሪው፣ በዚህ ዓመት ከ35 ሺህ ኩንታል በላይ የምርት ማሳደጊያ ግብአት በአርሶአደሮች እጅ ገብቶ ጥቅም ላይ በመዋል ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ልማቱ ሙሉ በሙሉ በመስመር የመዝራት አሰራረን በመጠቀም እንደሚከናወን የገለጹት አቶ ወንዴ፣ ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት ሙሉ የግብርና ፓኬጅ በመጠቀም እንደሚዘራም ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ የያዮ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወራቃ አያና እንዳሉት፣ በምርት ዘመኑ በወረዳው በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ከታረሰው 5 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ውስጥ ከ 4 ሺህ 400 በላይ የሚሆነው በበቆሎና ማሽላ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል፡፡

ዘንድሮ የሚለማው ባለፈው ዓመት በተሟላ የግብርና ፓኬጅ ከለማው መሬት ጋር ሲነጻጸር ከ500 ሄክታር በላይ መሬት ብልጫ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

አቶ ወራቃ እንዳሉት፣ የወረዳው አርሶአደሮች ከፋብሪካ ማዳበሪያ በተጨማሪ ከ110 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ለልማቱ ተስማሚ የሆነ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ አንድ ሄክታር የሚሆን ማሳቸውን ሙሉ ሙሉ በበቆሎ መሸፈናቸውን የገለጹት በያዮ ወረዳ ውጠቴ ቀበሌ  አርሶአደር ኢታና ጉግሳ ናቸው፡፡

የዳሪሙ ወረዳ ቤና ቀበሌ አርሶአደር አብዱልቃድር አወል በበኩላቸው አራት ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመኽሩ በበቆሎ፣ ማሽላና ሩዝ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን የእርሻ ሥራ እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ሃምሌ 5/2009 የትግራይ ክልል ወጣቶች ለማንነታቸው መገለጫ ለሆነው ባህልና ቋንቋቸው አምባሳደር ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቆመ።

ቢሮው በየዓመቱ ከነሐሴ አጋማሽ ወር ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በድምቀት የሚከበረውን የልጃገረዶች የአሸንዳ በዓል አስመልክቶ ዛሬ የፓናል ውይይት አካሂዷዋል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ እንዳሉት፣ ማንነትን ከሚያንጸባርቁ የቆዩ የትግራይ ክልል ባህሎች መካከል የ"አሸንዳ" በዓል አንዱ ነው።

በዓሉ ልጃገረዶች ባሸበረቁ ባህላዊ አልባሳትና በተንቆጠቆጡ ጌጣ ጌጦች ተውበውና ደምቀው የሚያከብሩት መሆኑን ገልጸው፣ በዓሉ ለቱሪዝም ልማት እድገት የድርሻውን እንዲወጣ በስፋት ማስተዋወቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዓሉን በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሴት ወጣቶች አሸንዳ የማንነታቸው መገለጫ መሆኑን አውቀው አምባሳደር ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዘንድሳ የአሸንዳ በዓል በክልል ደረጃ በመቀሌ ከተማ በድምቀት እንደሚከበር አቶ ዳዊት ጠቁመው፣ በተመሳሳይ በዓብይ ዓዲና በአክሱም ከተሞች በዓሉን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተናግረዋል።

የአሸንዳ በዓል አከባበርና ፋይዳውን አስመልክቶው በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የባህል ጥናት መምህር አለማዮሁ ካሳ፣ በዓሉን በድምቀት ማክበር ከተጀመረ ከ10 ዓመት በላይ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይህም የአሸንዳ በዓል ደምቆ እንዲወጣና በውጭ አገር ቱሪስቶች ይበልጥ እንዲተዋወቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአሽንዳ በዓል በትግራይና በአማራ ክልሎች በየዓመቱ በድምቀት እንደሚከበር የተናገሩት መምህሩ፣ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ድርጅት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓናል ውይይቱ ከተጋበዙ የጥበብ ባለሙያዎች መካከል አርቲስት ራሔል ኃይለ እንዳለችው፣ የክልሉን ባህልና ቋንቋ ለማስተዋውቅ የሚያግዙ ዘፈኖችና ፊልሞች ቢሰሩም እስካሁን የሚፈለገውን ውጤት አላመጡም።

በቀጣይ "ለባህላዊ አልባሳት ትኩረት ሰጥታ ለማስተዋወቅ እሰራለሁ" ስትልም አስተያየቷን ገልጻለች።

የአሸንዳን ባህል ለማስተዋወቅ አምባሳደር ሆና የተመረጠች የፊልም ባለሙያ ወጣት ፍሪያት የማነ በበኩሏ፣ በዓሉን በፊልም ሥራና በተለያየ መንገድ ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።

"የአሸንዳ በዓልን ለማስተዋወቅ በትጋት እሰራለሁ" ያለችው ደግሞ ኢትዮጵያን ወክላ በዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ላይ የተሳተፈችው ወጣት ቅሳነት ተክለሃይማኖት ናት።

በዓሉን አስመልክቶ ዛሬ በመቀሌ ከተማ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የክልሉ አመራሮች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የመቀሌ ከተማ ህዝብ ተወካዮችና ልዩ ፍላጎት ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሃምሌ 5/2009 በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ክፍት ቦታዎች ለህንፃ ግንባታና ለሌሎች አገልግሎቶች እየዋሉ መሆናቸውን ወጣቶች ተናገሩ።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ በአገሪቷ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለሌሎች አገልግሎቶች እንዳይውሉ ለማድረግ "ቦታዎቹን የመለየት ስራ እያከናወንኩ ነው" ብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ለተለያዩ ዓላማዎች እየዋሉ በመሆናቸው የወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ችግር አሳሳቢነቱ እየጨመረ መምጣቱን ወጣቶች የገለጹት።

ምንም እንኳ ብዙዎቹ ቦታዎች ለልማት መዋላቸው "ይበል" የሚያሰኝ ቢሆንም፤ ዋናውና ትልቁ ጉዳይ የሆነው የወጣቶች ጉዳይ ግን "የተረሳ ይመስላል" ሲሉ ነው ወጣቶች የተናገሩት።

በአዲስ አበባ የሽሮ ሜዳ አካባቢ ነዋሪው ወጣት ማሙሽ አካሉ  እንደተናገረው፤ ከዚህ በፊት የወጣቶች መዋያ የሆኑ ቦታዎች አማራጭ ቦታ ሳይዘጋጅ  ግንባታ በመካሄዱ ወጣቱም መዋያ በማጣቱ ለሱስ ተጋላጭ የመሆን እድሉ ሰፍቷል።

በቦሌ ቡልቡላ  አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች በፊት ስፖርታዊ እንቅሳቃሴዎችን ያደርጉበት የነበረው ቦታ ለሌላ ዓላማ በመዋሉ እንደተቸገሩ ማስተዋላቸውን የተናገሩት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ዮሃንስ ኃይሉ ናቸው።

የወጣቶቹ ጥያቄ የሆነው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን፤ ወጣቶቹ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሱባቸው ቦታዎች ዛሬ ገጽታቸው ተቀይሮ ታሪክ ሆነዋል።

ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ያስጠሩ ስፖርተኞች መነሻ በሆኑትና በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የማዘውተሪያ ቦታዎች ለሌላ ዓላማ እየዋሉ መሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

የወጣቶችና  ስፖርት ሚኒስቴርም የማዘውተረያ ቦታዎች ችግር በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች መኖሩን ያምናል። ችግሩን ለማቃለል የማዘውተሪያ ቦታዎችን የመለየት ሥራ እያከናወነ ይገኛል።

በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ እንዳሉት፤ ችግሩ የተፈጠረው ከዚህ በፊት የነበሩ የስፖርት አመራር አባላት ለማዘውተሪያ ቦታ የሰጡት ትኩርት አናሳ  ስለነበር ነው።

በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉ የማዘውተሪያ ቦታዎችን ችግር ለመታደግ መንግስት በመላ አገሪቷ የሚገኙ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ባሉ መዋቅሮች ቦታዎቹን የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት።

የማዘወተሪያ ቦታዎች የመለየቱ ስራ ከተከናወነ በኋላም የይዞታ ባለቤትነት ማረጋጋጫ ካርታ እንዲያገኙ በማድርግ "በቋሚነት ለወጣቶች የሰብዕና መገንቢያና የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ እንዲሆኑ ይደረጋል" ብለዋል።

በአዲሱ መሪ ፕላን መሰረት አዲስ የሚሰሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች የማዘውተሪያ ቦታዎችን ያካተቱ እንዲሆኑ መደረጉንም ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ተናግረዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 5/2009 በሥራ ተቋራጮችና በአማካሪ ድርጅቶች ላይ የሚስተዋለው የአቅም ክፍተት ዘርፉ እንዳያድግ እያደረገ መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ። 

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በበኩሉ የዘርፉ ባለሙያዎች "ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየሰራሁ ነው" ብሏል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሙያዎችና የማህበራት ወኪሎች የተቋራጮችና የአማካሪዎች አቅም ማነስ ከሌሎች የዘርፉ ችግሮች በበለጠ በኮንሰተራክሽን እድገት ላይ ጫና ማሳደሩን ይገልጻሉ።

የአመሃ ሥሜ የህንጻ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ባለቤትና የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፀሀፊ አቶ አመሃ ሥሜ እንደተናገሩት፤ የግንባታ ባለሙያዎች አቅም ማነስ ይስተዋልባቸዋል። 

በመሆኑም ተቋራጮች ግንባታዎችን በታቀደላቸው ጊዜ ያለማጠናቀቅና በግንባታዎቹም ላይ ጥራት እያጓደሉ መሆኑን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ የውኃ ነክ ሥራዎች ግንባታ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ታገሰም ባለሙያዎች የአቅም ክፍተት ችግር እንዳለባቸው የሚነገረውን ሀሳብ ይጋራሉ።  

በተለይም ግንባታ ከመጀመራቸው በፊት የሚካሄዱ አዋጭነትን የመሳሰሉ ጥናቶች ክፍተቶች አጠቃላይ የሥራ ሂደቱ ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።   

ባለሙያዎቹ፤ የአቅም ክፍተት መኖሩ ግንባታዎች በእቅድ እንዳይመሩና በሙያው ሥነ - ምግባር እንዳይፈጸሙ ማድረጉንም ተናግረዋል።

አግባብ ባልሆነ መልኩ እየተሰጠ ያለው የግንባታ ሥራ ፈቃድና የተቋራጮች ደረጃ ዘርፉን እየጎዳው መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግልጽ የሆነ የግዥ ሥርዓት አለመኖሩ ተቋራጮች እኩል ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ጫና ማሳደሩንም ይናገራሉ።

በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ደርቤ፤ በተለይም በሥራ ተቋራጮችና በአማካሪዎች ላይ የአቅም ክፍተት መኖሩን መስሪያ ቤታቸው እንደደረሰበት ተናግረዋል። 

በመሆኑም የፕሮጀክቶች መዘግየት፣ የግንባታ ሥራዎች ጥራት መጓደልና ከአቅም ክፍተት ጋር በተያያዘ የሥነ-ምግባር ግድፈቶችም በዘርፉ እንደሚስተዋሉ ነው የገለጹት።

አቶ ሲሳይ፤ ክፍተቱን ለመሙላት የሚቻልበት የሥልጠናና የልምድ ልውውጥ መድረኮችን በማዘጋጀት "የባለሙያዎቹን አቅም ለማጎልበት እየሰራን ነው" ብለዋል።

ከውጭ አገሮች ባለሙያዎች ጋር በመሆንም ለአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎች የቴክኖለጂ ሽግግር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አሁንም በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ከሙያው ሥነ-ምግባር ጋር በማይጣጣም መልኩ ድርጊቶችን እንዳይፈጽሙ ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ዘርፉ በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሃምሌ 5/2009 ቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ወደውጭ የሚልኩበት አዲስ አሰራር መጀመሩን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ገለፀ።

ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በሰጠው መግለጫ አርሶ አደሮችን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የቡና ግብይት ስርዓት ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን አሳውቋል።

በአዲሱ የግብይት ስርዓት መሰረትም ቡና አምራች አርሶ አደሮችና አነስተኛ አቅም ያላቸው አቅራቢዎች በቀጥታ ምርታቸውን ወደ ውጭ መላክና ለላኪዎች ማቅረብ ይችላሉ ።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ  አዲስ የተዘረጋው የቡና ግብይት ሥርዓት አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብይት ሥርዓቱ የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠርና ችግሮችን በማቃለል የቡና የወጭ ንግድን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተመልከቷል።

እንደ አቶ ኤርሚያስ ገለፃ፤ ከዚህ በፊት በነበረው ግብይት ላኪዎችና አምራች አርሶ አደሮች የሚገናኙት በደላሎች አማካኝነት በመሆኑ አርሶ አደሮቹ ተገቢውን ጥቅም አያገኙም።

በአዲሱ አሠራር አምራቾቹ በቀጥታ መላክ የሚችሉበትና ከላኪዎች ጋር የሚያገናኛቸው ሥርዓት በመፈጠሩ በደላሎች አማካኝነት የሚባክነውን ጊዜ እና ገንዘብ በመቆጠብ አምራች እርሶ አደሮቹ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር እንደገለጹት፤ መስፈርቱ ከሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር በላይ የቡና እርሻ ያላቸው፣ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሚችሉና የቡና ማበጠሪያ ውል ያላቸው የሚል ነው።

በዚህም መሠረት ያለ አገናኝ መገበያየት ለሚፈልጉ ሥልጠና በመስጠት ብቃታቸው በፈተና እየተረጋገጠ ወደ ግብይት መድረኩ የሚገቡበት ዝግጅት እተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

"አራት አምራች አርሶ አደሮችም ምርታቸውን ለመላክ እንቅስቃሴ ጀምረዋል" ብለዋል።

አምራች አርሶ አደሮቹ ከምርታቸው ተጠቃሚ ሲሆኑ የምርቱ ጥራት እንደሚጠበቅም አቶ ሻፊ ተናግረዋል።

ይህም ቡና ወደ ውጪ የመላክ ንግድ እንዲጨምርና በከፍተኛ ዋጋ እንዲሸጥ እንደሚያደርገው ገልፀዋል።

የምርት ጥራቱን ለማስጠበቅም በአምራች አርሶ አደሩና በአልሚ ባለሀብቶች ትስስር እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ "ይህም  አርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት እንዲያገኝ ያደርጋል" ብለዋል።

በአዲሱ የግብይት ሥርዓት የምርት ባለቤትነትንና ምርቱ የት ቦታ እንደተመረተ ገላጭ በሆነ የተሽከርካሪ ላይ ሽያጭም ተጀምሯል።

የተሽከርካሪ ሽያጭ የምርቱን ባለቤት ማንነት በሚገልፅ መልኩ ምርቱ ወደ መጋዘን ሳይገባ በተከለለ ጥብቅ ማቆያ ውስጥ መገበያየት የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።

ምርቱ ተሽከርካሪ ላይ እንዳለ ተቀምሶና ደረጃ ተሰጥቶት ለገበያ እንዲቀርብ የሚያደርግ ሥርዓት ነው።

የተሽከርካሪ ላይ ሽያጭ ምርት ለመጫንና ለማውረድ የሚወስደውን ጊዜ ከመቆጠብ ባሻገር የተለያዩ ምርቶች እንዳይቀላቀሉ የሚያደርግ የተሻለ አሠራር መሆኑን ተመልክቷል።

Published in ኢኮኖሚ

ሃምሌ 5/2009 ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለአለም ገበያ ካቀረበችው 221 ሺህ ቶን ቡና 886 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  ገቢ አገኘች፡፡

ዥንዋ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ  ልማትና ግብይት ባለሥልጣንን ጠቅሶ በድረ-ገጹ እንዳስነበበው አገሪቱ ወደውጭ ከተላከ ቡና ለማግኘት ካቀደችው 92 በመቶውን  ማሳካት ችላለች።

ዘንድሮ ቡናን ወደውጭ በመላክ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ወደውጭ የተላከው ቡና መጠን በ11 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ያሣየ ሲሆን ገቢው ደግሞ በ20 በመቶ ሊያድግ ችሏል ነው የተባለው፡፡

ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ከምታቀርበው ቡና 86 በመቶ የሚሆነውን የሚገዙት  ጀርመን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ አሜሪካ፣ ቤልጂየም፣ ሱዳንና ደቡብ ኮሪያ ናቸው።

ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና በማቅረብ ከአፍሪካ የቀዳሚነት ድርሻ ያላት ሲሆን ይህም  ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የአገሪቱ የጀርባ አጥንት ነው ሲል ዥንዋ ዘግቧል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሃምሌ 5/2009 10ኛው የዓለም ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በኬንያ ናይሮቢ ተጀምሯል።

ዛሬ በተጀመረው የታዳጊ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሳተፉባቸው ርቀቶች በሙሉ ማጣሪያውን አልፈዋል 

በ400 ሜትር የሴቶች ማጣሪያ ውድድር አትሌት ሃና አምሳሉ እና በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት አትሌት መልካሙ አሰፋ ማጣሪያውን ካለፉ አትሌቶች መካከል ናቸው።

መልካሙ ውድድሩን 47 ሰከንድ ከ23 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ነው ከምድቡ በአንደኝነት ያጠናቀቀው።

አትሌት ሃና አምሳሉና አትሌት መልካሙ አሰፋ የግማሽ ፍጻሜ ውድድራቸውን ነገ የሚያደርጉ ይሆናል።

በ1 ሺ 500 ሜትር ወንዶች በተደረጉ ውድድሮችም አትሌት አበበ ዲሳሳና በለጠ መኮንን ማጣሪያውን አልፈዋል።

ዛሬ አመሻሽ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉበት የ800 ሜትርና የስሉስ ዝላይ ወንዶች የማጣሪያ ውድድር ይደርጋሉ።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሜዳሊያ ታገኝበታለች ተብሎ የሚጠበቀው የሦስት ሺ ሜትር ሴቶች  የፍጻሚ ውድድር ዛሬ ምሽት ይጠበቃል። 

በኬንያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው 10ኛው የዓለም ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

ውድድሩ በአፍሪካ አህጉር ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፤ ሞሮኮ በ1997 ዓ.ም አራተኛውን የታዳጊ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አስተናግዳ ነበር።

ዘጠነኛው የዓለም ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ ካሊ መደረጉ አይዘነጋም።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሃምሌ 5/2009 ክረምቱን ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ፣ የአፈር መደርመስ፣ የኤሌክትሪክና የከሰል ጪስ አደጋዎች ጉዳት እንዳያደርሱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት በክረምቱ ወቅት ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ማብራሪያ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር አማኑኤል ረዳ በመግለጫቸው እንደተናገሩት በከተማዋ የውሃ መውረጃ ቱቦዎች በቆሻሻ በመሞላታቸው የክረምቱ ከባድ ዝናብ በመንገድ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

በወንዞች ዳርቻ ያሉ ነዋሪዎች ሊጎዱ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ "የድጋፍ ግንብ ባልተሰራላቸው ከፍተኛ ቦታ ላይ ያሉ ነዋሪዎች የአፈር መደርመስ አደጋ ሊደርስባቸው ስለሚችል ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል" ነው ያሉት።

ኮማንደር አማኑኤል የቆሼ አካባቢና የእንጦጦ ኪዳነምህረት አካባቢዎች የአፈር መደርመስ ስጋት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በወቅቱ በሚፈጠረው ከፍተኛ ነፋስ አማካኝነት "የኤሌክትሪክ ገመድ መገናኘትና መበጠስም አደጋ ሊያስከትል ይችላል" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለቅዝቃዜ ተብሎ ጥቅም ላይ የሚውለው የከሰል ጢስም አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የተደፈኑ የውሃ መውረጃ ቦዮች ውስጥ ያሉ ቆሻሻዎችን የሚመለከታቸው አካላትና ህብረተሰቡ ሊያፀዳቸው እንደሚገባና በውስጣቸው ቆሻሻ ከመጣል መቆጠብ እንዳለበት ተናግረዋል።

ኮማንደሩ እንደገለፁት በዝናብ ወቅት ህብረተሰቡ ከባድ ዝናብን ተጠልሎ በማሳለፍና ባለመጣደፍ ሊደርስ ከሚችል የመኪና፣ የመውደቅና የኤሌክትሪክ አደጋ ራሱን ሊጠብቅ ይገባል።

በዚሁ ክረምት በቤተል አካባቢ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ሁለት ሺ ብር የሚገመት ንብረት ሲወድም፤ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመተውን ንብረት ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

Published in አካባቢ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ