አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 11 July 2017

አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2009 በሐምሌ ከአውሮፕላን  ነዳጅ በስተቀር  የሌሎች የነዳጅ ምርቶች ዋጋ አሁን ባለበት እንዲቀጥል መወሰኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወርሃዊ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን አስመልከቶ ለኢዜአ በላከው  መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በሰኔ በነበረበት ይቀጥላል።

በአዲስ አበባ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ግን በሰኔ ከነበረው 15 ብር ከ 40 ሳንቲም ሽያጭ ላይ በ 1 ብር ከ 06 ሳንቲም ቀንሶ 14 ብር ከ 34 ሳንቲም እንዲሸጥ መወሰኑን አመልክቷል።

በዓለም ገበያ  የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መሰረት በማድረግም እንደአስፈላጊነቱ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የነዳጅ ዋጋው እንዲስተካከል የተደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 23 ቀን 2001 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በየወሩ እንዲከለስ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2009 የታችኛውን የኦሞ ሸለቆ ቅርስ በሚመለከት የተዘጋጀው ረቂቅ የውሳኔ ሰነድ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠበቅ መልኩ እንዲዘጋጅ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የተመራ የልዑካን ቡድን ፖላንድ ክራካዎ በተካሄደው 41ኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ  ስብሰባ ተካፍሏል፡፡

ልዑካን ቡድኑ በስብሰባው ላይ ያቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ ሰነድም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ተቀባይነት አግኝቷል።

ይህም በታችኛው ኦሞ ሸለቆ የሚደረገው ጥናት “ስትራቴጂካዊ የአካባቢ ጥናት ይሁን” የሚለውን የኮሚቴ ውሳኔ ቀልብሶ በአካባቢ ተጽዕኖ ጥናት እንዲተካ የሚያደርግ መሆኑን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በመግለጫው  እንደተቆመው፤ ውጤቱ ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታከናውነው የቅርስ ማስመዝገብና ልማት እንቅስቃሴ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

"በቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሰንድ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎች አስፈላጊ ናቸው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ኢትዮጵያ ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር የዓለም ቅርስን የመጠበቅ ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ተናግረዋል።

ረቂቅ ሰነዱ ለቅርስ ጥበቃ ቁርጠኝነቷ እውቅና በሚሰጥ መልኩ እንዲዘጋጅ መደረጉም ነው መግለጫው ያመለከተው፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለ2010 በጀት ዓመት ከ40 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ።

የከተማው ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለትም ቀጥሏል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ለቀጣዩ ዓመት 40 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን 282 ሺ 660 ብር  በጀት አጽድቋል።

በጀቱ ከታክስ ነክ፣ ታክስ ካልሆኑ እና ከማዘጋጃ ቤት ገቢዎች፣ ከመንገድ ፈንድ እንዲሁም ከውጭ እርዳታና ብድር የሚገኝ ነው።

የጸደቀው በጀት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 ነጥብ 4 በመቶ ወይም 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ብልጫ ዓለው።

በጀቱ የተመደበው በከተማይቱ ለሚከናወኑ የመንገድ ፣የመጠጥ ውሃ ፣የጤና ፣ የትምህርት ፣ የትራንስፖርት ፣ የፀጥታና ፍትህ ፣ የአረንጓዴ ፣ የፅዳትና ፓርክ ልማት ስራዎችን ለማከናወን ይውላል።

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት፣ መሬት ልማትና ማኔጅመንት፣ ቤቶች ልማት እና ሌሎችም በጀቱ የተመደበላቸው ዘርፎች እንደሆኑም ታውቋል።

ድህነትን በመቀነስና እድገትን በማፋጠን ወሳኝ ሚና ለሚጫወቱ የልማት መስኮች፣ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የካፒታል ክምችት ለሚያሳድጉና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን የሚያረጋግጡ ዘርፎችም የበጀት ዓመቱ የትኩረት መስኮች ናቸው፡፡

ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን እርካታ ለማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ በአንደኛና ሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውጤታማ አፈጻጸሞችን ይበልጥ ለማሻሻል፣ የዘላቂ ልማት ግቦችን ታሳቢ በማድረግ ነው በጀቱ የተዘጋጀው።

የከተማው ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ እስከ ፊታችን ሐሙስ ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2009 የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ የከተዋማን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ለዚህም የ2009 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው። 

የ15 ኛው የአዲስ አበባ ከተማ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ዛሬ ተጀምሯል።

ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ ወጣት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

እነዚህ ወጣቶች  በክረምትና በበጋ ወራት በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት የከተዋማን ማህበራዊ ችግሮች  እንዲቃለሉ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መርሃ ግብሩን ሲከፍቱ ተናግረዋል።

መንግሥት የወጣቶችን የልማት ፓኬጅ ቀርጾ ተግባራዊ ማድረጉን አቶ ደመቀ ገልጸው፤ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ ዘመቻ ሲሰማሩ ነፃ ሰጥቶ የመቀበል መርህን የሚተገብሩበት መሆኑንም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

መንግሥት ለክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ ስኬትም አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

Image may contain: 5 people, people on stage, people standing and indoor

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አበባ ሲራጅ በበኩላቸው፤ በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶች መልካም ሥራን ሰርተው የአዕምሮ እርካታን ከማግኘት ባለፈ ጊዜያቸውን በአልባሌ ሥፍራ እንዳያሳልፉ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው እንደሚሉት፤ የበጎ ፍቃደኝነት መገለጫ  አገር ወዳድነት፣ "እኔም ድርሻ" አለኝ ባይነት፣ከራስ በላይ ለሆነ አላማ ራስን ማጨት ነው።

የከተማዋ ወጣቶች በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በመንግስትና በሌሎች የልማት ኃይሎች ያልተዳሰሱ የከተማዋ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ወጣት አባይነህ አስማረ "የ2009 የወጣቶች የበጎ ፈቃድና ማኅበራዊ አገልግሎት መርሃ ግብር ከ900 ሺ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት የምናስመዘግብበበት ይሆናል" ብሏል።

ከክረምት በጎ ፈቃድ ተሳታፊ ወጣቶች መካከል ወጣት ሚሊዮን ሸዋንግዛውና ወጣት መንግሥቱ ፀጋዬ በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን በመግለጽ ሌሎች ወጣቶችም የእነርሱን አርአያ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

እስከ ጳጉሜ ሶስት ቀን በሚቆየው በዘንድሮው የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ከ900 ሺ በላይ ወጣቶች በተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ ለማሳተፍ 50 ሚሊዮን የሚገመት ዕውቀትና ጉልበት ለከተማዋ ለማዋል ታቅዷል።

Published in ማህበራዊ

አሶሳ ሀምሌ 4/2009 ራሱን የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ብሎ የሚጠራው ቡድን አባላትና አመራሮች መመለሳቸው በክልሉ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ክልሉ ያለው የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ ፣ እየተመዘገበ የሚገኘው የልማትና የመልካም አስተዳደር ስኬት የቡድኑ አባላትና  አመራሮች ወደ ክልሉ እንዲመለሱ ምክንያት ሆኗል፡፡

ሀገሪቱ ሰላምን መሰረት አድርጋ መስራቷ ተከታታይና ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ድህነትን በአጭር ጊዜ ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ 

"የክልሉ ህዝቦችም የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ቀጣይነት ሊኖረው የሚችለው ሠላም ሲረጋገጥ እንደሆነ በመገንዘብ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመታገል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ "ብለዋል፡፡

ህዝቡ ለሰላሙ መጠበቅ ያለው ቁርጠኝነት የቡድኑ አባላትና አመራሮች  ወደ ክልላቸው በመመለስ በሠላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስገድድ መሆኑን አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል፡፡ 

የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም  ኃይሎች ኤርትራን የመሳሰሉ አገራትን ማዕከል በማድረግ ሰላምና ልማትን ለማደናቀፍ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል፡፡

የቡድኑ አባላትና አመራሮች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ በተደረገው ጥረት ውስጥ ድርሻ ለነበራቸው አካላት ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

"ለተመለሱት የቡድኑ  አባላት በሕገ-መንግስቱ ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጣቸውና በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራት የራሳቸው መተዳደሪያ እንዲኖራቸው ክልሉ እገዛ ያደርጋልም" ብለዋል፡፡

እራሱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነጻነት ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው ቡድን 95 አባላት የአመጽ ድርጊታቸውን ትተው ከመንግስት ጋር በመስማማት በቅርቡ ወደ ሀገራቸው መግባታቸውንና ከመካከላቸውም 15ቱ በካርቱም ይኖሩ የነበሩ የድርጅቱ አመራር አካላት እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2009 በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በምገባ መርሃ ግብር የተካተቱና በክረምት ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ ጥሪ አቀረቡ።

ቀዳማዊ እመቤቷ ጥሪውን ያቀረቡት በክረምት ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አንድ መቶ ተማሪዎች የገንዘብና ምግብ ድጋፍ በተደረገበት ስነ ስርዓት ላይ ነው።

ኤሌምቱ የተቀናጀ ወተት ኢንዱስትሪ አክስዮን ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በላቸው ሁሪሳ በግላቸው ለአንድ መቶ ተማሪዎች ለአንድ ወር በቀን ግማሽ ሊትር ወተትና የቻይና የድህነት ቅነሳ ፋውንዴሽን 10 ሺ ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።

ወይዘሮ ሮማን በዚሁ ወቅት፤ "በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚካሄደው መርሃ ግብር በበጋ ወራት በመሆኑ ተማሪዎች ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንዲሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል።

በተለይም የኤች.አይ.ቪ በደማቸው ያለባቸው ተማሪዎች የክረምቱን ቅዝቃዜና ውርጭ ተቋቁመው ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ሲሸጋገሩ እንዳይከብዳቸው ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ ስለተደረገው ድጋፍ በማመስገን ሌሎች ድርጅቶችና ግለሰቦች ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

Displaying 04.10.09.first lady1..jpg

የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማሕበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ደብረወርቅ ልኡልሰገድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የምገባ መርሃ ግብሩ በክረምት ወቅት  ሲቋረጥ ገቢያቸው በጣም ዝቅተኛ የሆኑና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች በቀጣዩ ትምህርት ወቅት ጫና እንዳይፈጠር ለማድረግ የታሰበ ነው።

ተማሪዎችም ያጋጠማቸውን ጊዜአዊ የምግብና ሌሎች ችግሮችን ተቋቁመው በትምህርታቸው ጠንክረው የነገ አገር ተረካቢዎች እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ድጋፍ ያደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች በቀጣይም የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

Displaying 04.10.09.first lady2...jpg

በተጨማሪም ቤተ አማን የዓይን ህክምና ለሁለት ሺ ተማሪዎች አጠቃላይ የዓይን ህክምና ለመስጠት ከገባው ቃል የመጀመሪያ ተጠቃሚዎች እነዚህ ተማሪዎች እንደሚሆኑ ነው የተጠቆመው።

የተማሪዎች ምገባ በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን ከ20 ሺ በላይ ተማሪዎች በመርሃ ግብሩ ተካተዋል። 

መርኃ ግብሩ በ2007 ዓ.ም 5 ሺ100 ተማሪዎችን በመመገብ የተጀመረ መሆኑን ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ /ደሴ ሀምሌ 4/2009 በትግራይና አማራ ክልሎች ከ403 ሺህ 440 በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡

በሁለቱም ክልሎች ለተከናወኑት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች 449 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር  ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡

ከአውሮፓ ህብረት ባንክና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በተገኘ 199  ሚሊዮን ገደማ ብር  ብድር በትግራይ ክልል የተገነቡት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ147 ሺህ የሚበልጡ የማይጨውና አዲግራት ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡

ፕሮጀክቶቹ በተቋራጭ አቅም ውስንነትና በግብዓት እጥረት ምክንያት መጠናቀቅ ከነበረባቸው ጊዜ አምስት ዓመታትን ዘግይተው ነው ለአገልግሎት የበቁት፡፡

የክልሉ ውሃ ኃብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ተስፋሚካኤል ገብረዮሐንስ  የክልሉን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት  ከ80 በላይ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተተገበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ከአውሮፓ ህብረትና ከክልሉ መንግስት በተገኘ ከ250 ሚሊዮን በላይ ብር ተገንብተው ከ256 ሺህ 440 የሚልቁ የከሚሴ፣ ሸዋሮቢት፣ አጣዬ፣ ወረኢሉና መርሳ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ በተከናወነው ተግባር ባለፈው ዓመት 65 በመቶ የነበረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን  75 በመቶ ማድረስ ተችሏል።

የከተሞች በፍጥነት ማደግ በዘርፉ ተከታታይነት ያለው ስራ መስራትን እንደሚጠይቅ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

በሁለቱም ክልሎች የተገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶችን የመረቁት የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ "በአገሪቱ በ2023 ሁሉንም ዜጋ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ በራስ አቅምና በለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ስራዎች ይቀጥላሉ" ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከተሞቹን ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት የንጹህ መጠጥ ወሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርጓቸውም ነው የተናገሩት፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ አገልግሎቱን በቅርበት በማግኘት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ሰመራ ሀምሌ 4/2009 በእድሳት ላይ ሚገኘው የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 21 ቀናት አገልግሎት መስጠት ማቋረጡን የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለኢዚአ እንደተናገሩት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የአየርማረፊያዎችን ደረጃ የማሻሻልና ተደራሽ የማድረግ ሥራ ትኩረት የተሰጠው ቁልፍ ተግባር ነው።

በእዚህም በጠጠር ደረጃ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የሰመራ አየር ማረፊያ ወደ ኮንክሪት አስፓልት እንዲያድግ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተካሄደ ባለው የእድሳት ሥራ ምክንያት ለቀጣዮቹ 21 ቀናት አየር ማረፊያው አገልግሎት የማይሰጥ በመሆኑ ተጋዦች የኮምቦልቻንና መቀሌን አየርማረፊያዎች በአማራጭነት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በአየር ማረፊያው የማሻሻያ ሥራ ደረጃውን የጠበቀ የመንገደኞች ማረፊያ ተርሚናል ግንባታ ሥራ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ ይገኛል።

ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የአውሮፕላን መንደርደሪያ ኮንክሪት አስፓልት 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር ስፋት አለው።

ከአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳው ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአሁኑ ወቅት ግንባታው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪው የአውሮፕላን መንደርደሪያ የመጀመሪያ ደረጃ አስፓልት መልበሱን አቶ ወንድም አመልክተዋል።

ቀሪ ሥራዎችን በቀጣዮቹ 21 ቀናት ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ አየር ማረፊያው ሥራውን እንዲጀምር የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከሦስት ወር በፊት ግንባታው የተጀመረው ተርሚናል በአሁኑ ወቅት ሃያ በመቶ መጠናቀቁን አስታውሰው፣ ተርሚናሉን ክልሉ በቀጣይ ዓመት ለሚያስተናግደው 12ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ለማድረስ በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ተርሚናሉ የክልሉን ከፍተኛ ሙቀት ለመቋቋም በሚችል ዲዛይንና የሕብረተሰቡን ባህል በሚወክል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን በአንድ ጊዜ 150 መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም አለው።

ከእዚህ በተጨማሪ ልዩ መስተንገዶ የሚያስፈልጋቸው እንግዶች የሚስተናግዱበት ክፍሎች እንዲኖሩት መደረጉን ኃላፊው አቶ ወንድም ገልጸዋል።

የአየር ማረፊያውን ደረጃ ማሳደግ ስራዉ ተጠናቆ ለአገልገሎት ሲበቃ አሁን እያስተናገደ ከሚገኘዉ "Q-400" አውሮፕላን በተጨማሪ "ቦይንግ 737" አውሮፕላኖችን ማስተናገድ ይችላል።

ይህም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን ከማሻሻል ባለፈ እያደገ የመጣውን የተጓዥ ቁጥር በአግባቡ ለማስተናገድ የጎላ ፈይዳ እንደሚኖረው ነው የገለጹት።

ኤርፖርቱ ደረጃውን እንዲያድግ መደረጉ ለክልሉ ሕብረተሰብ ዘረፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ እንደሚያበረክትም አመልክተዋል።

የሰመራ ኤርፖርት የበረራ አገልግሎት ሥራውን ታህሳስ 2006 ዓ.ም እንደጀመረ ይታወቃል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ሀምሌ 4/2009 የአማራ ክልላዊ መንግስት  ምክር ቤት  ሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ከሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም  ጀምሮ ለስድስት ቀናት በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ እንደሚመክር ምክር ቤቱ አስታወቀ፡፡

የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ጉባኤው በ2009 የበጀት ዓመት የተከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አስመልከቶ በሚቀርብ ሪፖርት ላይ ይወያያል፡፡

እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የዋና ኦዲተርና የምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሪፖርቶችም በጉባኤው ላይ ቀርበው ይመከርባቸዋል።

በሚቀርቡ ሪፖርቶችም የጉባኤው ተሳታፊዎች ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት የተሻሉ አፈጻጸሞች እንዲቀጥሉና ክፍቶችም እንዲስተካከሉ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅንና የ2010 የስራ ዘመን ማስፈጸሚያ ረቂቅ በጀትን መርምሮ እንደሚያፀድቅ ያመለከቱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ የተለያዩ ሹመቶችንም ይሰጣል ብለዋል።

ምክር ቤቱ የሚወያይባቸው  አጀንዳዎችና የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች በአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይህም ህዝቡ በአጀንዳዎቹ ዙሪያና የሚወሰኑ ጉዳዮችንም እንዲያውቅ መደረጉ በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት በቂ መነሻ እንዲይዝ ያደርጋል ብለዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ጎንደር ሀምሌ 4/2009 በሰሜን ጎንደር ቋራና መተማ ወረዳዎች 159 ሺህ  ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የእጣን ዛፍ በማህበረሰብ አሳታፊ የደን መርሃ ግብር ጥበቃ እየተደረገለት ነው፡፡

በዞኑ ግብርና መምሪያ የደን ልማት ባለሙያ አቶ ሙሉቀን ተፈራ ለኢዜአ እንዳሉት በወረዳዎቹ የእጣን ዛፍን ከጉዳት ለመጠበቅ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጥበቃና ልማት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡

ጥበቃ ከሚደረግለት ውስጥም 6ሺህ  ሄክታር የሚሸፍን የእጣንና ሙጫ ዛፍ በ41 ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች  ተሰጥቷል፡፡

በመተማ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የደንና አግሮፎረስተሪ ባለሙያ አቶ ደጉ ዘገዬ በበኩላቸው በወረዳው የእጣን ዛፍን ጨምሮ 92 ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ደን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተከልሎ ጥበቃና ክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወረዳውን ወጣቶች በደን ልማትና ጥበቃ አሳትፎ ተጠቃሚ በማድረግ በኩልም በ14 ቀበሌዎች በ21 ማህበራት የተደራጁ ከ3ሺህ በላይ ስራአጥ ወጣቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ ወጣቶቹ ዛፎችን በመከባከብ ከአምና ጀምሮ የእጣን ምርትን ለገበያ በማቅረብ ህይወታቸውን እንዲመሩ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡

በመተማ ወረዳ የአዲስ ህይወት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ግብይት ህብረት ስራ ማህበር ሊቀ-መንበር ወጣት በየነ ውቤ ማህበሩ 162 አባላት እንዳሉትና 6ሺ ሄክታር የእጣን ዛፍ ተረክበው እያለሙ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

"የማህበሩ አባላት አምናና ዘንድሮ 850 ኩንታል እጣን አምርተው ለገበያ በማቅረብ ሦስት ነጥብ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል" ብሏል፡፡

በሰሜን ጎንደር እጣንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎች የሚገኝበት 288 ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ደን እንደሚገኝ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  

Published in አካባቢ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ