አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 10 July 2017

አዲስ አበባ ሀምሌ3/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት በተያዘው በጀት ዓመት የመዲናዋን የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈቱና ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንሰራለን አሉ።

መስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ በከተማዋ ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለማጠናከርና ለመገንባት፣ ሥራ አጥነትን በተደራጀ መልኩ ለመፍታትና ልማታዊ የመሬት ልማት አስተዳደር እንዲጠናከር የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጧል።

በትምህርትና በጤና ዘርፎች የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ፣ የቤት ልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩና የከተማዋን የውሃ አቅርቦት መጨመርም ሌላው ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የምክር ቤት አባላት የትኩረት አቅጣጫዎቹ እንዲሳኩ በተለይ ህዝብና መንግስትን የበለጠ የሚያቀራርቡ፣ የከተማ ልማት የሚያረጋግጡ ተግባራት እንዲጎለብቱና የበለጠ እንዲስፋፉ እንሰራለን ብለዋል። 

ከአባላቱ መካከል አቶ ኃይሌ አጽብሃ እንደገለጹት "መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ባካሄደው ተሃድሶ ባስቀመጠው አቅጣጫ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው"።

ለውጡን ለማስቀጠል በቀጣይ የምክር ቤቱ አባላት፣ አስፈጻሚውና ኀብረተሰቡ የከተማዋን የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈቱና የህዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊረባረቡ ይገባል።

አስፈጻሚ አካላትም ሥራቸውን በትኩረትና በጥልቀት ጊዜ ሰጥተው ተፈጻሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ለዚህም እንደ ህዝብ ተወካዮች ህዝቡን የማነቃቃትና የማሳተፍ ሥራ በስፋት እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ሃጂ ተሻለ ገብሬ በበኩላቸው ምክር ቤቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚቀርፉ ሥራዎችን በመስራትና የህዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የህዝብ አለኝታነቱን የሚያሳይ ስራ እንሰራለን ይላሉ።       

ምክር ቤቱ እስከ ታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ በመውረድ ኀብረተሰቡን የማሳወቅና የማስረዳት እንዲሁም አስፈጻሚውን የበለጠ መከታተል፣ መቆጣጠርና መደገፍም በትኩረት ከሚሰሩባቸው መካከል እንደሚጠቀስ አክለዋል።   

ስለሆነም የምክር ቤቱ አባላት ጠንካራ ጎኖች የበለጠ እንዲጎለብቱና ደካማ ጎኖች ደግሞ በፍጥነት እንዲታረሙ የሚያደርግ ተግባር ለማከናወን ያስችለናል ብለዋል።

ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ አበበች ነጋሽ ከመልካም አስተዳዳር አኳያ ብዙ ሊፈቱና ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ተገንዝበን እንደ ምክር ቤት አባል በንቃት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።       

በተለይ የአስፈጻሚውን አቅም በመገንባት፣ የወጣቱን የስራ ፈጠራና ፍላጎት በሟሟላት፣ የትምህርትና የጤና ሽፋንና ጥራት የበለጠ በማረጋገጥ፣ ጉዳዮች በትኩራት እንሰራለን ብለዋል።  

''የምክር ቤቱ አባላት በዘንድሮ በጀት ዓመት ያሳዩትን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የበለጠ በማጎልበት ያልተፈቱ ችግሮች እንዲፈቱ በሚያደረጉ ተግባራት ላይ እንደሚሰሩ የጠቆሙት ደግሞ ሌላው አባል አቶ እርቅይሁን ፎሌ ናቸው።

ይህም ያልተፈቱ ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን እርካታ ለመጨመር እንደሚያግዝ አስረድተዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማ ደረጃ 564፣ በክፍለ ከተማ ደረጃ 1 ሺህ 719 እና በወረዳ ደረጃ ደግሞ 4 ሺህ 476 የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ተንቀሷቅሷል።    

በዚህም በከተማና በወረዳ ደረጃ 76 በመቶ እንዲሁም በክፍለ ከተማ ደረጃ 75 በመቶ የሚሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት መቻሉን  ከአስተዳደሩ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

 

Published in ፖለቲካ

ሽሬ እንዳስላሴ ሃምሌ 3/2009 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ ወጣቶች 134 ሚሊዮን ብር ብድር  ተሰጠ፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገብረስላሴ ታረቀኝ  ለኢዜአ እንደገለጹት ብድሩ የተሰጠው በማህበር ለተደራጁ  አራት ሺህ 831 ወጣቶች ነው።

ወጣቶቹ ባቀረቡት የስራ  እቅድ  መሰረት ባለፈው ወር  እስከ ሩብ ሚሊዮን የሚደርስ የገንዘብ ብድር ደርሷቸዋል፤ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል  ግንባታ፣ ከብት ማደለብ፣ ንብ እርባታ ፣ ወተት ልማትና ንግድ ይገኙበታል፡፡

ከብድሩ ተጠቃሚዎች ውስጥም  ሁለት ሺህ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ያመለከቱት  አቶ ገብረስላሴ ገንዘቡ  የተገኘው መንግስት ከመደበው ተዘዋዋሪ ብድር ፣ ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምና ከከተማ የምግብ ዋስትና ፈንድ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከብድር አቅርቦት ሌላ የስራ አመራር ስልጠናና የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው ወደፊትም ወጣቶች በሚያቀርቡት የስራ እቅድ መሰረት የሚሰጠው  የገንዘብ ድጋፍ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል፡፡

በዞኑ የመደባይ ዛና ወረዳ ነዋሪ ወጣት አስፋ በላይ ተደራጅተው ወደ ስራ ከገቡት መካከል አንዱ ሲሆን የዘገየውን የብድር ገንዘብ  አሁን በማግኘታቸው  50 ዘመናዊ ቆፎ ገዝተው በማነብ ሥራ መሰማራታቸውን ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡

የወረዳው ነዋሪ ወጣት አልማዝ ግርማይ በበኩሏ ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር በማህበር በመደራጀት  በእንስሳት ማርባት ሥራ ተሰማርተን የራሳችን ገቢ ለማግኘት እየተጋን ነን ብላለች።

ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተደራጅተው ባገኙት የብድር ገንዘብ  ሁለት ባጃጆችን  ለመግዛት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ  የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሰሎሞን ካልአዩ ነው።

ወጣቶቹ እንዳሉት መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ  ተበረታትተው ራሳቸውን ለመቻል ጠንክረው እየሰሩ ናቸው፡፡ 

Published in ማህበራዊ

ሽሬ እንዳስላሴ ሀምሌ 3/2009 ጤፍን በኩታገጠምና በመስመር በመዝራት የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ እየተጉ መሆናቸውን በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ታህታይ ቆራሮ ወረዳ የሚገኙ አንዳንድ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በወረዳው ‘‘ማይ አድራሻ‘‘ በተባለ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ነጋሲ ታፈረ እንዳሉት፣“ባለፈው የምርት ወቅት በመስመር ከዘራሁት አንድ ሄክታር ማሳ 22 ኩንታል የጤፍ ምርት አግኝቻለሁ”ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በብተናና ግብአት በአግባቡ ሳይጠቀሙ በጤፍ ከሚሸፍኑት ማሳቸው ከሰባት ኩንታል የዘለለ ምርት አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አባዲ ሽሻይ በበኩላቸው፣ ጤፍን በመስመር መዝራት አድካሚ ቢሆንም ውጤቱ ግን አርኪ ነው፡፡

ባለፈው የምርት ዘመን የምርት ግብአት በሚገባ ተጠቅመው በመስመር ከዘሩት ግማሽ ሄክታር ማሳቸው ዘጠኝ ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ያገኙትን ምርት ተመሳሳይ ማሳ በብተና ዘርተው  ከሚያገኙት ከግማሽ በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

እንዲሁም በመስመር የተዘራው ጤፍ ከአረም ለማፅዳት ምቹና ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በወረዳው በምርት ዘመኑ 3 ሺህ 445 ሄክታር ማሳ ላይ ጤፍ በመስመር በመዝራት በአማካይ ከአንድ ሄክታር 22 ኵንታል ምርት ለመሰብስብ የሚያሰችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን በወረዳው ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የሰነ አዝርእት ባለሙያ አቶ ገዛኢ ህሉፍ ገልፀዋል።

''ወረዳው የጤፍ ምርት የልህቀት ማእከል ለማድረግም እየተሰራ ነው'' ብለዋል።

በወረዳው ባለፈው የምርት ወቅት በስፋት ከተዘሩት ''ኮራና ቁንጮ'' የተባሉ ምርጥ የጤፍ ዝርያዎች በቂ ምርት ለመሰብሰብ ተችሏል።

በወረዳው በአንድ ሺህ 994 ሄክታር ማሳ የተጀመረው በኩታገጠም የማልማት ሥራ ዘንድሮ ወደ 3 ሺህ 445 ሄክታር ማሳ ከፍ ብሏል።

በወረዳው በተያዘው የመኸር ወቅት 18 ሺህ 577 ሄክታር ማሳ በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ574 ሺህ ኩንታል በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሃምሌ 3/2009 ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ጅማ ከተማ  በ2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋገጡ።

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በሁለት ምድብ ተከፍሎ 32 ክለቦች ሲሳተፉበት የቆየው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ተጠናቋል።

በምድብ ሀ ተሳታፊ የነበረው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ከመቀሌ ጋር ባደረገው ጨዋታ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት በመለያየት በድምሩ 64 ነጥብ በመሰብሰብ የምድቡ አሸናፊ ሆኗል።

በምድብ ለ ደግሞ ጅማ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3 ለ 1 በማሸነፍ በ56 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለ ሌላኛው ክለብ ነው።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከስድስት ዓመታት በኋላ የትግራይን ክልል በፕሪሚየር ሊጉ የሚወክል ክለብ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልክ በ1990 ዓ.ም. ሲጀመር የትግራይ ክልልን ወክለው ጉና እና ትራንስ ኢትዮጵያ ተሳታፊ የነበሩ ቢሆንም፤ ጉና በ1998 ትራንስ ኢትዮጵያ ደግሞ በ2003 ዓ.ም ከፕሪሚየር ሊጉ በመውረዳቸው ላለፉት ስድስት ዓመታት ክልሉ በሊጉ ተወካይ አልነበረውም።

በ2010 ዓ.ም በሚደረገው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ግን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክልሉን ይወክላል።

ከምድብ ለ ወደ ፕሪሚየር ሊግ መግባቱን ያረጋገጠው  ጅማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ደግሞ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደውን ጅማ አባ ቡናን ተክቶ ኦሮሚያን በሊጉ የሚወክል ይሆናል።  

ከምድብ ሀ በሁለተኝነት ያጠናቀቀው መቀሌ ከተማና ከምድብ ለ ሁለተኛ ሀዲያ ሆሳዕና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ አሸናፊው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ይቀላቀላል።

ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድግ ሶስተኛው ክለብ የሚለይበትና የከፍተኛ ሊግ አሸናፊ የሚታወቅበት ጨዋታ ከአንድ ሳምንት በኋላ በድሬዳዋ ይካሄዳል።

አዲስ አበባ ከተማ፣ ጅማ አባ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፕሪሚየር ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረዱ ክለቦች ናቸው።

ከከፍተኛ ሊግ ሦስት ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያድጉ ስድስት ክለቦች ደግሞ ወደ ብሄራዊ ሊግ ወርደዋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሀምሌ 3/2009 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የከተማዋ ከንቲባ ገለጹ።

ከንቲባ ድሪባ ኩማ የአዲስ አበባን የ2009 ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለከተማዋ ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደገለፁት አስተዳደሩ ለግድቡ ግንባታ 150 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከ126 ሚሊዮን በላይ ብር ሰብስቧል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከከተማዋ ነዋሪዎች ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው የግሉን ባለሃብት እንደማይጨምር አስታውቀዋል።

የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን ለማድረግ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከመላው አገሪቱ ከዘጠኝ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሃምሌ 3/2009 በ60 ሆስፒታሎች በቴሌ-ራዲዮሎጂ የታገዘ ዘመናዊ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የጤና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ኢዮብ ከበደ እንደገለጹት በመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ የታገዘው ዘመናዊ  የጨረራ ህክምና አገልግሎት ስርዓት ከሶስት ሳምንታት በኋላ ይጀመራል።

መሳሪያዎቹ የሚገኙበትን ሰባት የህክምና ማዕከላት ከ60 ሆስፒታሎች ጋር በኔትወርክ በማገናኘት በጨረራ የመረጃ ግንኙነት የታገዘ የሕክምና ስርዓቱን ለመጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በመረጃ ግንኙነት መረብ /ቴሌ-ራዲዩሎጂ / ታካሚው በአካባቢው ባሉ የህክምና ተቋማት ውስጥ ሆኖ አገልግሎቱን ማግኘት የሚያስችል ነው።

ሆስፒታሎች በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የጤና ምርመራና የሕክምና አገልግሎት በተመሳሳይ መስጠት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

“በጨረራ የሕክምና ዘዴ የሚገኘውን መረጃ በልውውጥ ስርዓት ታካሚው ከአንዱ ጤና ተቋም ወደ ሌላው መሄድ ሳያስፈልገው ህክምናውን ባለበት ስፍራ እንዲያገኝ ከመርዳት ባሻገር ታካሚው የሚገጥመውን አላስፈላጊ ወጪና እንግልት ያስቀርለታል'' ብለዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ መሳሪያ ያላቸው የጤና ተቋማት ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ጥቁር አንበሳ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ጅማ፣ ሐዋሳና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች እንዲሁም ከአይደር ሆስፒታል ጋር እንደሚተሳሰሩ አብራርተዋል። 

በቀጣይም በመላው አገሪቱ ያሉ ሆስፒታሎችን በኔትወርክ መሰረተ ልማት የሚያስተሳስር ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሶስት ሺህ 500 የህክምና ተቋማት ጋር የኔትወርክ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ለማካሄድ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመረጃ መረቡ በአገሪቱ የቴሌ ህክምና ትምህርት ለመስጠት አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለጹት አቶ ኢዮብ ከዚህ ባሻገር የጤና ተቋማት ባለሙያዎች በየጊዜው ባሉበት ስፍራ የሙያ ማዳበሪያ ስልጠና እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

 

Published in ማህበራዊ

ደብረ በርሃን ሀምሌ 3/2009 በበጋ ወራት የሚካሄደው የመስኖ ልማት ያለሥራ ያባክኑት የነበረውን ጊዜ በሥራ እንዲያሳልፉና ኑሯቸውም እንዲሻሻል ማድረጉን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን  አስተያየታቸውን የሰጡ የመስኖ ተጠቃሚ አርሶአደሮች ገለጹ።

በተጠናቀቀው የበጋ ወራት በዞኑ በመስኖ  ከለማው መሬት  ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

በሞጃና ወደራ ወረዳ ነዋሪው አርሶአደር ከላላ ሀብተወልድ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በ2009 ዓ.ም የበጋ ወራት በሩብ ሄክታር መሬት ላይ  ነጭ ሽንኩርትና ምስር ማልማታቸውን ገልጸው፣ ከሽንኩርቱ ሽያጭ ከ40 ሺህ ብር ባላይ ማግኘታቸውንና ያመረቱትን አምስት ኩንታል ምስርም ለመሸጥ ገበያ እያፈላለጉ መሆኑን አስረድተዋል።

የመስኖ ሥራ መጀመራቸው የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ የወረዳው ዋና ከተማ በሆነችው ሰላ ድንጋይ ሁለት የቆርቆሮ  ቤቶችን ሰርተው በማከራየት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ማስቻሉን አመልክተዋል።

እምሻው አዘረፈኝ የተባሉ ሌላው የወረዳው አርሶአደር  በበኩላቸዉ፣ በመስኖ ያለሙትን ጎመን፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ምስር እና ድንች ገበያ አፈላልገው አዲስ አበባ ወስደዉ በመሸጥ ከ72 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በመርሐቤቴ ወረዳ የግሬት ቀበሌ አርሶአደር ደረሰ ቸርነት በበኩላቸው፣ ከጀማ ወንዝ ጀነሬተር በመጠቀም መስኖ ማልማት ከጀመሩ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት ላይ በርበሬና ቀይ ሽንኩርት በማልማት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት በበጋ መስኖ 38 ኩንታል ቀይ ሽንኩርትና 17 ኩንታል በርበሬ አልምተዉ ለአካባቢው ገበያ ቢያቀርቡም በገበያ እጦት ምክንያት 13 ሺህ ብር ብቻ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

አርሶአደር ደረሰ እንዳሉት፣ የመስኖ ልማት ሥራው ልጆቻቸውን በአግባቡ ከማስተማር ባሻገር የመኖሪያ ቤታቸውን ከሳር ክዳን ወደ 40 ሺህ ብር ግምት ያለው የቆርቆሮ ቤት ለመቀየር አስችሏቸዋል።

በተጨማሪም በዓለም ከተማ የወተት ላሞችን እና  እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን ለማርባት የሚያስችል በ18ሺህ ብር ቤት አየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወረዳዉ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ብርሃን፣ የወረዳዉ አርሶአደሮች በባህላዊ መንገድ የጀመሩትን የመስኖ ልማት ወደ ዘመናዊ አሰራር ለማሳደግ የክልሉ መንግስት በመደበው  በ50 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር "አይሰራውም" ወንዝን የመገደብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ በቀጣይ አመት ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ስራ ሲጀምር ከ600 ሄክታር በላይ መሬት በማልመት አርሶአደሮቹ ገበያ ተኮር ወደ ሆኑ ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ሥራዎች እንዲያተኩሩ ያግዛል ብለዋል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ ዉሃ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ ድፌ ወንድም አገኝ እንደለጹት፣ ባለፉት የበጋ ወራት  263ሺህ 899አርሶ አደሮች የገፀና የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም 86ሺህ 707 ሄክታር መሬት በመስኖ አልምተዋል።

እነዚህ አርሶአደሮች  ካለሙት ገበያ ተኮር የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ የስራስር  ተክሎች፣ ማሾ፣ በቆሎ፣ ቲማቲም፣ ቃሪያና ሌሎች ሰብሎች ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰበሰቡን ተናግረዋል።

በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶአደሮችም የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባሻገር ለዘላቂ ኢንቨስትመንት የሚሆን አቅም እየፈጠሩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ሃምሌ 3/2009 አማራጭ የኃይል ምንጭ የማገዶና የመብራት ወጪን በመቀነስ ኑሯቸውን ለማሻሻል  እንደረዳቸው በአማራ ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ ተጠቃሚዎች  ተናገሩ

በክልሉ  አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ  አማራጭ የኃይል ምንጭ መገልገያ መሳሪዎች  ለተጠቃሚው ተሰራጭቷል፡፡

በባህርዳር ከተማ አስተዳደር የግንቦት 20 ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰላም ሙሉጌታ እንዳሉት ማገዶ ቆጣቢ የሆነ ዝግ የእንጀራ መጋገሪያ ምድጃ ተክለው መጠቀም ከጀመሩ ዘጠኝ ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡

በዚህም  በእሳት ከመለብለብና በጭስ ምክንያት  ከሚመጣ የዓይን በሽታ ራሳቸውን እንዲጠብቁም አስችሏቸዋል።

በወር ለማገዶ መግዣ ያወጡት የነበረን እስከ 500 ብር በግማሽ በመቀነስ ኑሯቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸው ወይዘሮ ሰላም ተናግረዋል።

አርሶ አደር አምሳሉ ቆለጭ በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የዋዝንክስ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  ሶስት አምፖል ማብራት የሚችል በፀሐይ ኃይል የሚሰራ አማራጭ የኃይል ምንጭ መገልገያ  መሳሪያ  በመትከል ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው ገልጸዋል።

መሳሪያውን መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት ከኩራዙ የሚወጣው ጭስ በዓይናቸውና በመተንፈሻ አካላቸው ላይ ከነቤተሰባቸው የጤና እክል ይገጥማቸው እንደነበር አመልክተዋል።

አሁን ግን ከችግሩ ተላቀው  ልጆቻቸው መብራት ሄደ ቀረ ብለው ሳያስቡ ትምህርታቸውን  በፈለጉት ሰዓት እንዲያጠኑ እንዳስቻላቸው ጠቅሰዋል፡፡

በዚሁ  ወረዳ የማር ወለድ ቀበሌ አርሶ አደር ቸኮል ሁሉቃ በበኩላቸው  በፀሓይ ሃይል የሚሰራ መሳሪያ  ገዝተው መጠቀም ከጀመሩ አንድ ዓመት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

ቴሌቪዥንን ከማሳየት በተጨማሪ አራት አምፖሎችን በማብራት ዘመናዊ አኗኗርን በመልመድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ተጠቃሚዎቹ እንዳመለከቱት አማራጭ የኃይል ምንጭ የማገዶና የመብራት ወጪን  በመቀነስ እንዲሁም ጤናቸውን በመጠበቅ ኑሮቸውን ለማሻሻል  ረድቷቸዋል፡፡

በክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ  የባዮ-ኢነርጂ ምንጮችና ቴክኖሎጂዎች ልማት ዳይሬክተር አቶ ወንድም በሪሁን በክልሉ  ባለፉት ሁለት ዓመታት  አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ አማራጭ የኃይል ማንጭ መገልገያ መሳሪያዎች ለተጠቃሚዎች መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

ከተሰራጩት መካከል ከ356 ሺህ የሚበልጡት የኤሌክትሪክ አማራጭ በሌላቸው የገጠር መንደሮች በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ  ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ናቸው፡፡

ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎቹ ጥቅም ላይ መዋላቸው 364 ሺህ 800 ቶን በላይ የማገዶ እንጨትን መቆጠብ መቻሉን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

እስከ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻም ተጨማሪ ከሶስት ሚሊዮን የሚበልጡ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩና የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ለተጠቃሚዎች ለማሰራጨት እየተሰራ ነው፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በክልሉ  ከአንድ ሚሊዮን በላይ  አማራጭ የኃይል ምንጭ መገልገያ መሳሪዎች ለተጠቃሚዎች ተሰራጭተው ጥቅም ላይ መዋላቸውም ተመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ ሀምሌ 3/2009 የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በ82 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች አስረከበ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መርሻዬ ብርሃኔ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በዘንድሮው ዓመትም ዩኒቨርሲቲው ያስገነባቸውን 120 ቤቶች በኃላፊነት፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ መምህራን ቅድሚያ ሰጥቶ ማስረከቡን ገልፀዋል፡፡

በሚቀጥለው በጀት ዓመት 180 መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት 390 ሚሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨረሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተርና የባዮሎጂ ትምህርት መምህር አቶ ቶሎሳ ሙለታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለረጅም ጊዜ የቆየውን የመምህራን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ መመለሱ የመማር ማስተማር ስራውን የተቀላጠፈና የተሻለ እንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡

የመኖሪያ ቤቱ ተጠቃሚ በመሆናቸው ከመማር ማስተማሩ ባሻገር የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ስራቸውን በተገቢው ለማካሄድ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት አቅርቦቱ በስራዬ ላይ ብቻ ትኩረት እንዳደርግ ይረዳኛል ያሉት ደግሞ በዩኒቨረሲቲው የኬሚካል ምህንድስና መምህር ንጉስ ወርቁ ናቸው፡፡

''በተለይ በምርምርና ጥናት ዘርፍ ትኩረት ላደረጉ ምሁራን ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያደርግ በመሆኑ ለትምህርት ጥራት ድርሻው የጎላ ነው'' ብለዋል፡፡

በ2004 የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በስድስት ኮሌጆችና በ33 የትምህርት ክፍሎች ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሃምሌ 3/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲሱ በጀት ዓመት በስራ ፈጠራ፣ በመሬት ልማት፣ ትምህርትና ጤና ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ገለጹ።

የከተማው ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።

ከንቲባው የአስተዳደሩን ዓመታዊ ሪፖርት ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ እንዳሉት መዲናዋን ለማልማት፣ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለማጠናከርና ለመገንባት የሚረዱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት በቀጣይ በጀት ዓመትም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

ሥራ አጥነትን በተደራጀ መልኩ መፍታት፣ የመሬት ልማት አስተዳደርን ማጠናከር፣ የትምህርትና የጤና ዘርፎች በትኩረት የሚሰራባቸው እንደሆኑም ነው የተናገሩት።

የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞውን የሚያደናቅፉ አመለካከቶችና ተግባሮች በተደራጀና ኀብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የመታገል ተግባርም በበጀት ዓመቱ በትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑን ነው ከንቲባው የገለፁት።

በቤት ልማት ዘርፍም በመገንባት ላይ ያሉትን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለተጠቃሚ የማስተላለፍና አዳዲስ ግንባታዎችን በማፋጠን በተለይ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎችና ለመንግስት ሠራተኞች በኪራይ መልክ በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርባል ብለዋል።

በከተማዋ ያለውን የውሃ ችግር ለማቃለልና አቅርቦቱን ለመጨመርም ያልተጠናቀቁ ጉድጓዶችን የማጠናቀቅና በከተማዋና በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች የመቆፈር ስራ ይሠራል ነው ያሉት።

"በንግድ መስክ ያለውን ግብይት በሥርዓት እንዲመራ በማድረግ በንግድና ኢንቨስትመት ከተማዋ የምታገኘውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ በገቢ ላይ ያሉ የአመለካከትና የክህሎት ችግሮችን የመቅረፍ ስራ ይከናወናል" ሲሉም ገልጸዋል ከንቲባው።

የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።

በነገ ውሎው ዛሬ የቀረበውን የ2009 ሪፖርት በማጠቃለል ሲያጸድቅ፤ የ2010 በጀት ረቂቅና የከተማው ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ